በሰው ሠራሽ ዝናብ የሕንድ ዋና ከተማን መርዛማ አየር ማስተካከል ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት የሕንድ ዋና ከተማ በመርዛማ አየር ሰትታፈን የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ብክለቱን ለመቀነስ እንደ መፍትሔ ሰው ሠራሽ ዝናብ (ክላውድ ሲዲንግ) እየታሰበ መሆኑን ገልጸዋል።
የዕቅዱ ውጤታማነት የሚወሰነው ከሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከበርካታ የፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይሁንታ በማግኘቱ ላይ ነው።
ሐሳቡ ተቀባይነትን ካገኘ ደግሞ ያለውን የአየር ሁኔታ መሠረት በማድረግ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ሊተገበር ይችላል ተብሏል።
ዘዴው የዋና ከተማዋን የዴልሂን የአየር ብክለት ለመከላከል መፍትሔ ሆኖ ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ይህ ውስብስብ እና ውድ የሆነ ዘዴ የአየር ብክለትን ለመዋጋት በመዋሉ ረገድ ያለው ውጤታማነት ሙሉ በሙሉ ያልተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ የረጅም ጊዜ የአካባቢ ተጽዕኖውን ለመረዳት ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
የዴልሂ ብክለት ነዋሪዎችን ከመጉዳቱም በላይ ዓለም አቀፍ ዜና መሆኑ በመሪዎች ዘንድ መፍትሔ እንዲሰጥ የቆረጡ ይመስላል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የከተማዋ የአየር ጥራት መረጃ ጠቋሚ (AQI) ከ450 ማለፉን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ይህ ቁጥር መሆን ከነበረበት በ10 እጥፍ ገደማ ከፍ ያለ ነው።
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የጣለው አጭር የተፈጥሮ ዝናብ የአየር ብክለቱን አውርዶታል።
የዲዋሊ በዓልን (የሕንዶች የብርሃን በዓል ነው) ለማክበር ርችት በየቦታው መተኮሱ የከተዋን አየር ብክለት በድጋሚ አደገኛ አድርጎታል።
የተሽከርካሪ፣ የኢንዱስትሪ ጭስ ልቀት እና አቧራን ጨምሮ ዴልሂ ዓመቱን በሙሉ በብክለት ችግር ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል።
በተጨማሪም በአጎራባች አካባቢዎች ያሉ ገበሬዎች የሰብል ተረፈ ምርታቸውን ስለሚያቃጥሉ እና በዝቅተኛ የንፋስ ግፊት ወደ ከፍተኛ ብክለት ስለሚያመራ የከተማዋ አየር በተለይ በበጋ ወቅት ወደ መርዛማነት ይለወጣል።
የዴልሂ አስተዳደር በበጋ ወቅት ትምህርት ቤቶች ቀደም ብለው እንዲዘጉ እና የግንባታ እንቅስቃሴዎችን ማገዱን አስታውቋል።
ከከተማዋ መርዛማ አየር ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችን የሚሰማው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለሰው ሠራሹ ዝናብ ዕድል እንደሚሰጠው ተስፋ ሰንቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክላውድ ሲዲንግ ምንድን ነው?
ክላውድ ሲዲንግ በደመና ውስጥ ያለውን የእርጥበት መጠን በማፋጠን ዝናብ የመፍጠር ዘዴ ነው።
እንደ ሲልቨር አዮዳይድ ወይም ክሎራይድ ያሉ የጨው ቅንጣቶችን በአውሮፕላኖች ወይም በመሬት ላይ ባሉ የመርጫ መሳሪያዎች በመጠቀም በደመና ላይ ያለውን ሂደት በማፋጠን የሚከናወን ነው።
የጨው ቅንጣቶቹ በደመናው ውስጥ የበረዶ ቅንጣቶች እንዲፈጠሩ ለማስቻል ያገለግላሉ። በደመናው ውስጥ ያለው እርጥበት ወደ እነዚህ የበረዶ ቅንጣቶች ተጣብቆ ወደ ዝናብ ይቀየራል።
ይህ ሂደቱ ግን ሁልጊዜ አይሳካም።
በአየር ጥራት እና ጤንነት ላይ ተመራማሪ የሆኑት ፖላሽ ሙከርጂ እንደሚሉት፣ ይህ እንዲሳካ በከባቢ አየር ውስጥ በሚፈለገው ሁኔታ መጠን መገኘት አለበት።
“በደመና ውስጥ የበረዶ ኒውክሊየስ እንዲፈጠር ትክክለኛ የእርጥበት መጠን መኖር አለበት” ሲል ተናግሯል። እንደ የንፋስ ፍጥነት ያሉትም አስፈላጊ ናቸው። በዴልሂ ያለው የንፋስ ፍጥነት ደግሞ በጣም ተለዋዋጭ ሊሆን ይችላል።
የጨው ቅንጣቶች እንዲሁ የተወሰነ የደመና ዓይነት ውስጥ መበተን አለባቸው ሲሉ የአየር ሁኔታ ሳይንቲስቱ ጄአር ኩልካርኒ በ2018 ለዳውን ቱ ኧርዝ መጽሔት ተናግረዋል።
ይህ ዝናብን የማዝነብ ሂደት ለብዙ አሥርት ዓመታት የነበረ ነው። የአየር ንብረት ተመራማሪው እና መጀመሪያው የአገሪቱ የሜትሮሎጂ ኃላፊ የነበሩት ኤስኬ ባነርጂ በ1952 ሞክረውታል።
እአአ በ1960ዎቹ የአሜሪካ ጦር የቬትናም ወታደራዊ አቅርቦትን ለማደናቀፍ የቬትናም አንዳንድ አካባቢዎችን የዝናብ ወራት ለማራዘም ቴክኒኩን በአወዛጋቢ ሁኔታ ተጠቅሞበታል።
እንደ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ያሉ አገራት እና አንዳንድ የሕንድ ግዛቶችም የዝናብ መጠንን ለመጨመር ወይም ድርቅ መሰል ሁኔታዎችን ለመቋቋም ሂደቱን ሞክረውታል።
የዴልሂ መንግሥት ምን ለማድርግ አቅዷል?
የፕሮጀክቱ ዕቅድ በሕንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (IIT) ካንፑር ከፍተኛ የምህንድስና ኮሌጅ ተመራማሪዎች ቀርቧል።
በዕቅዱ መሠረት ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፎች የሚከናወን ነው።
የመጀመሪያው ምዕራፍ 300 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ወቅቱ ተስማሚ ነው በማለት ፕሮጀክቱ ኅዳር 20 እና 21 እንዲተገበር የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱን የሚመሩት ሳይንቲስቱ ማኒንድራ አግራዋል ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በተጠቀሱት ቀናት ዴልሂን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን በቂ ደመና ባይጠብቁም “ጥቂት መቶ ኪሎ ሜትሮች ላይ ጥሩ ይሆናል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብክለቱን ለመከላከል የሚረዳ ሊሆን ይችላል?
የዝናብ መኖር በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙትን ብናኞች በማጠብ አየሩን የበለጠ ንፁህ እና ለመተንፈስ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል የሚል አመክንዮ ነው የሚቀርበው።
አርብ እና ቅዳሜ አጭር ዝናብ ከጣለ በኋላ የዴልሂ አየር ብክለት ላይ የመቀነስ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ታይቷል።
ሰው ሠራሹ ዝናብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን ግን ግልጽ አይደለም ይላሉ ባለሙያዎች።
ሙከርጂ እንደሚሉት ከሆነ ሰው ሠራሽ ዝናብ ለሌሎች አገራት የአየር ጥራት አያያዝ እና አቧራን ለማጥፋት ቢያገለግልም ሁሌም ግን ውጤታማ አልሆነም።
“ዝናብ በአየር ጥራት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ብትመለከቱ የብክለት ደረጃውን በፍጥነት ቢቀንሰውም፤ ብክለቱ ከ48 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ይመለሳል። ሰው ሠራሽ ዝናብ ውድ ነው። ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ለማይሰጥ ዘዴ ከፍተኛ ሐብትን ማፍሰስ ዘላቂ አይሆንም” ብለዋል።
በፖሊሲ ደረጃ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባም አክለዋል። “ጊዜያዊ ውሳኔ ሊሆን አይገባም። ተከታታይ የአተገባበር እርምጃዎች ሊኖሩት ይገባል። ይህንን የሚያዘጋጅ ቡድን ከሜትሮሎጂ ባለሙያዎች፣ ከአየር ጥራት ፖሊሲ ባለሙያዎች እና ከመሳሰሉት ሊዋቀር ይገባል” ብለዋል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ስለ ሂደቱ እስካሁን የማናውቀው ነገር ሊኖር ይችላል በሚል ያሳስባቸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እና የዘላቂነት ኤክስፐርት የሆኑት አቢናሽ ሞሃንቲ “በአሁኑ ጊዜ በሰው ሠራሽ ዝናብ ምን ያህል ብናኞች እንደሚወርዱ ተጨባጭ ማስረጃ የለም” ብለዋል።
“የተፈጥሮ ሂደቶችን ለመቀየር የሚደረግ በመሆኑ የሰው ሠራሽ ዝናቡ ውጤቶቹ ምን እንደሆኑ አናውቅም። ይህ ውስንነት ይኖረዋል” ሲሉ አክለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ አየር ብክለትን “የሜትሮሎጂ እና እንደ ዝናብ እና የንፋስ ፍጥነት” ያሉትን በመጠቀም ብቻ የሚቀረፍ አይደለም።
“ወጥ ካልሆኑ እና ከስህተት ሙከራዎች ይልቅ የአየር ብክለትን ለመግታት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለብን” ብለዋል።












