ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለቤቱን ለዓመታት ያስደፈረው ግለሰብ ዘግናኝ ድርጊት እየታየበት ያለው የፍርድ ሂደት
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ አንባቢዎችን የሚረብሽ ይዘት አለው።
በፈረንሳይ ለሰው ህሊና የሚዘገንን ወንጀልን የሚዳኝ የፍርድ ሂደት ተጀምሯል።
ጂዜል ፔሊኮት የተባለችን ግለሰብ ባለቤቷ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯታል።
ይህም ለአስር ዓመታት ያህል የተፈጸመ ሲሆን፣ ግለሰቡ ባለቤቱን በተደጋጋሚ የደፈረበትን እና የማያውቋትን ወንዶች እያጋበዘ ያስደፈረባቸው ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ኮምፒውተሩ ላይ ተገኝተዋል።
ግለሰቡ ባለቤቱን የደፈረበት እና ያስደፈረበትን በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎች በማንሳት እና ቪዲዮዎችን በመቅረጽ አስቀምጧል።
አነስተኛ በሆነችው በደቡባዊቷ ፈረንሳይ፣ ማዛን የተፈጸመው ይህ ድርጊት በርካቶችን ያንቀጠቀጠ ነው። የድርጊቱን ፈጻሚዎች ሰብዓዊነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ፣ የጭካኔ ጥግን ያጋለጠ እንዲሁም የሰማውን ሁሉ ህሊና የረበሸ ሆኗል።
ባለቤቱን ያስደፈረው ግለሰብ እና ከሃምሳ በላይ ደፋሪዎች የፍርድ ሂደት ከሰሞኑ በፈረንሳይ ተጀምሯል።
የፍርድ ሂደቱ አቪግኖን በተሰኘችው ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በአንደኛው ዕለት ችሎቱ ፀጥታ ሰፍኖበት በርካቶች በመረበሽ እና በድንጋጤ በዝምታ የሚሆነውን ይከታተላሉ።
የተሰየመው ችሎት ዶሚኒክ ፔሊኮት የተባለው ግለሰብ ባለቤቱን ሲደፍር እና ሲያስደፍር የሚያሳዩ ተጨማሪ ቪዲዮዎችን በማስረጃነት የሚያቀርብበት ነው።
ግለሰቡ “ጥቃት” (አቢዩዝ) በሚል ርዕስ የሰጣቸው እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ቪዲዮዎች ለአስር ዓመታት የተቀረጹ አሰቃቂ ድርጊቶችን ያሳያሉ።
ባለቤቱ እንድትደነዘዝ እና ራሷን እንድስት ካደረገ በኋላ ከደፈሯት መካከል በ50ዎቹ ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመባት የ72 ዓመቷ ጂዜል ፔሊኮት የፈረንሳይ ሕግ የሰጣትን ማንነቷን የመደበቅ መብቷን በመተው ታሪኳንም ሆነ ራሷን ለሕዝብ ይፋ አድርጋለች።
ግለሰቧን የወከሏት ጠበቆች የተፈጸመባትን ጥቃቶች የሚያሳዩት ቪዲዮዎች በፍርድ ቤት እንዲታዩ ታግለዋል።
ምንም እንኳን ዳኛው ቀድም ብለው “ይህ በጽኑ የሚረብሻቸው” ካሉ መውጣት እንደሚችሉ ቢናገሩም ከጂዜል ፔሊኮት ጠበቆች አንዱ እንደተናገሩት በርካቶች የተፈጸመባትን መደፈሮች ለመመልከት ወስነዋል ብለዋል።
ሚስቱን እንዲደፍሩለት በኢንተርኔት የመለመላቸው ወንዶች የፈጸሙት ድርጊት መድፈር ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
በዚህ የፍርድ ሂደት ላይ ባለቤቱን የደፈረው እና ያስደፈረው ፀጉሩን ሽበት የወረረው ዶሚኒክ ፔሊኮት ወንበሩ ላይ ሸርተት ብሎ ተቀምጧል።
ጂዜል ፔሊኮት በበኩሏ ዓይኗ ዝግት፣ ክድን፣ ክፍት ሲል የታየ ሲሆን፣ ፊቷ ላይም ማንበብ የሚከብድ ስሜት ይታይባት ነበር።
ቪዲዮው መታየት ጀመረ። በስክሪኑ ላይ ሰማያዊ የውስጥ ሱሪ እና ጥቁር ካልሲ ብቻ የለበሰ አጭር እና ገርጣ ያለ ሰው ወደ አልጋው ሲጠጋ ይታያል።
ካሜራው ግለሰቡን ሲከተለው የተወሰነ መንቀጥቀጥ ያሳያል። ከግለሰቡ ጀርባ አንዲት ሴት ራቁቷን በተጨማደደ ነጭ አንሶላ ላይ በግራ ጎኗ ተኝታለች።
ከዚያም ያለ ምንም ብዥታ የመደፈሩ ድርጊት በግልጽ ይታያል።
በመሃልም ላይ በጥልቅ እንቅልፍ ላይ የነበረችው ግለሰብ ስታንኮራፋ ይሰማል።
ይህንን እየተመለከተ የነበረው ዶሚኒክ ጆሮውን በሁለት እጆቹ ጥርቅም ሲያደርግ ይታያል።
ግለሰቡ ለዓመታት የባለቤቱን ምግብ እና መጠጥ በጭንቀት መድኃኒት እና በእንቅልፍ እንክብል ሲመርዝ ቆይቷል።
ሚስቱ በየምሽቱ ራሷን ከመሳት በተጨማሪ ጤንነቷ ክፉኛውኑ ተጎድቷል።
ይህ እና መሰል ቪዲዮዎች በፍርድ ቤቱ የታዩ ሲሆኑ በርካቶችም ችሎቱን አጨናንቀውት ነበር።
የግለሰቡን ግብዣ ተቀብለው ወደ ቤቱ የመጡ ከ50 በላይ ወንዶች ሚስቱ ራሱን እንደሳተች ያውቃሉ ሲሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ይከራከራሉ።
እነሱ እንደሚሉት የተኛች በማስመል የወሲብ ጨዋታ ሳይሆን ፈቃደኛ እንዳልነበረች ያውቁ እንደነበር እና ሊደፍሯት አቅደው ነበር ይላሉ።
ግለሰቦቹን የወከሉት ጠበቆች ራሷን እንደሳተች አያውቁም ነበር ሲሉ ይከላከላሉ።
በዚህ ግለሰቧን እየደፈረ እንደሆነ በቪዲዮ ላይ የታየው ግለሰብ የ43 ዓመት አናጢ ነው።
አንገቱን አቀርቅሮ የቀረበውን ይህንን ግለሰብ ዳኛው “የተከስስክበትን የመድፈር ወንጀል ዝርዝር ታውቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት።
ግለሰቡም “አላውቅም” የሚል ምላሽ ሰጠ።
ዶሚኒክ የተባለው ግለሰብ ባለቤቱ በአንድ የወሲብ ጨዋታ ፈቃደኛ እንደሆነች እንደነገረው እና ከዚያ በኋላ ብዙም እንዳላሰበበት ማብራሪያ ሰጠ።
በዚህም ወቅት ጂሴል “ይህንን ሰው መታገስ አልችልም” ብላ ከፍርድ ቤቱ ለትንሽ ደቂቃ ያህል ወጣች።
ግለሰቡ ሁኔታው ትንሽ ግራ እንዳጋባው እና ከዚህ ቀደም ገጥሞት እንደማያውቅ አስረድቷል። ሆኖም “በወቅቱ ብዙ አላሰብኩበትም” ብሏል።
ሆኖም እናቱን፣ የሕግ ባለሙያዎችን እና ፍርድ ሂደቱን በመመልከት ስለ ፈረንሳይ ሕግ፣ ስለ መድፈር ትርጉም እና ስለፈጸመው ድርጊት ክብደት የበለጠ ተረድቻለሁ ብሏል።
“በአሁኑ ወቅት ስለተፈጸሙት ክስተቶች ስረዳ የፈጸምኩት ድርጊት መድፈር እንደሆነ ነው” ብሏል።
ጂዜል ፔሊኮት “የጥቃትህ ሰለባ መሆኗን ተረድተሃል?” ወይ ተብሎ በዳኛው ሲጠየቅ፤ “አዎ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ፔሊኮት የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ አምኗል።
ጂዜል ይህንን አስደንጋጭ ሁኔታ የተረዳችው ከአራት ዓመታት በፊት ነው።
ለአምስት አስርት ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው ባለቤቷ ከ80 በላይ የሚሆኑ ወንዶችን በመጋበዝ እንዳስደፈራት እና ድርጊቱን እንደቀረጸው የተረዳችው ከፖሊስ ነው።
በመድፈር ወንጀሉ ላይ የተሳተፉት ወንዶች ቁጥር ብዛት ፈረንሳይን አስደንግጧል።
በቪዲዮው ላይ ከታዩት 83 ወንዶች መካከል ፖሊስ መለየት የቻለው 50ዎቹን ብቻ ነው።
ዕድሜያቸው ከ26 እስከ 68 ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ያሉ ናቸው። የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፋርማሲስቶች፣ ነርስ፣ የእስር ቤት ጠባቂ፣ ጋዜጠኞች ተካተውበታል። በርካቶች የልጆች አባት እና ባለትዳሮች ናቸው።
አንደኛው ኤችአይቪ በደሙ እያለ እያወቀ ስድስት ጊዜ እንደደፈራት ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳን ኤችአይቪ ባይተላለፍባትም ሌሎች በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ተይዛ እንደነበር የጤና ባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የጤና እክሎች እንደተከሱባት ተገልጿል።
ከተከሰሱት ውስጥ 15ቱ መድፈራቸውን ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ በወሲባዊ ድርጊት ብቻ ተሳትፈናል ብለዋል።
ዶሚኒክ በአንድ ድረ ገጽ ላይ “እሷ ሳታውቅ” ከባለቤቱ ጋር ወሲብ እንዲፈጽሙ አንድ ጽሁፍ መለጠፉን ተከትሎ ነው በርካቶች የመጡት።
ድረ ገጹ በአሁኑ ወቅት የተዘጋ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 500 ሺህ ጎብኚዎች ነበሩት።
ፖሊስ ባደረገው ምርመራ 4 ሺህ የሚሆኑ ጂሴል የምትደፈርበትን ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች አግኝቷል።
ድርጊቱ ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2020 የተፈጸመ ሲሆን፣ 200 ገደማ መደፈሮችን ይዘዋል።
ሁኔታው ይፋ የሆነው ግለሰቡ በአንድ መደብር ውስጥ ተደብቆ የሴቶች ቀሚስ ስር ፎቶ ሲያነሳ በመያዙ ነበር።
በዚህም ነበር የግለሰቡ ኮምፒውተር የተፈተሸው።
ጂዜል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስትጠራ በሱቁ መደብር ውስጥ ባለቤቷ ስላነሳቸው ፎቶዎች ልትጠየቅ እንደነበር ነው ያሰበችው።
ስለ ወሲብ ሕይወቷ ፖሊስ ሲጠይቃት “ከባለቤቷ በስተቀር ሌላ ወንድ አላውቅም” ስትል መለሰች።
ፖሊሱም ደስ የማይል ነገር ላሳይሽ ነው ብሎ “ስደፈር የሚያሳይ ፎቶ አሳየኝ።”
“አለሜ ሁሉ ተገለባበጠ” ትላለች።
ጂዜልን በትዳራቸው ደስተኛ እንደነበሩ እና ከገንዘብ፣ ከጤና ጋር የተያያዙ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳለፉ ተናግራለች። በመደብሩ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር እንደማይደገም ይቅርታ ጠይቆ ይቅር ብላው እንደነበረ ገልጻለች።
“አብረን የገነባነው ሁሉ ጠፋ። ሦስት ልጆች፣ ሰባት የልጅ ልጆችን አፍርተናል። የምንዋደድ ባልና ሚስት ነበርን” ብላለች።
በአቪግኖን የተጀመረው የፍርድ ሂደት ለበርካታ ሳምንታት የሚቀጥል ሲሆን፣ ውሳኔውም ከፈረንጆቹ ገና በፊት እንደሚበየን ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ ከተከሳሾቹ መካከል ግማሽ ያህሉ ምስክርነት እንዲሰጡ ተጠርተዋል፤ ነገር ግን የደረሰባትን ዘግናኝ፣ ለሰው ህሊና የሚከብድ አሰቃቂ ድርጊት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
ጂዜል ታሪኳን እንዲሁም ማንነቷን በማውጣት ድፍረቷን እንዲሁም ጀግንነቷን አሳይታለች።
የጂሴል ጉዳይ ስለ ፈረንሳይ ሕጎች፣ መደፈርን በተመለከተ የቀደሙ ክርክሮች እንዲሁም የሴት ፈቃደኝነት እንዴት ይገለጻል? እስከምን ድረስ? የሚሉ ጉዳዮች እንደገና መወያያ ሆነዋል።
በጂዜል ጉዳይ በርካታ ወንዶች ጥፋታቸውን አምነዋል፤ በሰሞኑ የፍርድ ሂደት ምስክርነቱን የሰጠው ግለሰብ ጂሴልንን ይቅርታ ጠይቋል።
ሆኖም ሁሉም ለመድፈር ስላላሰቡ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንዳያደርጋቸው አጥብቀው ይከራከራሉ።