በናይጄሪያ መስጊድ ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ አምስት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ ቦርኖ ግዛት ውስጥ በሰዎች በተጨናነቀ መስኪድ ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ናሁም ዳሶ ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን በዋና ከተማዋ ማዱጉሪ በሚገኘው የጋምቦሩ ገበያ በሚገኝ መስኪድ ውስጥ በምሽት ፀሎት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በደረሰው ፍንዳታ 35 ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የሚዘዋወሩ እና ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎች ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላ ሰዎች በገበያ ቦታ ላይ በአቧራ ተከብበው እንደነበር ያሳያሉ።
ጥቃቱን የፈፀመ ቡድን ማን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን ታጣቂዎች ቀደም ሲል በአካባቢው በሚገኙ መስኪዶችና በተጨናነቁ ቦታዎች ላይ የአጥፍቶ ጠፊ እና በቤት ውስጥ በሚሰሩ ፈንጂዎች ጥቃት ሲፈጽሙ ነበር።
ፖሊስ የመጀመርያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርቶች የተፈጸመው ጥቃት በአጥፍቶ ጠፊ የተፈጸመ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ፖሊስ በጥቃቱ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራዎች እያደረገ መሆኑን የቦርኖ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
ዳሶ ጥቃት የተፈጸመበት አካባቢ ተጨማሪ ጥቃቶች ሊያደርሱ የሚችሉ ተቀጣጣይ ነገሮች አለመኖራቸውን ምረምራ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ክልል በቦኮ ሃራም እና ከቡድኑ ተለይቶ በወጣው ኢስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ ፕሮቪንስ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸማሉ።
እአአ ከ2009 ጀምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ሚሊዮኖች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
ማዱጉሪ በታጣቂው እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሃራም እና ኢስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ ፕሮቪንስ ዋና ማዕከል ሆና ቆይታለች።
ቦኮ ሃራም በቦርኖ ግዛት ውስጥ እስላማዊ ካሊፌት ለመመስረት የሚያካሂዱት ወታደራዊ ዘመቻ የተጀመረው እአአ በ2009 ነበር።
በቡድኑ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ አልፎ አልፎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል አልቻሉም።















