መቀለ እና ባሌ የታዩት ኦባሳንጆ የሰላም ጥረቱ ‘ዘገምተኛ’ ነገር ግን ‘ወደፊት እየሄደ ያለ’ ነው አሉ

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውይይት ለመቋጨት የሚደረገው ጥረት ‘ዘገምተኛ’ ነገር ግን ‘ወደፊት እየሄደ ያለ’ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ከቀናት በፊት በመቀለ ከህወሓት ሊቀመንር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር እየተነጋገሩ ታይተዋል።

ዛሬ ደግሞ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕምድ ጋር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ሮቤ ከተማ ላይ ተገኝተዋል።

ጦርነት ውስጥ የገቡትን የፌደራሉን መንግሥት እና ህውሓትን ለማደራደር በርካታ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፤ “ለውጥ አለ ግን ዘገምተኛ ነው። ዛሬ ያለው ሁኔታ ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው የተሻለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“እያደረግን ያለነው፤ ማድረግም ያለብን መተማመን [በተዋጊዎች መካከል] መፍጠር የሚያስችል ስራዎችን መስራት ነው” ያሉት ኦባሳንጆ፤ እየመሩት ያለው የድርድር ጥረት ሁለት ውጤቶችን እንዲያስመዘግብ ፍላጎታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ኦባሳንጆ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እና በድርድር ተኩስ ማቆም የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረስ ፍላጎታቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኦባሳንጆ “ይፋዊ የግጭት ማቆም ውሳኔ እንዲኖር እንፈልጋለን” ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም በተደጋጋሚ ጥረት እያደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በቅርቡም በጦርነቱ ተሳታፊ ከሆነ አካላት መሪዎች ጋር የታዩት፤ የትግራይ ኃይሎች እና የኤርትራ ጦር በአዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው በተሰማ ማግስት ነው።

ኦባሳንጆ ማክሰኞ ግንቦት 23/2014 ዓ.ም. ከህወሓት ሊቀመንር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር “በቀጠናዊ ጉዳዮች” መነጋገራቸው ተገልጿል።

ኦባሳንጆ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 25/2014 ዓ.ም. ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከተመራው ልዑክ ጋር ለሥራ ጉብኝት ባሌ ሮቤ ከተማ ላይ ተገኝተዋል።

“በጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አልፈልግም”

የአፍሪካ ሕብረት ለኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥ የተናገሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት፤ የሰላም ስምምነት በቅርብ የሚመጣ ይምስልዎታል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አልፈልግም” ብለዋል።

“አሁን ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም አድርገዋል። ይህ ለሰብዓዊነት ሲባል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት በድርድር ወደሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ማደግ አለበት። ይህ ስምምነት ደግሞ ወደ ይፋዊ ለግጭት አለመፈላለግ ስምምነት ሊያሸጋግረን ይገባል” ብለዋል።

ኦባሳንጆ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ለግጭት ላለመፈላለግ ከስምምነት እንዲደርሱ ማድረግ ምን ያክል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል እርግጠኛ አይደሉም።

“ይህን ማሳካት የሚቻለው በ1 ወር፣ 3 ወር፣ 6 ወር ወይም በአንድ ዓመት ይሁን አላውቅም ግን ብዙዎች ከሚገምቱት በፊት እናሳካዋለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግጭት ማቆም፣ ግጭትን መግታት፣ ለግጭት አለመፈላለግ . . . ምን ማለት ነው?

የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ማቆም (Humanitarian Truce) ሆነ የተኩስ አቁም ስምምንት (Cease Fire) በአንድ አካባቢ የሚካሄድን ግጭት ለማብረድ ቁልፍ ሚና ቢኖራቸውም፣

 ተፈጻሚነታቸውም ሆነ ከዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚታለፉ ዝርዝር ሁኔታዎች የተለያዩ ናቸው።

በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሁለት ጎራ ሆነው ሲፋለሙ የነበሩት አሜሪካ እና ሩሲያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለግጭት አለመፈላለግ (cessation of hostilities) የሚል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

በወቅቱ በኪንግስ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን በጦርነት ጉዳዮች ጥናት መምህር እና ፀሐፊ የሆኑት ሳሚር ፑሪ፤ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭትን መግታት/ማቆም (Humanitarian Truce)፣ ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities)፣ የተኩስ አቁም ስምምነት (Cease Fire) እና ግጭትን ማብቃት (Armistice) ልዩነቶች ላይ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

ግጭትን መግታት(Truce)

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ከሆነ ግጭት ለመግታት ስምምነት ተደረሰ ማለት፤ በተዋጊዎች መካከል በጊዜያዊነት ተኩስ ለማቆም 'ብዙ ያልተመከረበት ስምምነት' መኖሩን ያመላክታል ይላሉ።

ተዋጊዎች ግጭት ለመግታት ከስምምነት ለመድረስ (Truce) ይፋዊ እና ሥርዓትን የተከተለ ስምምነት ላይ መድረስ አይጠበቅባቸውም።

በዚህ ውሳኔ ተፋላሚ ኃይሎች ረዥም ጊዜ የዘለቀ ጦርነት ጋብ እንዲል እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲገታ ሊስማሙ ይችላሉ።

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ከሆነ ተዋጊ ኃይሎች በሁሉም ግንባሮች ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ግንባር ብቻ ግጭት ለመግታት ሊወስኑ ይችላሉ። ለሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ተዋጊዎች ግጭትን ለመግታት ውሳኔ ሊያሳልፉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።

ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities)

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities) እንደ የተኩስ አቁም ስምምነት (Cease Fire) ይፋዊ እና ዝርዝር ነገር ባይኖረውም ግጭትን ለመግታት (Truce) ከሚደረስ ስምምነት የተሻለ ይፋዊ የሆነ ሥርዓት አለው።

ተዋጊ ኃይሎች ለግጭት ላለመፈላለግ (Cessation of hostilities) ስምምነት ደረሱ ማለት፤ ላለመዋጋት እና ሠራዊታቸው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ ተስማምተዋል ማለት ነው በማለት ያብራራሉ።

ይኹን እንጂ ይላሉ ዶ/ር ሳሚር፤ "ይሁን እንጂ፤ በግጭት ላለመፈላለግ መስማማት (Cessation of hostilities) ተኩስ ማቆም ማለት አይደለም።" ነገር ግን ይህ ለግጭት ላለመፈላለግ የሚደረስ ስምምነት ዘላቂ ለሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።

እንደ ዶ/ር ሳሚር ገለጻ ለግጭት ላለመፈላለግ የተስማሙ ተዋጊዎች በአንድ አካል ትንሽ ጠብ አጫሪነት ስምምነታቸው በቀላሉ ፈርሶ ወደለየለት ጦርነት ተመልሰው ሊገቡ ይችላሉ።

ተኩስ አቁም (Ceasefire)

በተዋጊዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት (Ceasefire) ተደረሰ ማለት፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ወገኖች በሚገዛ ስምምነት ተዋጊ ኃይሎች ግጭት ለማቆም ቁርጠኝነት አሳዩ ማለት ነው ይላሉ ዶ/ር ሳሚር።

የተኩስ አቁም ስምምነት ትጥቅ መፍታት፣ ወታደሮች ይዘዋቸው ከሚገኙ ቦታዎች መልቀቅ፣ ቀጠናዎችን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግን ሊያካትት ይችላል።

ግጭትን ማብቃት (Armistice)

እንደ ዶ/ር ሳሚር ገለጻ ግጭትን የማብቃት ስምምነት (Armistice) በመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚመጣ ነው።

ተዋጊ ኃይሎች ከተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ዘላቂ ሰላም ስለሚመጣበት ሁኔታ ከስምምነት ሲደርሱ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ግጭትን ለማብቃት ተስማሙ ማለት ይቻላል ይላሉ።

ግጭትን ለማብቃት የሚደረጉ ስምምነቶች ሕጋዊ ኃላፊነቶችን ይዘው ይመጣሉ።

እንደ ምሳሌም ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በይፋ እንደቆሙ ያረጋገጡት ከስምምነት የተደረሱ ግጭትን የማብቃት (Armistice) ስምምነቶች መሆናቸውን ዶ/ር ሳሚር ያብራራሉ።