የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ መቀለ እንደሚገኙ ተገለጸ

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ናይጄሪያዊው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ትግራይ ክልል እንደሚገኙ ተገለጸ።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት መቀለ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ከህወሓት ሊቀመንር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር እየተነጋገሩ የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል።

አቶ ጌታቸው “ከቀጠናዊ ጉዳዮች ጋር ለመምከር ዛሬ ፕሬዝደንት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሳንጆን ተቀብለዋል” ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ኦባሳንጆ በትግራይ የተገኙት ባለፉት ቀናት በትግራይ ኃይሎች እና በኤርትራ ሠራዊት መካከል ጦርነት ተካሂዶ እንደነበረ በተገለጸበት ወቅት ነው።

ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገውን ጦርነት እና ፍጥጫ ለማስቆም በተደጋጋሚ ጥረት እያደረጉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሰላም ለማውረድ የሚካሄደውን ጥረት በተመለከተ ምንም ሳይሰማ ወራት ተቆጥረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በናይጄሪያ እና በኬንያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ንግግር እየተካሄደ መሆኑን የሚያመለክቱ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ሲወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ግን፣ በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ምንም አይነት ድርድርን የተመለከተ ነገር እንዳልነበረ ለቢቢሲ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ከተማ ላይ ጥቃት ከፍቷል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአንድ ሳምንት በፊት ማለትም ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ. ም. የኤርትራ ጦር ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበረ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።

ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ታማኝ ምንጮች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ በኤትራ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ተካሂዷል ስለተባለው ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ያለው ነገር የለም።

የኦባሳንጆ የአዲስ አበባ እና መቀለ ጉዞዎች

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባና መቀለ የተመላለሱ ሲሆን፣ ወደ ትግራይ ለመጨረሻ ጊዜ በመሄድ ከህወሓት አመራሮች ጋር የተነጋገሩት ጥር 2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበረ።

ኦባሳንጆ ሰላም ለማምጣት በተደጋጋሚ ላደረጉት ጥረት ከሁለቱም ወገኖች በኩል አውንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን የተናገሩ ቢሆንም ይህን ነው የሚባል ፍጥጫውን የሚያስቆም መቋጫ ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነቱ ተፋፍሞ ከነበረበት ከጥቅምት ወር ወዲህ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ቢያንስ ለሦስት ጊዜያት ያክል ወደ ትግራይ ተጉዘው ከህወሓት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከወራት በፊት በነበራቸው ጉዞ ከትግራይ በተጨማሪ ጦርነቱ ተስፋፍቶባቸው የነበሩትን የአማራ እና የአፋር ክልል ባለሥልጣናትን ስለማነጋገራቸው ተዘግቦ ነበር።

ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ በተጨማሪ የጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም አስካሁን የተገኘ ውጤት የለም።

ባለፈው መጋቢት ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀው የሰብአዊነት ተኩስ አቁምን የትግራይ ኃይሎች ከተቀበሉት በኋላ ግጭቶች የቆሙ ሲሆን የአርዳታ አቅርቦትም ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑ ተዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜ የእርስ በእስር ጦርነቱ ጋብ ይበል እንጂ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ ነው በማለት ይካሰሳሉ።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የትግራይ ኃይሎች በፌደራሉ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተከትሎ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩትን በመቅጠፍ በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።