ጋና በቴል አቪቭ ዜጎቼ ተጉላልተዋል በሚል እስራኤላውያንን ከአገሯ አባረረች

የጋና ኮቶኮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ጋና ረቡዕ ዕለት ወደ አገሪቱ የገቡ ሦስት እስራኤላውያንን ዜጎቼ በእስራኤል ቤን ጉሪዮን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደል ተፈጽሞባቸዋል በሚል አባረረች።

በቴልአቪቭ በሚካሄድ የመረጃ መረብ ደኅህንነት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ያመሩ አራት የጋና መንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሰባት ጋናውያን ያለምንም ማብራሪያ ለሰዓታት በእስር እንዲቆዩ ተደርጓል ተብሏል።

ጋናውያኑ ለአምስት ሰዓታት ያህል በእስር እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ ሦስቱ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሌሎቹ ግን እንዲገቡ እንደተፈቀደላቸው የጋና መንግሥት አስታውቋል።

የጋና መንግሥት ሁኔታውን "ክብርን ዝቅ የሚያደርግ አያያዝ" በማለት አውግዟል።

የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአክራ የሚገኙ የእስራኤል ከፍተኛ ዲፕሎማት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠራታቸውን እና ሁለቱም አገራት የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጿል።

ቢቢሲ ከእስራኤልን ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱ አገራት ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ የወዳጅነት ግንኙነት እንደነበራቸው ጠቅሶ፣ ይህ የእስራኤል ድርጊት ከታሪካዊ ግንኙነታቸው ጋር የማይጣጣም ነው ብሏል።

"የጋና መንግሥት የእስራኤል ባለሥልጣናት የፈጸሙትን ድርጊት የጋና ተጓዦችን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ዒላማ እንዳደረገ ይቆጥረዋል፤ እንዲሁም በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን አሳፋሪ አያያዝ በተመለከተ በጽኑ ይቃወማል" ሲል በመግለጫው አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ዜጎቻችን [እስራኤል] ሌሎች መንግሥታት ዜጎቿን እንዲያስተናግዱ በምትጠብቅበት መንገድ በክብርና በአክብሮት እንዲያዙ እንጠብቃለን" ሲልም አክሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ ለአንድ የአገራቸው መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ከእስራኤል ለሚመለስ እያንዳንዱ ጋናዊ አንድ እስራኤላዊ እንደሚያባርሩ ተናግረዋል።

በጋና እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት መነሻ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆንም፣ ጋና በእስራኤል እና በፍልስጤም ግጭት ላይ ያላት የቅርብ ጊዜ አቋም ለዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በመስከረም ወር ጋና የእስራኤል የአየር ኃይል በኳታር የፈጸመውን ድብደባ "የዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የሚጥስ" እና የኳታርን ሉዓላዊነት የሚያዋርድ በማለት አውግዛለች።

እስራኤል በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ የተሰበሰቡትን ከፍተኛ የሐማስ መሪዎችን ዒላማ በማድረግ ነበር የአየር ጥቃት የፈጸመችው።

ባለፈው ወር የጋና ባለሥልጣናት በጋዛ የሚሰቃዩ ሰላማዊ ሰዎች ሁኔታ "ልብ የሚሰብር" ነው በማለት እስራኤል ወደ ጋዛ ተጨማሪ እርዳታ እንዲገባ እንድትፈቅድ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ 40 ቶን የጋና ቸኮሌት እና የካካዎ ምርቶችን ለፍልስጤማውያን በስጦታ አበርክተዋል።

ይህም አገሪቱ ፍልስጤማውያን ነጻ አገር ለመመሥረት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያሳይ ተገልጿል።

ተንታኞች እንደሚጠቁሙት እነዚህ እርምጃዎች በተለይም እስራኤል የጋናን አቋም አድሏዊ ወይም አሉታዊ እንደሆነ አድርጋ የምትመለከተው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ላለው የሻከረ ግንኙነት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይሁን እንጂ ጋና ጉዳዩ የእስራኤል ኤምባሲ ዜጎቿን ከቴል አቪቭ በማባረር ጉዳይ ውስጥ ትብብር አላደረገም ከሚለው ክስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሯታል።

ጋና በቴል አቪቭ የሚገኘው ኤምባሲዋ "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚከተል እና ምላሽ የሚሰጥ ነው" ብላ አጥብቃ ትከራከራለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ስድስት ሰዎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ድጋፍ እንደምትፈልግ ተናግረዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ከጋቦን ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ለመጓዝ በጣም ታማሚ ነው።