የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የብድር ስምምነት ሊያጸድቅ ነው

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕንጻ እና የአይኤምኤፍ አርማ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባ የብድር ስምምነትን እንደሚያጸድቅ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ምክር ቤቱ ነገ የሚያካሂደውን አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው።አፈ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባውን የጠሩት የምክር ቤቱ አባላት ዕረፍት ላይ በመሆናቸው ምክንያት ነው።

በ2008 ዓ.ም. ወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ፤ “ምክር ቤቱ በዕረፍት ላይ እያለ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚሹ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣን እና ተግባር የሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ ክፍል፤ “[ምክር ቤቱ] የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያጸድቃል” ሲል ይደነግጋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያጸድቀው የብድር ስምምነት የትኛው እንደሆነ ባይጠቀስም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ በተራዘመ የብድር አቅርቦት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁን አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው በአፋጣኝ ለአገሪቱ እንደሚለቀቅ የተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰኞ ሐምሌ 22/ 2016 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፏል።

በአራት ዓመታት የሚለቀቀው ይህ ብድር “መንግሥት እየተገበረው ያለውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ለመደገፍ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ለማስወገድ፣ የውጭ ዕዳ አከፋፈል ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በግል ዘርፉ የሚመራ ዕድገትን መሠረት መጣል” እንደሆነም አስታውቋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይህንን ያስታወቀው አገሪቱ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን መሠረት ባደረገ መልኩ ብር ከዶላር አንጻር 30 በመቶ ማዳከሟን ተከትሎ ነው።

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለዓመታት መንግሥት ብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ ተመን ማዳከም እንዳለበት ሲጎተጉቱ ነበር።

ለአስርት ዓመታት አገሪቱ ስትመራበት የነበረውን በመንግሥት የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት (ፊክስድ ፎሬይን ኤክስቸንጅ ማርኬት) አሠራርን በተመለከተ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ሲተች ቆይቷል።

ተቋማቱ ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ ከፍ ያለ በመሆኑም የወጭ ንግድን ለማበረታታት በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት ቢዘረጋ አገሪቱ ያለባትን ማነቆ መፍታት እንደሚያስችላት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት ይደረግለታል የተባለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል።

መንግሥት ይህንን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውንም የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከል እና የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለትን ለመፍታት፣ የዋጋ ግሽበትን ለማውረድ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን ማዘመን፣ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የአገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ አገራዊ የልማት ፍላጎቶትን በአገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል በመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነትን ማዳበር፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት እንደሆኑ ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት እነዚህን ግቦች ለማሳካት ይረዱኛል ያላቸውን በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፣ የመንግሥት ገቢን ማሳደግ ያስችላል የተባለውን የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲሁም የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደር ማሻሻያዎችን አውጥቷል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፍ እንደሆነም ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል መንግሥት ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ለመደጎም መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

መንግሥት ድጎማ ይደረግባቸዋል ያላቸው ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት እና የምግብ ዘይትን የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ አራት መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚኖረው ጫና በአንድ ጊዜ ወደ ሕዝቡ እንዳይወርድ እንደሚደረግም ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

ይህንንም አስመልክቶ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አንቶኒየት ሳየህ በተቋሙ ድረገጽ ላይ በወጣው መግለጫ በነዳጅ እና ማዳበሪያ ላይ የሚደረገውን ድጎማ “ጊዜያዊ” ሲሉ የጠሩት ሲሆን በሂደትም እነዚህ ድጎማዎች ሊቀሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

መንግሥት እነዚህን ማሻሻያዎች ለመተግበር “የሽግግር ወቅት ወጪዎችን እና የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ” 13.5 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከውጭ አጋሮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓመታት በፊት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ድጋፍ በተመለከተ ባደረገው ውይይት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው በሂደት ብርን ማዳከምና ከትይዩው ገበያው ጋር ማመጣጠን ነበር ።

አገሪቱ ከገባችበት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመውጣት የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም፣ አይኤምኤፍ ብድር ሲያመቻችላትም ከተቀመጡላት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በዋነኝነት የብር የውጭ ምንዛሪ ተመንን በፍጥነት መቀነስ እና የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በሂደት በገበያ ፍላጎት እንዲወሰን ማድረግ የሚሉ ነበሩ።

ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ ይህንን የብድር ድጋፍ ለማግኘት የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር፣ የመንግሥትን ወጪን መቀነስ እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችም ተቀምጠውላታል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ የምንዛሪ ተመንን ማዳከም ወደ ውጭ አገር ምርታቸውን የሚልኩ ባለሃብቶችን እንዲበረታቱ እና የንግድ ጉድለቱ እንዲስተካከል፣ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ እንዲሁም ያለባትን ማነቆ እንድትቀርፍ ያስችላል ሲሉ ቆይተዋል።

ነገር ግን ለዓመታት በተዛባ የንግድ ሥርዓት በተለይም የወጪ እና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ስትፈተን የቆየችው ኢትዮጵያ ብሯን ማዳከሟ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበትን እንዲሁም ተጨማሪ የንግድ ሚዛን ጉድለት ያመጣል የሚሉ ስጋቶችንም ጭሯል።

ተቋሙ ለኢትዮጵያ የሰጠው የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሌሎች የልማት አጋሮች እና አበዳሪዎች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲገኝ እንደሚያበረታታም መግለጫው ጠቁሟል።