ቼልሲ ከአርሰናል - ማን ያሸንፋል? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ውጤት ግምት

ማንቸስተር ሲቲ ከ2018 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፏል። ቅዳሜስ ምን ይጠብቀው ይሆን?

ሲቲ ቅዳሜ ከተሸነፈ ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የከፋ ጊዜ ያሳልፋል ማለት ነው። ሲቲዎች በ2006 መርሃ ግብር ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፈው ነበር።

“ሲቲ በዚህ ሰዓት ብራይተንን አይችለውም” ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።

እሑድ በሚደረግ ጨዋታ ደግሞ ቼልሲ በስታንፈድር ብሪጅ አርሰናልን ያስተናግዳል። ይህን የሰሜን ለንደን ደርቢ ማን ያሸንፋል? ሱተን ግምቱን አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ብሬንትፈርድ ከቦርንመዝ

በአሁኑ ወቅት ጥሩ አቋም ላይ ያሉ ሁለት ቡድኖች የሚገናኙበት ጨዋታ ነው። እንዴት ነው ይህን ጨዋታ የምገምተው?

ቦርንመዝ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከአርሰናል፣ ከአስተን ቪላ እና ከማንቸስተር ሲቲ 7 ነጥቦች አግኝቷል። ብሬንትፈርድ ደግሞ በሜዳው ምርጥ አቋም ላይ ነው።

ቦርንመዝ አጥቂያቸው ዲሞኒክ ሶላንኬን ለቶተንሃም ሲሸጡ ግብ ማን ያስቆጥርላቸዋል? የሚል ጭንቀት ነበረኝ። ነገር ግን ቡድኑ በጋራ ስለሚጫወት ይህ ግራ አልገባውም።

ብሬንትፈርድ በሜዳው ይሸነፋል የሚል እምነት የለኝም። ጨዋታው በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።

ግምት፡ 1 - 1

ክሪስታል ፓላስ ከፉልሃም

ፓላስ ወደ አቋሙ እየተመለሰ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ሊያጣጥሙ ጫፍ ደርሰው ነበር። በ96ኛው ደቂቃ ዎልቭስ ላይ ያስቆጠሩት ግብ ተሽሮባቸዋል። እኔ ጎሉ መቆጠር ነበረበት ብዬ አምናለሁ።

ፉልሃም በሜዳቸው ጠንካራ ናቸው። ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ነጥቦች ማግኘት ችለዋል።

ይህም ጨዋታ በአቻ ይጠናቀቃል ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ዌስት ሃም ከኤቨርተን

ዌስት ሃም አደጋ ላይ ናቸው። በአዲሱ አሠልጣኝ ጁለን ሎፔቴጊ ሥር ቅርፅ አልባ ሆነዋል። በሜዳቸው ማንቸስተር ዩናይትድን ቢረቱም ዕድለኛ በመሆናቸው እንጂ ማሸነፍ የሚገባቸው ጨዋታ አልነበረም።

ምንም እንኳ ዌስት ሃም በደረጃ ሰንጠረዡ ከኤቨርተን በላይ ቢሆንም ኤቨርተን የተሻለ አቋም ላይ ነው። ኤቨርትን ባለፈው ሳምንት በሳውዝአምፕተን መሸነፋቸው ያልጠበቁት ነበር።

ኤቨርተን ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው ክለብ ኢፕስዊችን ብቻ ነው። ይህን ጨዋታም ያሸንፋሉ የሚል እምነት የለኝም።

ይህንን ጨዋታ አቻ ማለት ባልፈልግም ከዚያ እንደማይዘል እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 2

ዎልቭስ ከሳውዝአምፕተን

ይህ የወራጅ ቀጠና ፍልሚያ ነው። ለሁለቱም ክለቦች አሠልጣኝ ትልቅ ጨዋታ ነው። ምንም እንኳ የሁለቱም ክለቦች ውጤት ደካማ ቢሆንም አጨዋወታቸው ግን መልካም ነው።

የሳውዝአምፕተኑ አሠልጣኝ ረስል ማርቲን ቡድኑ ውጤት ባያመጣም የአጨዋወት ቅርፁን መቀየር አለመፈለጉን አደንቅለሁ። ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ድል አጣጥመዋል።

በዚህ ጨዋታ ግን ዎልቭስ የተሻለ ነገር ያሳያል የሚል ግምት አለኝ። ተጫዋቾቹ ግብ ማስቆጠር ይችላሉ።

ግምት፡ 2 - 0

ብራይተን ከማን ሲቲ

ብራይተን ባለፈው ሳምንት ወደ አንፊልድ ተጉዘው ከሊቨርፑል ጋር እልህ አስጨራሽ ጨዋታ ቢያደርጉም ተሸንፈዋል።

ከበረኛው ጀምሮ በሙሉ መተማመን ኳስ መሥርተው ለመጫወት የሚያደርጉት ሙከራ የሚደነቅ ነው። ሊቨርፑል 1 ለምንም ከመመራት ተነስቶ ቢያሸንፍም ብራይተን የአቅሙን አድርጓል።

ማንቸስተር ሲቲ የውጤት ቀውስ ውስጥ ነው ያለው። ማክሰኞ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በስፖርቲንግ ሊዝበን መሸነፋቸውን ተከትሎ አማካዩ በርናንዶ ሲልቫ “ከባድ ጊዜ ላይ ነን” ብሏል።

ቢሆንም ሲቲ ሻምፒዮን ነው። ከውድቀቱ መነሳት ይችላል።

ግምት፡ 1 - 2

ሊቨርፑል ከአስተን ቪላ

አስተን ቪላ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከክለብ ብሩገ ጋር የነበራቸው ጨዋታ በሽንፈት ተጠናቋል። ከቪላ የተሻለ ነገር ጠብቄ ነበር።

ቪላ ወደ አንፊልድ መጥቶ መታገል ካለበት የተሻለ አቋም ማሳየት ይጠበቅበታል። ነገር ግን የአርን ስሎት ሊቨርፑል የወቅቱ አቋሙ እጅግ ጠንካራ ነው። ለቪላ ይንበረከካሉ ብየም አላስብም።

ሞሐመድ ሳላህ ይቆያል ወይ የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል። ሳላህ የመጨረሻ ዓመቱ ላይ ቢሆንም ለሊቨርፑል አስፈላጊ አጥቂ መሆኑን እያሳየ ነው።

ግምት፡ 2 - 0

እሑድ

ዩናይትድ ከሌስተር

ማንቸስተር ዩናይትድ በካራባዎ ዋንጫ ሌስተርን አስተናግዶ 5-2 ረምርመዋል። ጊዜያዊው አሠልጣኝ ሩድ ቫን ኒስትልሮይ በመጀመሪያ ጨዋታ ድል ቀንቶታል። ነገር ግን ሌስተር በአብዛኛው በተቀያሪ ተጫዋቾች ነበር የገባው።

ዩናይትድ በበርካታ ግቦች ያሸንፋል ብዬ ባላስብም እንደሚያሸንፍ ግን እገምታለሁ።

የዩናይትዱ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ ባለፈው ሳምንታ ከቼልሲ ጋር በነበረው ግጥሚያ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሯል። በዚህኛውም ጨዋታ ወጥ አቋሙን ያሳየናል ብዬ እጠብቃለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ኖቲንግሀም ከኒውካስል

የኒውካስሉ አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳክ ባለፈው ሳምንት አርሰናል ላይ ግብ አስቆጥሮ ለቡድኑ 3 ነጥብ ማስገኘት ችሏል። በግንባሩ ያስቆጠረው ኳስ እንደ ክሪስ ዉድ የጭንቅላት ግቦች ዓይነት ነው።

ይህ ጨዋታ የሁለቱ አጥቂዎች ፍልሚያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ክሪስ ዉድ በዚህ ጨዋታ ልቆ ይገኛል፤ ለቡድኑም ድል ያከናንባል እላለሁ። የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ እንደሚያስቆጥር እጠብቃለሁ።

ኖቲንግሃም ጥሩ አቋም ላይ ነው። ሲከላከሉ በጋራ ነው። ግብ ከማስቆጠርም ወደኋላ አይሉም። አሁን ያሉበት የራስ መተማመን ከፍ ያለ ይመስላል።

ግምት፡ 2 - 1

ቶተንሃም ከኢፕስዊች

የስፐርሱ አሠልጣኝ አንግ ፖስቴኮግሉ አጨዋወታቸው የማደንቀው ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። ነገር ግን የምወደው ዓይነት ጨዋታ ነው የሚያሳዩን።

ኢፕስዊች ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ከመታ በኋላ የመጀመሪያ ድሉን ለማጣጣም እየተሟሟተ ነው። ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰዓት በፈፀሙት ስህተት ከሌስተር ጋር አቻ ተለያይተዋል።

ቶተንሃም በአውሮፓ ሊግ ጨዋታ ወደ ቱርክ ተጉዞ 3-2 ተሸንፎ ነው የመጣው። ቢሆንም ይህን ጨዋታ ያሸንፋል የሚል ግምት አለኝ። ኢፕስዊች ምናልባትም ወደ ታችኛው ሊግ የመመለሱ ዕድል የሰፋ ይመስላል።

ግምት፡ 3 - 1

ቼልሲ ከአርሰናል

ኮል ፓልመር ተሰልፎ ይጫወታል ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው። በአርሰናል በኩል ደግሞ የዴክለን ራይስ ነገር አልለየለትም። አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ከረዥም ጊዜ ጉዳት ስለተመለሰ ሙሉ አቋሙ ላይ ይሆናል ብዬ አላስብም።

ፓልመር ባለፈው ሳምንት ከዩናይትድ ጋር በነበረው ጨዋታ በገጠመው ጉዳት ምክንያት የልምምድ ቦታ ላይ አልታየም። ቼልሲ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ካለበት ኮል ፓልመር መሰለፍ አለበት።

ፓልመር ባይሰለፍ እንኳ አርሰናል ያሸንፋል ብዬ አልገምትም። አርሰናል ወደ ተቃራኒ ቡድን ሳጥን ውስጥ ሲገቡ ብዙ መዋሃድ አይታይባቸውም።

ግምት፡ 1-1