ወደ ሕዋ በመጓዝ የመጀመሪያዋ አካል ጉዳተኛ የሆነችው መሀንዲስ

ጀርመናዊቷ መሀንዲስ ሚቻላ ቤንቱስ

የፎቶው ባለመብት, Blue Origin

የምስሉ መግለጫ, ጀርመናዊቷ መሀንዲስ ሚቻላ ቤንቱስ

ጀርመናዊቷ መሀንዲስ ሚቻላ ቤንቱስ ወደ ሕዋ በመሄድ የመጀመሪያዋ አካል ጉዳተኛ ሆናለች።

ከሰባት ዓመት በፊት ተራራማ አካባቢ ሳይክል ስትነዳ በደረሰባት አደጋ ምክንያት የጀርባ አጥንት ሕመም ገጥሟታል።

የጠፈር ተመራማሪ የመሆን ሕልሟ ይሳካ እንደሆነ ለማወቅ ጡረተኛ የሕዋ መሀንዲስ አነጋግራም ነበር።

ዕድለኛ ሆና ብሉ ኦሪጅን የ10 ደቂቃ ጉዞ አዘጋጅቶላታል። ብሉ ኦሪጅን በጄፍ ቤዞስ የተመሠረተ የሕዋ ቱሪዝም ድርጅት ነው።

ሚቻላ እና ሌሎች አምስት ተጓዦች ከቴክሳስ በተነሳው የሕዋ መንኮራኩር ተሳፍረዋል።

የመሬትን እና የሕዋን ድንበር የሚለየው አካባቢ (the Kármán line) ደርሰውም ተመልሰዋል።

ብሉ ኦሪጅን በለቀቀው ቪድዮ ላይ "በጣም አስደናቂ ተሞክሮ ነው። ስበት አልባ ከመሆን እና ያንን ዓለም ከመመልከት በተጨማሪ ወደ ሕዋ የመጓዝ እያንዳንዱ ደቂቃ አስደሳች ነው" ብላለች።

ብሉ ኦሪጅን 'ኒው ሼፐርድ' የተባለ የሕዋ መንኮራኩሩን ከቴክሳስ አስወንጭፏል።

በአውሮፓ የሕዋ ኤጀንሲ ውስጥ የምትሠራው መሀንዲሷ ጉዳት ከደረሰባት በኋላ ዓለም እንዴት ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ እንደሆነች መገንዘቧን ትናገራለች።

ከዊልቼሯ ወደ መንኮራኩሩ ያለ ድጋፍ እንድትገባ የሚያመች መንገድ ተዘርግቶላት ነበር።

ጡረተኛው የስፔስኤክስ ኃላፊ ሀንስ ኮንግስማን ናቸው ጉዞውን ያመቻቹት።

"የተዋወቅነው በበይረ መረብነበር። ስፔስኤክስ ብዙ ዓመት ሠርተሀል፤ እንደኔ ያሉ ሰዎች ወደ ጠፈር የሚጓዙ ይመስልሀል? ብዬ ጠየቅኩት" ትላለች መሀንዲሷ።

"እሷን ስመለከት መነቃቃት አደረብኝ። ከውጭ እመለከተው የነበረውን ዓለም በቅርበት ለማየትም ወሰንኩ" ይላሉ ሀንስ ኮንግስማን።

ብሉ ኦሪጅን የመሀንዲሷን ጉዞ ምቹ ለማድረግ የአካል ጉዳተኞች መጓዣ በመንኮራኩ አቅራቢያ አሠርቷል።

የኒው ሼፐርድ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊል ጆይስ "የእሷ ጉዞ ትልቅ ትርጉም አለው። ሕዋ የሁሉም እንደሆነ ያሳያል። ሕልሟን እውን በማድረጋችን እንኮራለን" ብለዋል።

ብሉ ኦሪጅን እስካሁን 16 የሕዋ ቱሪዝም ጉዞዎች አድርጓል። መሀንዲሷ ወደ ሕዋ የተጓዘችበትን ወጪ ይፋ አላደረገም።

ከዚህ ቀደም ድምጻዊት ኬቲ ፔሪ፣ የጄፍ ቤዞስ እጮኛ ሎረን ሳንቼዝ እና የሲቢኤስ መሰናዶ አቅራቢ ጌል ኪንግ ከሌሎች ስድስት ሴቶች ጋር ወደ ሕዋ ተጉዘው 11 ደቂቃ ቆይተዋል።

የግል የሕዋ ቱሪዝም ተቋማት ገበያውን ለመቆጣጠር ፉክክራቸውን ቀጥለዋል።