ናሳ ከ50 ዓመት በኋላ ተመራማሪዎችን የያዘች መንኩራኩር ወደ ጨረቃ ሊልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, NASA
ናሳ በጨረቃ ዙሪያ ለአስር ቀን ጉዞ ለማድረግ የጠፈር ተመራማሪዎችን የካቲት ወር ላይ እንደሚልክ አስታወቀ።
የአሜሪካው የኅዋ ኤጀንሲ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ድረስ ተመራማሪዎችን ለመላክ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቀረብ አድርጎታል።
አሜሪካ ወደ ጨረቃ ተመራማሪዎቿን ከላከች 50 ዓመት አልፏታል።
ናሳ አራት የጠፈር ተመራማሪዎችን እንደሚልክ እና ስርዓቱን ለመፈተሽ እንደሚመልሳቸው አስታውቋል።
አርሚስ II ተብሎ የተሰየመው ይህ ጉዞ የአርቴሚስ ፕሮግራም የጠፈር ተመራማሪዎችን በጨረቃ ላይ ለማሳረፍ እና ለረዥም ጊዜ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ሁለተኛው ማምጠቅ ነው።
የናሳ ጊዜያዊ ምክትል አስተዳዳሪ ላኪሻ ሃውኪንስ የሰው ልጅ ኅዋን በሚያስስበት ታሪኩ ወሳኙ ቅጽበት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
"እኛ በጋራ በታሪክ ከፊት የመቀመጥ ዕድል አለን" ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።
"የማምጠቅ ስራው ከየካቲት 5 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ቢሆንም ደህነንትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባራችን መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ" ብለዋል።
የአርቴሚስ ዳይሬክተር ቻርሊ ብላክዌል ቶምፕሰን የጠፈር ተመራማሪዎቹን ጨረቃ ላይ ለማድረስ አቅም ያለው የሮኬት ስርዓት መገንባቱን አብራርተዋል።
ወደ ኅዋ የማምጠቅ ስርዓቱ "ሙሉ በሙሉ አልቆ ለመምጠቅ ዝግጁ ሆኗል" ብለዋል።
የቀረው ስራ የበረራ አባላቱን የሚይዘው እና ኦሪየን ተብሎ የሚጠራው 'ካፕሱል' ብቻ ነው።
እህ ካፕሱል ከኅዋ ማምጠቅ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ ፍተሻ ይደረግለታል ብለዋል።
እአአ በ2022 ሕዳር ወር የመጠቀችው የመጀመርያው አርቴሚስ 25 ቀናት የፈጀች ሲሆን ሰው አልባ ነበረች።
በወቅቱ የተደረገው ወደ ኅዋ በረራ በጣም ስኬታማ የነበረ ሲሆን መንኮራኩሩ ወደ መሬት ሲመለስ አካሉ የመሞቅ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር።
ይህ ደግሞ ከዚያ ወደ ጊዜ ሲስተካከል ቆይቷል።
አርቴሚስ II አራት የጠፈር ተመራማሪዎችን ይዞ በጨረቃ ዙሪያ ተሽከርክሮ ወደ ምድር ለመመለስ የ10 ቀን ቆይታ ያደርጋል።
የጠፈር ተመራማሪዎቹ ሬይድ ዋይዝማን፣ ቪክቶር ግሎቨር፣ ክርስቲና ኮች እና ከካናዳ የኅዋ ኤጀንሲ ጀርሚ ሃንሰን ናቸው።
መንኮራኩሯ ጨረቃ ላይ የምታርፍ ባይሆንም በ1972 ከመጠቀችው አፖሎ 17 ወዲህ ከመሬት ምህዋር ዝቅ ብላ የምትሽከረከር የመጀመሪያዋ መንኮራኩር ትሆናለች።
በኦፕን ዩኒቨርስቲ የኅዋ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሲሞን ባርበር ይህንን በረራ በጉጉት አንደሚጥብቁት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም "በአዲስ መንኮራኩር ወይም የኅዋ ስርዓት መብረር አስደናቂ ነው ምክንያቱም አዳዲስ እድሎችን ይከፍታል" ካሉ በኋላ "እንዲሳካ አጥብቀን እንመኛለን። እጅግ በጣም ተደንቀናል፤ ጓጉተናልም። ዳግም የሰው ልጅ ጨረቃን እንዲረግጥ ማድረግ እንፈልጋለን፤ ያ ደግሞ ሌላ አስደናቂ ነገር ነው" ብለዋል።
የኅዋ ኤጀንሲው አርቴሚስ ፕሮግራም አሜሪካ የሰው ልጅን ወደ ጨረቃ ለመመለስ የምታደርገው ጥረት አካል ነው።
ይህ ፕሮግራም ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ የሚደረግበት ሲሆን ልክ እንደ ተቀናቃኟ ቻይና እአአ በ2030 የጠፈር ተመራማሪዎችን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ አቅዳለች።
አርቴሚስ II ኤጀንሲው ተልዕኮውን ማሳካት ይችል አንደሆን የሚፈትሽበት ሲሆን፣ አርቴሚስ III ደግሞ እአአ በ2027 ስፔስኤክስ ስታርሺፕ ሮኬትን ይዞ ለመስራት ዕቅድ ተይዞለታል።
አርቴሚስ III ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ ታቅዷል።
አርቴሚስ II ናሳ ወደ ኅዋ የሚያመጥቀውን መንኮራኩር እና ኦሪዮን የተሰኘውን ካፕሱል ያካትታል።
ናሳ ወደ ጨረቃ ሰው ልኮ ማሳረፍ የቻለው ከ50 ዓመት በፊት ኒል አርምስትሮንግን ነው።
ኒል አርምስትሮንግ በአፖሎ 11 መንኮራኩር እአአ በ1969 ጨረቃን መርገጥ የቻለ የመጀመርያው የጠፈር ተመራማሪ ነው።















