በመሬት ዙሪያ ሌሎች ዓለማት እና ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ይኖራሉ? ወደ ምድር ሊመጡ ይችላሉ?

የምንኖርባት ፕላኔት፣መሬት፣ ከርቀት ስትታይ መብራቶች በርተው ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የምንኖርባት ፕላኔት፣መሬት፣ ከርቀት ስትታይ መብራቶች በርተው ይታያሉ

በደማቅ ኮከቦች የተሸለመውን የሌሊት ሰማይ ስንመለከት ራሳችንን መጠየቃችን አይቀርም።

በእርግጥ በዚህ ሰፊ አጽናፈ ዓለም ውስጥ ብቻችንን ነን?

ምናልባት ላንሆን እንችላለን። መሬት ከሰፊው ፕላኔቶች ውስጥ ትንሿ ነጥብ ናት። ታድያ እንዴት በዚህች ዓለም ላይ ብቻችንን ልንሆን ወይንም ያለ ባዕድ ጎረቤት ብቻችንን ልንኖር እንችላለን?

ስለዚህ ባለንበት ምድር በአግባቡ ቁጥጥር ከሚደረግበት ዓለም ውጪ ስላለው ሕይወት ምን እናውቃለን?

ብዙ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ባዕድ ፍጡራን መኖራቸውን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ባይኖርም እንኳ፣ እዚህ አብረውን እንዳሉ መደምደም አለብን።

የእኛ ጋላክሲ፣ ሚልክ ዌይ፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉ ከ200 ቢሊዮን ጋላክሲዎች መካከል አንዷ ናት። በዚህ ሚልክ ዌይ ውስጥ ብቻ 300 ቢሊዮን ከዋክብት ይገኛሉ።

የራሳችን ኮከብ፣ ፀሐይ፣ በምድር ላይ የሕይወት ዋነኛ ምንጭ ናት።

ሳይንቲስቶች ደግሞ በእነዚያ ከዋክብት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ፕላኔቶችን 'ኤክሶፕላኔት' ሲሉ የሚጠሯቸውን፣ ያለማቋረጥ እያገኙ ነው።

ኤክሶፕላኔት ማለት ከእኛ የፀሐይ ሥርዓት ውጪ ያለ ማለት ነው።

የጠፈር ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ማጊ አደሪን ፖኮክ እንደሚሉት የማይታወቁ አካላት "እዚያ እንዳሉ እርግጠኞች ነን።"

"የቁጥር ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር፤ የመሆን ዕድል አለው" ብለዋል።

ሦስት ሰዎች፣አንድ ትልቅ ሰው እና ሁለት ትንንሽ ልጆች ጀርባቸውን ለካሜራ ሰጥተው ተቀምጠው የሌሊቱን ሰማይ እየጠቆሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳይንቲስቶች በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ የሕይወት ምልክቶች ያላቸውን ፕላኔቶች እናገኛለን ብለው ያምናሉ

አሁን ያለን ቴክኖሎጂ እነዚህን ኤክሶፕላኔቶች በዝርዝር እንድንመረምር ያስችለናል።

የሳይንስ ሊቃውንት በከዋክብቶቻቸው ዙሪያ የሚሽከረከሩትን የሰማይ አካላት ኬሚካላዊ ይዘት ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ቴሌስኮፖችን በመጠቀም በእነሱ ውስጥ የሚያልፈውን የከዋክብት ብርሃን ኬሚካላዊ ስብጥር ለመመልከት ችለዋል። ይህ ስፔክትሮስኮፒ ይባላል።

ዋናው ነገር ከመሬት ጋር የሚመሳሰል ኬሚካላዊ ስብጥር ማግኘት ነው። ማለትም አካባቢው ሌላ ቦታም አለ። ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ የብርሃን ዓመታት ርቆ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም ከእኛ ጋር የሚመሳሰል ሕይወትን ሊቀጥል ይችላል።

ምልክቶቹ አበረታች ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት የአስትሮፊዚክስ ፕሮፌሰሩ ቲም ኦብሬን "በመቶ የሚቆጠሩ መኖሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ፕላኔቶችን እናውቃለን" ብለዋል።

"በእርግጠኝነት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ሕይወት እንዳለባቸው ማስረጃዎችን ልናገኝባቸው ወደ የምንችልባቸው ፕላኔቶች እንሄዳለን።"

የበለጠ አበረታች ማስረጃ ግን እዚህ ምድር ላይ ይገኛል።

ቀደም ሲል ሕይወት ያላቸው ነገሮች ለመኖር በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል ተብሎ በሚታሰብባቸው ቦታዎች ተገኝተዋል።

የፀሐይ ብርሃን ወይም ሙቀት በማይደረስባቸው ቦታዎች፣ ለምሳሌ በውቅያኖቻችን ጥልቅ ጉድጓዶች ውስጥ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ተገኝተዋል።

ዶ/ር ማጊ አደሪን ፖኮክ
የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ማጊ አደሪን ፖኮክ

ቀደም ባሉት ጊዜያት ሕይወት ሊኖር የሚችለው ተገቢውን ጨረር ስለሚያገኝ በአካባቢው ካለ ኮከብ የተወሰነ ርቀት ባለው ፕላኔት ላይ ብቻ ነው የሚል ግምት ነበር።

በምድር ላይ ባላሰብንበት ቦታ እየኖሩ መመልከታችን፣ ፕላኔቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ጨረቃ ላይ ጭምር ሕይወት ሊኖር ይችላል የሚለውን የአስተሳሰብ አድማሳችንን ከፍቶልናል።

ይህ ማለት ግን እንደለመድናቸው ተክሎች አረንጓዴ ይሆናሉ ማለት አይደለም።

መናገር የምንችለው እዚያ ሕይወት ሊኖር እና በሕይወት መኖር ይችላል የሚለውን ብቻ ነው።

ምንም እንኳን በሌላ ዓለም ሕይወት ያላቸው ነገሮች የመኖራቸው ዕድል ከፍ ያለ ቢሆንም፣ አሁን ግን የማሰብ፣ የማሰላሰል አቅም ያለው ፍጡር ይኖራል የሚለውን ለመናገር አዳጋች መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

"በምድር ላይ ያለው አብዛኛው የሕይወት ታሪክ በጣም ቀላል ነበር። በእርግጥ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት የባክቴሪያ ሕይወት ነበር" ብለዋል ፕሮፌሰር ኦብሪየን።

እና በፕላኔታችን ላይ ባለ ብዙ ህዋሶች ሕይወት እንዲዳብር ያደረጉ ተከታታይ ክስተቶች ነበሩ። የባዕድ ፍጡራን ከእኛ ጋር ለመገናኘት አካላዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂም የላቁ መሆን አለባቸው።

የሚመጣ ይኖራል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

እንግዲያውስ ብቻችንን ካልሆንን የሌላ ዓለም ፍጡራን ይመጣሉ ብለን መጠበቅ አለብን? ውስብስብ ነው።

በከዋክብት መካከል ርቀቶችን አቋርጦ መጓዝ ላይ የደረሰ የትኛውም ዓይነት ሕይወት ያለው ነገር የለም ብሎ ማመን ይከብዳል። ታዲያ ይህ ለምን እስካሁን አልሆነም?

ዶ/ር አደሪን ፖኮክ "ትልቁ ችግራችን ያለን አንድ የሕይወት ምሳሌ ብቻ ነው። ያ ደግሞ በዚህ ፕላኔት ላይ ያለው ሕይወት ነው" ብለዋል።

ግን ግን ይህ በዩኒቨርስ ውስጥ ለሌላ ቦታ ማንፀሪያ ንድፍ ላይሆን ይችላል።

ለምሳሌ ዶ/ር አደሪን ፖኮክ እንዳሉት፣ "በጣም ንቁ በሆነ ኮከብ ውስጥ የምትኖር ከሆነ፣ ከሚለቀቀው ጨረር ራስህን ለመከላከል ከመሬት በታች ልትኖር ትችላለህ… ይህ ማለት የማሰብ ችሎታ ያለው ሕይወት እዚያ የለም ማለት አይደለም፤ ነገር ግን የምትኖረው ከምድር በታች ስለሆነ መልዕክቶችን ለመላክ ብልሃት ላይኖርህ ይችላል።"

በሚሊዮን የብርሃን ዓመታት ከምድር ርቆ የሚታወቀው ጠመዝማዛ ጋላክሲ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወደ ሌሎች ሕይወት ወዳላቸው ነገሮች ለመላክ የምንሞክረው ማንኛውም መልዕክት ለመድረስ በሺዎች አልፎ ተርፎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት እንደሚወስድ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ

ወይም በቀላሉ በሳይንስ ረገድ ተመሳሳይ ቋንቋ አለመናገራችን ሊሆን ይችላል።

"ከ1960 ገደማ ጀምሮ ከምድር ሥልጣኔ ውጪ የሚመጡ ድምጾችን ለማዳመጥ የሬዲዮ ቴሌስኮፖችን ተጠቅመናል" ይላሉ ፕሮፌሰር ኦብሪየን።

ነገር ግን ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምልክቶችን የሚልኩባቸው ብዙ የተለያዩ መንገዶች አሉ፣ ቢሆንም ምንም ነገር መልሰን መስማት አልቻልንም።

ምንም እንኳን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉ ሌሎች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሞገድ ላይ ብንሆንም፣ ያለው ሰፊ ርቀት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እና ምላሽ ለማግኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።

እንደ ቀደመው ዘመን ደብዳቤ ብንላላክ ምን ያህል ቀርፋፋ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይበቃል።

በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው ብሬክስሩ ሊስን (Breakthrough Listen) በተሰኘው አዲስ ፕሮጀክት አማካኝነት ሳይንቲስቶች ወደ ምድር መልዕክቶችን መላክ ከሚችል ማንኛውም አካል መልዕክት ለመቀበል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የቅርብ ከዋክብትን እየፈለጉ ነው።

25 ሺህ የብርሃን ዓመታት ርቆ በሚገኘው የእኛ ሚልክ ዌይ መካከል ያሉትን ከዋክብትንም እየተመለከቱ ነው።

ይህ ማለት ከእነዚህ ከዋክብት የተላከ መልዕክት ወደ እኛ ከመድረሱ በፊት ወደ 25 ሺህ ዓመታት ገደማ መጓዝ ይኖርበታል።

ስለዚህ የሌላ ዓለም ፍጡራን እዚያ ካሉ አካላት ምንም ነገር ከመስማታችን በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

ብዙ ይቀረናል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በጋላክሲዎች መካከል የሚደረግ የጠፈር ጉዞ የሚታሰብ አይደለም።

የሬዲዮ ሞገዶችን በብርሃን ፍጥነት መላክ እንችላለን። ነገር ግን ይህ በባዶ ስፍራ መጓዝ የሚችል የሬዲዮ ሞገድ ብቻ ነው።

ማንኛውም ዓይነት የጠፈር መጓጓዣ በከዋክብት መካከል መጓዝ አይችልም።

እንደ የጠፈር ተመራማሪዎች ወይም ሌሎች ነገሮችን ወደ ህዋ ለመላክ ብንፈልግ እንኳ ከባድ ነው።

ባለሙያዎች እኛ የደረስንበት ሥልጣኔ ይህን ማድረግ ካልቻለ፣ በሌላ ዓለም የሚኖሩ ባዕድ ፍጡራንም ይህን ማድረግ አይችሉም ይላሉ።

ወደ እኛ ለመጓዝ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ቢኖራቸውም እንኳ አለመፈለጋቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።

እንዲሁም የተወሰነ መጠን ያለው የጠፈር ዕድል፣ ወይም ምቹ ጊዜ አብሮ መግጠም አለበት።

ሥልጣኔያችን በምድር ላይ ምን ያህል ለትንሽ ጊዜ እንደቆየ ማስታወስ ከባድ ሊሆን ይችላል።

መሬት ከ3.5 ቢሊዮን ዓመታት በላይ ሕይወት አስተናግዳለች። ነገር ግን ዘመናዊ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ የኖሩት በግምት ለ300 ሺህ ዓመታት ብቻ ነው።

ሥልጣኔዎች በፍጥነት ሊጠፉ ስለሚችሉ ከሌላ ዓለም ፍጡራን ጋር የመገናኘት ዕድሉ ጠባብ ነው።

የሌላ ዓለም ፍጡራን ማሳችንን፣ ጓሯችንን ጎብኝተው እንደሆን እርግጠኛ መሆን አንችልም።

ጥቂትም ቢሆን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ምናልባት ሰዎች በዚህች ፕላኔት ላይ በተንከላወሱበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ ብቅ አለማለታቸውን ነው።

ዶ/ር አደሪን ፖኮክ "ሥልጣኔዎቻችን ካልተመሳሰሉ እንግዶቻችንን በፍጹም ልናገኛቸው አንችልም" ይላሉ።

ምናልባት ከረጅም ጊዜ በፊት መጥተው ይሆናል፤ ወይም የሰው ልጅ ሕይወት ካበቃ ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደፊት ይመጣሉ።

ስለዚህ ምናልባት ዳይኖሶሮች በጁራሲክ ዘመን ውስጥ ከሌላ ዓለም ከመጡ ፍጡራን ጋር ስቀው ተጫውተው ይሆናል።

ነገር ግን አሁን በጭራሽ የምናውቀው ነገር የለም።