ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸውን እንደሚያራዝሙ እና ምርጫ እንደሚዘገይ ጠቆሙ
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክ ቴሼኬዲ፤ በአውሮፓውያኑ 2028 የሥልጣን ዘመናቸውን ሲጠናቀቅ ለሦስተኛ ጊዜ ለመሪነት መወዳደር እንደሚያስቡ ተናገሩ።
ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን የማራዘም ጉዳይ ሊሆን የሚችለው ዜጎችን በሕዝበ ውሳኔ በማማከር ብቻ እንደሚሆን ገልጸዋል። በኮንጎ ሕግ መሠረት አንድ ፕሬዝዳንት መወዳደር የሚችለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።
ቲሼኬዲ "ሦስተኛ የሥልጣን ዘመን አልጠየቅሁም። ነገር ግን እየነገርኳችሁ ነው፤ ሕዝቡ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ከፈለገኝ እቀበላለሁ" ሲሉ ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍል ባለው ግጭት ምክንያት ምርጫ በታቀደው ጊዜ ሊካሄድ እንደማይችል ጠቁመዋል። ከአገሪቱ መንግሥት ጋር የሚዋጉት የ'ኤም23' ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት ቁልፍ ከተማ የሆኑትን ጎማ እና ቡካቭን ጨምሮ በሰሜናዊ እና በደቡብ ኪቩ ክልሎች የሚገኙ ግዛቶችን ተቆጣጥረው ነበር።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ሁለቱን ክልሎች የማያካትት ድምጽ የመስጠት ሂደት ሊዘጋጅ ይችላል። የምርጫው የጊዜ ሰሌዳው ግን የሚወነሰው ግጭቱ በምን ያህል ፍጥነት ይፈታል በሚለው ላይ እንደሚሆን አክለዋል።
በ2023 ወደ ሥልጣን የመጡት ቲሼኬዲ "እንደ ዕድል ሆኖ፤ ይሄንን ጦርነት መቋጨት የማንችል ከሆነ በ2028 ምርጫ ማካሄድ አንችልም" ብለዋል።
በቤተ መንግሥት በተካሄደው ለሦስት ሰዓታት የቆየ ዝግጅት ላይ ከ200 በላይ ጋዜጠኞች እና ደጋፊዎቻቸው ተገኝተዋል።
የኮንጎ መንግሥት፤ በሩዋንዳ እንደሚደገፍ ከሚታመነው ኤም23 ታጣቂ ቡድን እንዲሁም በምሥራቃዊ ኮንጎ ከሚገኙ ሌሎች አማጺ ቡድኖች ጋር ለዓመታት ሲዋጋ ቆይቷል።
ሩዋንዳ ኤም23ን እንደምትደግፍ የሚያሳዩ በርካታ መስረጃዎች ቢኖሩም እገዛ ማድረጓን አስተባብላለች። ክልሉ ወታደሮቿ ያሉት ኮንጎ ውስጥ ባሉ ታጣቂ ቡድኖች ለተደቀነባት ስጋት የመከላከያ እርምጃ ለመውሰድ መሆኑን ትናገራለች።
ፕሬዝዳንቱ በረዕቡ ዕለት ንግግራቸው፤ ሥልጣን ከመልቀቃቸው በፊት ቅድሚያ ሰጥተው የሚያከናውኑት ተግባር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰላምን መመለስ እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም ግን የሰላም ሂደቱን እያደናቀፈች ነው ያሏትን ሩዋንዳን ወቅሰዋል።
ሩዋንዳ በዴሞክራቲክ ኮንጎ የማዕድን ሀብት ትርፍ እያጋበሰች እንዲሁም ባለፈው ታኅሣሥ ላይ የተፈረመው ስምምነት ትግበራን እያጓተተች ነው ሲሉ ከስሰዋል።
ቲሼኬዲ አሜሪካ ታጣቂ ቡድኖችን ይደግፋል በሚል በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ ስለጣለችው ማዕቀብም አንስተዋል።
ሁኔታውን "እጅግ የተበላሸ" ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በአንድ ወቅት የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ቀያሾች ተብለው የተወደሱ ሰዎች "መቃብር ቆፋሪዎች" ሆነዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለተጨማሪ ጊዜ ሥልጣን ላይ ስለመቆየት የተናገሩት ተቃዋሚዎች እና ሌሎች በቡድኖች ከሁለት ጊዜ በላይ በመሪነት ለመቀጠል እያሰቡ ነው የሚል ክስ በቅርቡ ካሰሙ በኋላ ነው።
ባለፈው መጋቢት ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀርቧል። ደጋፊዎች የሕዝበ ውሳኔ ረቂቅ ሕጉ ዴሞክራሲን እንደሚያጠናክር እርምጃ አድርገው ያቀርቡታል።
ተቃዋሚዎች ግን የፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን ላይ የተቀመጠውን ገደብ ለማሻሻል የተደረገ የተሰላ እርምጃ ሲሉ ተችተውታል።