ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት "ያለ ቅድመ ሁኔታ" ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
የፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ በሚል ውድቅ ባደረገው ምርጫ የተመረጠውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ የመለሰው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ "ያለ ቅድመ ሁኔታ" ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።
"ለሰላማዊ እና በድርድር ለሚመጣ መፍትሔ" ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።
ህወሓት፤ ከፌደራል መንግሥት የቀረበውን "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሱዳን መንግሥት እየተባበረ ነው" የሚል ክስ "መሠረት የለሽ" በማለት ውድቅ አድርጓል።
ህወሓት ይህንን ያለው ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 28/2018 ዓ. ም. "ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ" ለመስጠት ባወጣው መግለጫ ነው።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ግዛት የተነሳ ድሮን በዋና ከተማዋ ኻርቱም የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዳጠቃ በመግለጽ ላቀረበችው ክስ ማክሰኞ ዕለት ምላሽ የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የአገሪቱ ጦር "የህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎችን እየተጠቀመ ነው" በሚል ወንጅሎ ነበር።
በሱዳን ጦርነት ውስጥ "የህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በስፋት የመጠቀም" ድርጊት መታየቱን የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ "የሱዳን ጦር ለእነዚህ ቅጥረኛ ተዋጊዎች የመሣሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ አቅርቧል" ብሎ ነበር።
የሱዳን ጦር ባደረገው ድጋፍ እነዚህ ኃይሎች "በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ድንበር በኩል የሚያደርጉትን ወረራ አመቻችቷል" ሲል ከስሷል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሱዳን መንግሥት ጋር እየተባበረ ነው" በሚል የቀረበበትን ክስ "በፍጹም እንደማይቀበል" አስታውቋል።
"[ክሶቹ] መሠረት የሌላቸው፣ ኃላፊነት የጎደላቸው እና በሐሰተኛ መረጃ ትኩረትን ለማስቀየር ተደጋግሞ የሚታይ አካሄድ ነጸብራቅ ናቸው" ብሏል።
"ህወሓት ቀጣናዊ መረጋጋትን በሚያናጉ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ አልተሳተፈም፤ ወይም አልደገፈም" ሲልም ራሱን ተከላክሏል።
ሱዳን በትግራይ ጦርነት ወቅት ለተፈናቀሉ ሰዎች "ሰብዓዊ እርዳታ እና መጠጊያ" መስጠቷን አስታውሶም፤ "ይህ ሰብአዊ ድርጊት ለተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ትርክቶች እንዲያገለግል ለራስ ጥቅም ሲባል መጣመም የለበትም" ብሏል።
ከውጥረት "መታቀብ እና ገንቢ ግንኙነት" በቀጣናው አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ እንዲህ ዓይነት ክሶች "ውጥረትን እንደሚያቀጣጥሉ እንዲሁም ለተጠያቂት እና ለእውነተኛ የሰላም ጥረቶች ያለውን አስቸኳይ ፍላጎት እንደሚጋርዱ" ገልጿል።
ህወሓት በመግለጫው የሁለት ዓመቱን የትግራይ ጦርነት ስላስቆመው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት አንስቷል።
የትግራይ ሕዝብ "የተፈናቀሉ ዜጎች በደኅነት፣ በፈቃደኝነት እና በክብር ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ" ማድረግን ጨምሮ ስምምነቱ "በሙሉ እና በታማኝነት እንዲተገበር በትዕግስት ሲጠብቅ" መቆየቱን ገልጿል።
"በምዕራብ ትግራይ የሚገኙትን ጨምሮ ኃይሎቻችን፤ [የተፈናቃዮች] መመለስ በሰላማዊ፣ ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲካሄድ ለማድረግ ቁርጠኛ ናቸው" ብሏል።
ህወሓት አሁንም "ለሰላማዊ እና በድርድር ለሚመጣ መፍትሔ" ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። ህወሓት ይህንን ያለው የፕሪቶሪያ ስምምነት "በፌደራል መንግሥት ፈርሷል" የሚል ክስ አቅርቦ፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ውድቅ ሆኖ የቆየው የትግራይ ክልል ምክር ቤት እንዲመለስ ባደረገ ማግሥት ነው።
ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና ፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ ባለው ምርጫ የተቋቋመው ምክር ቤት ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን ባደረገው ስብሰባ፤ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነት ሾሟል።
በክልሉ አዲስ ርዕሰ መስተዳደር የተሾመው የፌደራል መንግሥት በዚህ ወር መጀመሪያ ለአንድ ዓመት ሥልጣናቸውን ያራዘመላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በመሪነት ሥፍራቸው እንዳሉ ነው። ይህንን እርምጃ በተለከተ እስካሁን ከፌደራል መንግሥት በኩል ምላሽ አልተሰጠም።
የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ እያካሄደ በነበረበት ዕለት ግን ተዋጊ ጄት በመቀለ ከተማ ሲበርር መታየቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ህወሓት በትናንቱ መግለጫው "ለመሸከም ከባድ የሆኑ ተግዳሮቶች ቢቀጥሉም፤ ለሰላማዊ እና በድርድር ለሚመጣ መፍትሔ ያለን ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ነው" ብሏል።
"ለሰላም፣ ለመረጋጋት እና ለገንቢ ግንኙነት ያለንን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በግልጽ በድጋሚ እናረጋግጣለን" ሲልም አክሏል። "ያለ ቅድመ ሁኔታ ለሚደረግ" ድርድር ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።
"ዘላቂ እና ፍትሐዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሚካሄድ፣ ተዓማኒ፣ አካታች እና ውጤት ተኮር የንግግር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን" ሲል አቋሙን ገልጿል።