ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ያገደችው አውስትራሊያ በግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጫና ውሳኔዋን እንደማትቀይር ገለጸች

አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ማገዷን ተከትሎ ከግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለሚደርስባት ጫና እንደማትበገር አስታወቀች።
ስናፕቻት፣ ሜታ፣ ቲክቶን እና ዩቲዩብን ጨምሮ 10 የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እአአ ከታኅሣሥ 10/2025 አንስቶ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአውስትራሊያ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር አኒካ ዌልስ "የቆምነው ለወላጆች ነው እንጂ ለግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አይደለም" ብለዋል።
የፌስቡክ አስተዳዳሪ ሜታ፤ የታዳጊዎችን የበይነ መረብ ደኅንነት መጠበቅ መልካም ቢሆንም፤ እገዳ መጣል መፍትሔ እንደማያመጣ ገልጿል።
አንዳንድ ባለሙያዎችም የእገዳው ውጤታማነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
የአውስትራሊያ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ግን፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እያደረሱ ስላለው ጉዳት ከተገለጸላቸው በኋላ አሠራራቸውን ለማረም ከ15 እስከ 20 ዓመታት ቢሰጣቸውም ለውጥ አለማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።
"የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን አልፈራቸውም። ውሳኔያችን የሞራል ሚዛንን የጠበቀ ነው" ብለዋል።
ልጆቻቸው ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ የሚሹ ወላጆች የሰጧቸው ማበረታቻ በአቋማቸው እንዲጸኑ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
የመንግሥታቸው ውሳኔ ብዙ አገራትን "እንዳስቀና" ጠቅሰው፤ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ለሚፈልጉ አገራት ተሞክሯቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"የመጀመሪያው አገር በመሆናችን ደስተኛ ነን። ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፍ የሚፈልጉ አገራትን ማገዝም እንፈልጋለን" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸውን የቴክኖሎጂ ተቋማት የሚጎዳ አገርን እንደማይታገሱ ገልጸዋል።
አውስትራሊያ በማኅበራዊ ሚዲያ የጣለችውን እገዳ ያረቀቀው ተቋም ኮሚሽነር፤ በአሜሪካ ምክር ቤት ተገኝተው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቋል።
አሜሪካ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት ብትችልም አውስትራሊያ ግን "ግቧን ከማሳካት እንደማትዘናጋ" ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
"ኃላፊነታችን ለአውስትራሊያውያን ግብር ከፋዮች ነው። ለሕዝብ ፖሊሲ የምናወጣው እነሱ በሚከፍሉት ገንዘብ ነው" ብለዋል።
አውስትራሊያ እርምጃውን በመውሰድ ቀዳሚ አገር በመሆኗ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት እገዳው ሊያስፈራቸው እንደሚችል እንደሚገነዘቡም አልሸሸጉም።
"ደኅንነቱ ያልተጠበቀ መተግበሪያ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ከሆነ ሕዝቡም እርምጃ እንድንወስድ ይጠብቃል" ሲሉም አክለዋል።
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጠንካራ የወላጆች ቁጥጥር መተግበር ወይም ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ ትምህርት መስጠት የተሻለ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።
የአውስትራሊያ ሕግ በይዘት ከዓለም ቀዳሚው ቢሆንም፤ ተቀራራቢ ፖሊሲዎችን ለመተግበር የሞከሩ አገራት አሉ።
እነዚህ አገራት እምብዛም ስኬታማ እንዳልሆኑ በመጥቀስ አውስትራሊያም መሰናክሎች ሊገጥሟት እንደሚችሉ የገለጹ ተንታኞችም አሉ።
የተወሰኑ የአሜሪካ ግዛቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እገዳ ለመጣል ያቀረቧቸው ረቂቆች በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርገዋል።
ባለፈው ሳምንት ሁለት አውስትራሊያውያን ታዳጊዎች አዲሱን ሕግ የልጆችን መብት ይጥሳል ብለው በከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ከፍተዋል።
አውስትራሊያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እገዳ ስትጥል የጌም መጫወቻ መተግበሪያዎችን ችላ ማለቷ አስተችቷታል።
የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሯ "እንደ ሮብሎክስ ያሉ ጌሞችን ጉዳይም እየተመለከትን ነው። ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እርምጃዎች ይወሰዳሉ" ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት የአገሪቱ መንግሥት እገዳው ላይ ግምገማ ያደርጋል።
"ችግሩን በአጠቃላይ የሚፈታ ዕቅድ አይደለም። ጊዜያዊ ማስታገሻ ነው። የሚሠራውን እና የማይሠራውን እያየን ማሻሻያ እናደርጋለን" ሲለም ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
እገዳው ሲተገበር መደነቃቀፍ መፈጠሩ ባይቀርም፤ በጊዜ ሒደት ማኅበራዊ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ያምናሉ።
"ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች መጠጣት ባይፈቀድላቸውም አንዳንዶች ሕጉን ጥሰው ይጠጣሉ። ቤተሰቦቻቸው የሚያበረታቷቸውም አሉ። ይሄ ማለት ግን ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች መጠጥ እንዲጠጡ መፍቀድ አለብን ማለት አይለም" ሲሉም በምሳሌ አስረድተዋል።
ሦስት ልጆቻቸው ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን የቆይታ ጊዜ እንዲሁም የሚጠቀሟቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንደሚከታተሉ ሚኒስትሯ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
"ሕግ አውጪ እንደመሆኔ ውሳኔዬ ለእኔም ልጆች ይሆናል። አልጎሪዝሙን መቆጣጠር ስለማይቻል እገዳው አስፈላጊ ነው። በርካታ ወላጆችም አመስግነውኛል።"















