ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እሁድ ዕለት በጎንደር ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ለወራት የዘለቀው በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ግጭት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ቢቢሲ ከተለያዩ ስፍራዎች የሚያገኛቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ትናንት እሁድ መስከረም 13/2016 ዓ.ም. በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ መዋሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተለይ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙት ማራኪ፣ ልደታ እና ቀበሌ 18 ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ተኩስ እንደነበር ተናግረዋል።
ለደኅንነቱ ሲል ስሙን እንዳንጠቅሰው የጠየቀን የከተማዋ አንድ ነዋሪ “ግጭቱ የተፈጠረው ፋኖ ሁለት እስር ቤቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞችን ማስለቀቁን ተከትሎ ነው” ብሏል።
ነዋሪው አክሎም በፖሊስ ጣቢያዎቹ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ፣ በከተማዋ አብዛኛው አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
በጎንደር አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ የሚናገረው ቴዎድሮስ የተባለው የፋኖ ቡድን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሆነ የገለጸ የቡድኑ አባል “ጥቃት የከፈትነው ጎንደር ከተማ ውስጥ በፈለግነው ሰዓት መግባት እንደምንችል ለማሳየት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሰሩ አባሎቻችንን ለማስፈታት ነው” ብሏል።
ጨምሮም እሁድ ዕለት በነበረው ግጭት ሦስተኛ እና ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተያዙ እስረኞችን ማስለቀቃቸውን ገልጿል።
ነገር ግን የአገር መከላከያ ሠራዊት ክስተቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የፋኖ ታጣቂ በጎንደር ከተማ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮ ከ50 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና ታጣቂዎቹን ከከተማ ማባረሩን ገልጿል።
የቡድኑ ተወካይ ግን የተጠቀሰው ቁጥር “ሐሰት” መሆኑን በመግለጽ፣ በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በማስለቀቅ የመከላከያ ሠራዊቱ እና ንብረቶቹ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጾ፣ ነገር ግን “ይህንን ሁሉ ስንፈጽም ያለመስዋዕትነት አይደለም፣ የተጠቀሰው ቁጥር እጅግ የተገጋነነ ነው” ብሏል።
የመከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ በስም የጠቀሳቸው የፋኖ አመራሮች መገደላቸውን የገለጸ ቢሆንም፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የተባሉት የቡድኑ አባላት ያልተገደሉ መሆናቸውን እና በቅርቡም ራሳቸው መረጃ እንደሚሰጡ ገልጿል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ሌላኛው ነዋሪ እሁድ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱ “ጠዋት አካባቢ ከማራኪ ጀምሮ እስከ ፒያሳ ድረስ የፋኖ ታጣቂዎች ተቆጣጥረውት የነበረ ቢሆንም፣ ከሰዓት በኋላ መከላከያ ሠራዊት ኃይሉን በመጨመር የፋኖ ታጣቂዎችን ከአብዛኛው የከተማዋ አካባቢዎች አስወጥቷቸዋል” ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ወደ ከተማዋ ዘልቆ የገባው የፋኖ ታጣቂ በሸማቾች ሕብረት ሥራ ላይ ዘረፋ መፈጸሙን ገልጿል።
የፋኖ የሕዝብ ግንኙነት ግን ክሱን አይቀበለውም። “ከተማዋን ለስድስት ቀናት ተቆጣጥረን በነበረበት ወቅት ምንም ነገር አልነካንም። አሁንም ባንኮችን ሳይቀር ተቆጣጥረን በነበረበት ወቅት ሸማቾች ጋር ልንዘርፍ አንችልም” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ሁለቱ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ተኩስ ስለነበረ ዝርፊያውን ለማጣራት ዕድል እንዳላገኙ የገለጹ ሲሆን፣ ከተማዋን ለቀናት ሲንጣት የነበረው የከባድ መሣሪያ ተኩስ ግን በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በከተማው የነበረውን ግጭት ተከትሎ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ቢሄዱም፣ በመከላከያ ሰራዊት ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን እና ሕክምናቸው መቋረጡን ይናገራሉ።
ወንድማቸው በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ሆስፒታል እንደነበረ ለቢቢሲ የሚገልጹ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ “በመከላከያ ሠራዊ አባላት አምስት ቁስለኞች ከሆስፒታል መወሰዳቸውን” እና ከእነዚህ መካከል አንደኛው የእርሳቸው ወንድም መሆኑንም ገልጸዋል።
ወንድማቸው በጫማ ማስዋብ ሥራ የሚተዳደር እና የ24 ዓመት ወጣት መሆኑንም ገልጸዋል። ነገር ግን እሁድ ዕለት በነበረው ግጭት ጉልበቱን በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ሆስፒታል እንደወሰዱት እና የቀዶ ሕክምና እያደረገ በነበረበት ወቅት ሕክምናውን አቋርጠው እንደወሰዱት ተናግረዋል።
ቢቢሲ በግጭቱ በሰዎች ላይ የደረሰን ጉዳት እና ተወሰዱ የተባሉ ቁስለኞችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ከሆስፒታሉ ለማግኘት ቢሞክርም ለጊዜው አልተሳካም።
ዛሬ ሰኞ እስከ እኩለ ቀን ድረስ በጎንደር ከተማ ውስጥ ምንም አይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ የሰው እንቅስቃሴ ቢኖርም የመንግሥት ተቋማት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራቸውን ማቆማቸውም ተነግሯል።
ነዋሪዎቹ በከተማዋ ዳርቻዎች እስከ ሰኞ ጠዋት ድረስ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ የቴዎድሮስ ብርጌድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውም በከተማው የተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም የፋኖ ታጣቂዎች መኖራቸውን አረጋግጧል።
ከጎንደር በተጨማሪ በማክሰኝት እና ቆላድባ ከተሞችም ተኩስ መኖሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል። በዚህ ሳቢያም ከጎንደር ወደ ባሕር ዳር በሚወስደው መንገድ ትራንስፖርት መቋረጡን ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ የተባባሰው በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ እየተነገረ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ ከተደነገገ በኋላ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት በአማራ ክልል ውስጥ የተሰማራ ሲሆን፣ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶች የተነሳ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።