ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ እና ሶማሌ አወሳኝ ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መስፋፋቱ ተገለጸ
በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች የወሰኑ ቦታዎች ላይ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች መስፋፋቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታወቀ።
በሽታው በተስፋፋባቸው 10 ወረዳዎች አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በከፍተኛ የአደጋ ስጋት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
አስከ ሰኞ ጥር 22/2015 ዓ.ም. ድረስ 1,055 በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም 28 ሰዎች ሞተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኮሌራ ወረርሽኙ በኦሮሚያ ክልል በባሌ፣ በጉጂ እና በምዕራብ አርሲ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 8 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 66 ቀበሌዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን በሁለት ወረዳዎች ውስጥ ተስፋፍቷል።
በዚህም ሳቢያ ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ30 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ባሌ ዞን የተቀሰቀሰው ወረርሽኝም አዋሳኝ ወደሆኑት ምዕራብ አርሲ፣ ጉጂ እና ወደ ሶማሌ ሊበን ዞኖች ተስፋፍቷል።
የመጀመሪያው በኮሌራ የተያዘ ሰው ሪፖርት የተደረገው ባለፈው ዓመት ነሐሴ መጨረሻ ላይ ባሌ ዞን ውስጥ ነበር። አስካሁንም ድረስ በዞኑ ካሉ 13 ወረዳዎች ስድስቱ ውስጥ በሽታው መገኘቱን መረጋገጡ ተገልጿል።
የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ከሁለት ሳምንት በፊት በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልልሎች በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ መከላከያ ጠብታ ክትባት መስጠት ዘመቻ ተጀምሯል።
ኦቻ እናዳለው በአሁኑ ወቅት አጠቃላዩ የኮሌራ በሽታ ክስተት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፤ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአዳዲስ አካባቢዎችም ወረርሽኙ ተመዝግቧል።
በበሽታው ምክንያትም ያጋጠመው ሞት ከ0 አስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ላይ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል 25 በመቶዎቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ናቸው።
ይህ የኮሌራ ወረርሽኝ ወደ ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል እንዳይስፋፋ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሪፖርት አመልክቶ፣ ስለበሽታው አንዳንድ ያልተረጋገጡ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎም የፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደ ቤንች ማጂ ዞን ሸኮ ወረዳ እና ወደ ኮንታ ልዩ ወረዳ ተሰማርቶ ምርመራ እየተደረገ ነው።
በተጨማሪም የኮሌራው ወረርሽኝ በሰሜናዊ ኬንያ ማርሳቢት ግዛት ውስጥ መገኘቱ እየጨመረ መሆኑ በመረጋገጡ ወደ ኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን ሊስፋፋ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ኮሌራ ምንድን ነው? የኮሌራ በሽታ የሚተላለፈው ኮሌራ ቪብሮ ኮሌሬ በተባለ ባክቴሪያ ሲሆን፣ የተበከሉ ምግቦች እና መጠጦች አማካይነት የሚከሰት ነው።
የንጽህና ጉድለት ዋነኛው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ነው። በተለይ በባክቴሪያው የተጠቃ ሰው ዐይነ ምድር፣ ምግብን እና ውሃን በቀላሉ ይበክላል።
ባክቴሪያው ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ አስፈላጊው ሕክምና በአስቸኳይ ካልተደረገ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከትን በማስከተል፤ ከፍተኛ ፈሳሽን ከሰውነታችን እንዲወጣ በማድረግ እስከ ሞት የሚያደርስ በሽታ ነው።
ምልክቶቹ፡ አብዛኞቹ በኮሌራ ባክቴሪያ የተጠቁ ሰዎች የበሽታው ምልክቶች ላይታይባቸው ይችላል። ሌሎቹ ግን አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ያጋጥማቸዋል።
በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰውነት ፈሳሽ ስለሚወጣ ክፉኛ ይዳከማሉ። በተጨማሪም ክንድና እግሮች ላይ ሕመም እንዲሁም የሆድ ቁርጠት ያጋጥማል።
በሽታው በተለይ ህጻናት ላይ የሚበረታ ሲሆን በአስቸኳይ ህክምና እንዲያገኙ ካልተደረገ በቀላሉ ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል።