ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቨርፑል ከዩናይትድ፣ ሲቲ ከኒውካስል፤ የፕሪሚየር ሊግ ግምቶች
የሳምንቱ የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ሊቨርፑልን ከዩናይትድ፣ ሲቲን ከኒውካስል እንዲሁም መሪዎቹ መድፈኞችን ከበርንዝማውዝ ያገናኛል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ የጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከለተው አስቀምጧል።
ክሪስ ሱቶን ስለ ሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ሲናገር፤ ማንችስተር ዩናይትድ አንፊልድ ላይ ሊቨርፑልን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው እአአ 2016 መሆኑን ያስታወሳል።
በዚህ የውድድር ዘመን ችግር ውስጥ ያሉት ሊቨርፑሎች በደጋፊያቸው ፊት ሊሸነፉ ይችላሉ ሲልም ግምቱን አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ማንችስተር ሲቲ ከ ኒውካስል ዩናይትድ
የ26ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ ከሰዓት 9፡30 ሲል ማንችስተር ሲቲን ከ ኒውካስል ያገናኛል።
ሱቶን ኒውካስሎች የተቀዛቀዙ ቢመስሉም በኢትሃድ ሲቲን ሊፈትኑ ይችላሉ ይላል። ኒክ ፖፕን ወደ ሜዳ ይዞ የሚገባው ኒውካስል በሲቲ ላይ ጎል ቢያስቆጥርም ሽንፈት ግን አይቀርለትም ይላል።
ግምት፡ ሲቲ 3 - 1 ኒውካስል
አርሰናል ከ በርንዝማውዝ
ቅዳሜ 12 ሰዓት ሲል አምስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይጀምራሉ። ከእነዚህ መካከል የሊጉ መሪ አርሰናል ከበርንዝማውዝ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
አርሰናል በሲቲ ከተሸነፈ በኋላ የነበሩትን ሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በርንዝማውዝ ሁሌም ጠንካራ ተፎካካፊ ሆነው ለመቅረብ ቢጥሩም በዚህ ጨዋታ የሚሰምርላቸው አይመስለኝም ይላል ሱቶን።
ስለዚህም መድፈኞች እያሳዩት ካሉት ድንቅ ጨዋታ አንጻር ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
ግምት፡ አርሰናል 3 - 0 በርንዝማውዝ
አስተን ቪላ ከ ክርስታል ፓላስ
ፓላስ በ2023 ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። ነገር ግን በዚህ ዓመት አቻ መውጣትን ተክኖበታል። ከዚህ ቀደም ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስቱን አቻ ተለያይተዋል። በዚህ ጨዋታ ተሻሽለው ይቀርባሉ የሚል ግምት ሱቶን የለውም።
በአንጻሩ ቪላ የሚዋዥቅ ውጤት ሲያስመዘግብ ቆይቷል። “ቪላዎች በኡናይ ኤምሪ ስር ሆነው ለውጥ እያመጡ እንደሆነ ይሰማኛል” የሚለው ሱቶን ይህን ጨዋታ ባለሜዳዎቹ እንደሚያሸንፉ ግምቱን አስቀምጧል።
ግምት፡ ቪላ 2 - 0 ፓላስ
ብራይተን ከ ዌስት ሃም
ማራኪ ጨዋታ ሊታይበት የሚችለው ግጥሚያ በተመሳሳይ ሰዓት ቅዳሜ 12 ሰዓት ይጀምራል። ዌስት ሃም ባለፈው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ፎረስት ላይ 4 ግቦችን አስቆሮ ማሸነፉ መነቃቃትን ፈጥሮለታል።
ይሁን እንጂ ዌስት ሃም ድንቅ ጨዋታ የሚጫወቱትን እና የማይዋዥቅ አቋም የሚያሳዩትን ብራይተንን ማሸነፍ አይቻላቸውም ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ብራይተን 2 - 1 ዌስት ሃም
ቼልሲ ከ ሊድስ
“እውነት ለመናገር ምን አይነት ውጤት መገመት እንዳለብኝ ከማላውቃቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ ይህ ነው” ይላል ሱቶን።
እውነት ነው ቼልሲ ማሸነፍ አለበት። ግን ግን በዚህ ዓመት ሪያል ማድሪድ በእንግሊዝ ከቼልሲ በላይ ጎል አስቆጥሯል የሚለው ስታቲስቲክስ መስማት ለጆሮ እንደሚከብደው ሁሉ የለንደኑ ክለብ ይህን ጨዋታ ስለማሸነፉም አጠራጣሪ ነው።
ይህን ጨዋታ ማንም ያሸንፍ ማን፤ ጨዋታው በጠባብ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።
ግምት፡ ቼልሲ 1 - 0 ሊድስ
ዎልቭስ ከ ቶተነሃም
ሌላው አቋም የለሽ ክለብ ቶተነሃም ነው። የቶተነሃም ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው።
በኤፍ ኤ ካፕ በሼፊልድ ከተሸነፉ በኋላ በሞለኒዩ ያሸንፋሉ ብዬ አልገምትም። ዎልቭስም ቢሆን ተመሳሳይ ነው።
ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚታገለው ቡድን አጨዋወጥ ማጥቃት ላይ የተመሠረት አደለም።
ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 1 ቶተነሃም
ሳውዝሃምፕተን ከ ሌስተር
የሳውዝሃምፕተን እና የሌስተር ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት 2፡30 ላይ ይጀምራል።
ሁለቱም ክለቦች በሳምንቱ አጋማሽ በኤፍ ኤ ካፕ ውድድሮች ያልተጠበቀ ሸንፈትን አስተናግደዋል። ከታችኛው ዲቪዥን በመጡ ክለቦች በሜዳ እና በደጋፊው ፊት ተሸንፏል።
ሁለቱም ቡድኖች ማሸነፍ ግድ ቢላቸውም ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ሳውዝሃምፕተን 1 - 1 ሌስተር
እሁድ
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ኤቨርተን
ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ ነው። ኖቲንግሃም ሦስት ነጥብ ካገኘ ከወራጅ ቀጠና ርቆ እንዲቀመጥ ያስችለዋል። እነዚህ ሦስቱ ነጥቦች ኤቨርተንን ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ማውጣት ይችላሉ።
ኤቨርተን ምንም ያህል ሦስቱን ነጥብ ቢፈልግ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የሚሳካለት አይሆንም።
ፎረስቶች በሜዳቸው በቀላሉ የሚቀመሱ አይደሉም። ለማንችስተር ሲቲም እንደማይመለሱ በቅርቡ አሳይተዋል። ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳቸው የተሸነፉት መስከረም ላይ ነው።
ግምት፡ ኖቲንግሃም ፎረስ 1 - 1 ኤቨርተን
ሊቨርፑል ከ ማንችስተር ዩናይትድ
የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ እሁድ ምሽት 1፡30 ሲል ይጀምራል።
ዩናይትድ በኤፍ ኤ ካፕ በዌስትሃም ሲፈተን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ካዜሚሮን እና ራሽፎርድን ቀይረው ካስገቡ በኋላ ጨዋታውን ተቆጣጥረው አሸንፈው ወጥተዋል።
በዩናይትድ እና በሊቨርፑል መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ዩናይትድ ጨዋታ መቀየር ይችላል። ሊቨርፑል ግን በተለያዩ ምክንያቶች በውድድር ዘመኑ በሙሉ ለውጥ ማምጣት አልቻለም።
በእሁዱ ጨዋታ ዩናይትድ የመሃል ሜዳውን በመቆጣጠር አጥቅቶ ተጫውቶ የበላይነትን ይዞ ይወጣል።
ግምት፡ ሊቨርፑል 1 - 2 ማንችስተር ዩናይትድ
በሬንትፎርድ ከ ፉልሃም
የ26ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሳረጊያ ብሬንትፎርድ ከፉልሃም የሚያደርጉት ነው።
እነዚህ ሁለቱም ቡድኖች ከሊጉ ሰንጠረዥ በላይ የሆኑት በምክንያት ነው። ከየትኛውም ቡድን ጋር ቢገናኙ እጅ አይሰጡም፤ አጥቅተው ይጫወታሉ።
ከወራት በፊት በነበረው ጨዋታ ፉልሃም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል አስቆጥሮ ሙሉ ነጥብ ወስዶ ነበር። በዚህ ጨዋታ ግን ባለሜዳዎቹ በጠባብ ሜዳ ያሸንፋሉ ብዬ ጠብቃለሁ።
ግምት፡ ሬንትፎርድ 2 - 1 ፉልሃም