ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኬ መርከብ በሁቲዎች ሚሳኤል መመታቷን የአሜሪካ ጦር አስታወቀ
ንብረትነቱ የዩናይትድ ኪንግደም የሆነች የዕቃ መጫኛ መርከብ በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ በየመን ሁቲዎች ሚሳኤሎች ተመታች።
ሁለት ሚሳኤሎች የተወነጨፈባት መርከቧ መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባትም የአሜሪካ ጦር አስታውቋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በየመን ደቡባዊ ምስራቅ በምትገኘው የወደቧ ከተማ ኤደን ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የባህር ኃይል ባለስልጣናት የተወነጨፉት ሚሳኤሎች በመርከቧ ላይ የእሳት ቃጠሎ እንዳስከተለባትም ተናግረዋል።
የሁቲ ቃለ አቀባይ መርከቧን ዒላማ ማድረጋቸውን አረጋግጠው የአሜሪካ የጦር መርከብንም በድሮን መምታታቸውን አክለዋል።
በኢራን የሚደገፉት እና አብዛኛውን የሰሜን ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ከህዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባህር የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን እያጠቁ ይገኛሉ።
ባለፉት ጥቂትወራት ውስጥም የንግድ መርከቦችም ላይ ሮኬቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት ፈጽመዋል።
የሁቲ አማጽያን እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እርዳታ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እንዲሁም እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለውንም የማያባራ ጥቃት እንድታቆም ጠይቀዋል።
ጥቃታቸው ያነጣጠረው ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች ላይ ነው ቢሉም ይህ ሲሆን አይታይም።
የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም የጦር መርከቦች የባህር ላይ ቅኝቶችን እንዲሁም የባህር ላይ የንግድ ትራንስፖርት ጥበቃ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ግብረ ኃይልነት ተሰማርተዋል።
እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም የጦር አውሮፕላኖች የሚደገፈው የአሜሪካ ጦር ከጥር ወር ጀምሮ በየመን የሁቲ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ።
የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ ሐሙስ ከሌሊቱ 10፡30-11፡30 ባለው ወቅት የአሜሪካ ኃይል እና የጥምር ጦር መርከብ ስድስት የሁቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) በቀይ ባህር ላይ መምታታቸውን አስታውቋል።
ከሰዓታት በኋላም ሁቲዎች ከደቡብ የመን ሁለት ባሌስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ኤደን ባህረ ሰላጤ መተኮሳቸውንም አክሏል።
መርከቧ ቀለል ያለ ጉዳት ቢደርስባትም ጉዞዋን መቀጠሏ ተነግሯል።
ቀደም ሲል የዩናይትድ ኪንግደም የባህር ንግድ ኦፕሬሽን ኤጀንሲ ከኤደን በስተደቡብ ምስራቅ 130 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሁለት ሚሳኤሎች አንዲት መርከብ እንደመቱ እና እሳትም መነሳቱን አስታውቋል።
ኤጀንሲው ስሟን ይፋ ያላደረጋት መርከብም ጉዞዋን መቀጠሏን እና ሰራተኞቹም ደህና መሆናቸውን ገልጿል።