ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች በጥቅምት እና በኅዳር በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች እና በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከጥቅምት ወር መጨረሻ አንስቶ በክልሎቹ ውስጥ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በተመለከተ የደረሱትን ጥቆማዎች እና አቤቱታዎችን መሠረት አድርጎ ባደረገው ክትትል፣ በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸሙት ጥቃቶች ሳብያ መጠነ ሰፊ እና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።
በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ ዞን እና በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን እና በቄለም ወለጋ ዞን እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ውስጥ፣ በተፈጸሙት ጥቃቶች በቁጥር የተጠቀሱ ከ50 በላይ ሲቪሎች መገደላቸው ተገልጿል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “…እየደረሰ ያለው እጅግ አሠቃቂ ጉዳት የበለጠ ከመባባሱ እና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግሥት ተገቢውን ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ” ጥሪ አቅርበዋል።
የኢሰመኮ መግለጫ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በዝርዝር ያወጣ ሲሆን በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶች ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት መድረሱን ቢያመለክትም የሞቱ ሰዎችን አሃዝ ግን አልገለጸም።
በተጨማሪም በክልሉ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 እና ኅዳር 1/2016 ዓ.ም. “ኢመደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለጸ ቡድኖች” በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ጉዳት ሲደርስ፣ በግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወደ ኦሮሚያ ክልል እንደሄዱ ተገልጿል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን በሦስት ቀበሌዎች ውስጥ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ኅዳር 19/2016 ዓ.ም. ለረዥም ሰዓት በፈጸሙት ጥቃት አስራ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ፣ 7 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል እንዲሁም አንድ ሽማግሌ ታፍነው ተወስደዋል ብሏል - ኢሰመኮ።
በተጨማሪም በሦስቱ ቀበሌዎች ያሉ መንደሮች በአብዛኛው በእሳት ሲቃጠሉ፣ በእርሻ ላይ የነበረ ሰብል እና የቤት እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ውድመት ከመድረሱ ባሻገር ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተሰደዋል።
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ ታጣቂዎች ከኅዳር 13/2016 ዓ.ም. ጀምሮ “ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች” በፈጸሟቸው ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃቶች ቢያንስ 30 ሰዎችን መግደላቸውን የመብት ድርጅቱ ገልጾ፣ ከሟቾች መካከልም ጨቅላ ሕፃንን ጨምሮ ነፍሰጡር ሴቶች እና ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊ ይገኙበታል ብሏል።
ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ 36 ምዕመናኖቿ መገደላቸውን በመግለጽ፣ በአካባቢው ከዚህ ቀደምም ጥቃቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን በማመልከት የጥቃቱ ኢላማ ምዕመናኖቿ መሆናቸውን ገልጻለች።
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፣ በሃሞ ቶኩማ አጥቢያ የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን አባላት ላይ “ማንነታቸው ያልተለዩ ታጣቂዎች” ኅዳር 14/2016 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት ዘጠኝ ምዕመናን፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ተገድለዋል።
በክልሎቹ ውስጥ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት ኮሚሽኑ ለይቶ ያወቃቸው ቢያንስ 53 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ውስጥ በተከሰተ ግጭት እና ጥቃቶች የተገደሉት ሰዎች አሃዝን በርካታ መሆናቸውን ገልጿል።
ኢሰመኮ በመግለጫው በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ዐውድ ውስጥ እና ከግጭት ዐውድ ውጪ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ አመልክቷል።
“በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ተስፋፍተው በቀጠሉት ግጭቶች ዐውድ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እና ዘረፋዎች የነዋሪውን ሕይወት እጅግ የከፋ አድርገውታል” በማለት ያለውን ሁኔታ መባባስ ገልጿል።
በአማራ እና በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂ ቡድኖችን ለመቆጣጠር መንግሥት ሠራዊቱን ያሰማራ ሲሆን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳ/ር ዳንኤልም በክልሎቹ ውስጥ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም “ሁሉም ታጣቂ ቡድኖች እና መንግሥት ሰብአዊ የተኩስ ማቆም አድርገው ወደ ውይይት እንዲያመሩ፣ መንግሥት በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች እና ነዋሪዎች በሙሉ የተሟላ ጥበቃ እና ደኅንነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በአማራ ክልል ባለፉት ወራት ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ታጣቂ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጠያቂ መሆናቸውን መንግሥት ቢከስም ቡድኖቹ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
በአገሪቱ በተለይም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ያለውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት ንግግር እንዲደረግ ጥሪ ሲቀርብ የቆየ ሲሆን፣ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ከሳምንታት በፊት ያደረገው ድርድር ያለ ውጤት መክሸፉ ይታወሳል።