ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱኒዚያዊቷ የህግ ባለሙያ በቀጥታ የዜና ስርጭት ወቅት በቁጥጥር ስር ዋለች
ሲቪል የለበሱ እና ጭምብል ያጠለቁ የደህንነት መኮንኖች ቅዳሜ ዕለት በህግ ባለሙያዎች ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው አንዲት የህግ ባለሙያን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት መተላለፉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ሶንያ ዳህማኒ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ቱኒዝያ የከፋ ሁኔታ ላይ ስለመገኘቷ በቃለ መጠይቅ ወቅት ከሰጠቻቸው አስተያየቶች ጋር በተያያዘ ትፈለግ ነበር።
በቁጥጥር ስር በዋለችበት ወቅት “የህግ ባለሙያዎች ነፃ ናቸው። ከፖሊስ ነፃ ናቸው!” የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል።
በፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ አገዛዝ የመናገር ነፃነት ላይ ክልከላዎች ተበራክተዋል የሚሉ ትችቶች እየጨመሩ መጥተዋል።
አርብ እለት ዳህማኒ “ከሰሃራ በታች ያሉ ስደተኞች በቱኒዝያ መቆየት ለምን ይፈልጋሉ? ቱኒዝያ የራሷን ወጣት እየገፋች ያለች እና ተመራጭ አገር አይደለችም ማለቷን” አስመልክቶ ፍርድ ቤት ቀርባ ለማስረዳት ፈቃደኛ አልሆነችም ሲሉ ጠበቃዋ ተናግረዋል።
ቅዳሜ በፍራንስ 24 የቀጥታ ስርጭት ላይ ዘጋቢዋ ማሪሊን ዱማስ፤ ዳህማኒ በነበረችበት የማህበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝታ ነበር።
ከዚያም ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች በጉልበት ወደ ቢሮ ሲገቡ ዱማስ የጀመረችውን አረፍተ መጨረስ ሲያቅታት ታይቷል። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ጭምብል የለበሱት ሰዎች ሲወጡ ሰዎች ሲጮሁ ተሰምተዋል።
ጭምብል ካጠለቁት ግለሰቦች መካከል አንደኛው ካሜራውን ሊሸፍን ሲሞክር ዱማስ "እኛ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ ነን። ይህንን ለማድረግ መብት የለህም" ስትል ተሰምታለች።
ፍራንስ 24 በበኩሉ "ጋዜጠኞች ለፍትህ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስከበር የሚሞክሩትን ጠበቆችን ተቃውሞ ሲዘግቡ የጸጥታ ሃይሎች የፈጸሙት የከፋ ጣልቃገብነት" ሲል አውግዞታል።
እሑድ ዕለት ሁለት ጋዜጠኞች በሰነዘሩት ትችት ምክንያት መታሰራቸውን አንድ የህግ ባለሙያ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።
የጋዜጠኞቹ እስራት እና የዳህማኒ በቁጥጥር ስር መዋል ፕሬዚዳንቱ መስከረም 2022 ከፈረሙት ድንጋጌ 54 በመባል ከሚታወቀው አከራካሪ ህግ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ይታሰባል።
የቱኒዝያ ባለሥልጣናት ህጉ ሐሰተኛ ዜናን ለመዋጋት መውጣቱን ቢናገሩም ተቺዎች ግን ግልጽ ያልሆነ እና በስም ማጥፋት ወይም በስድብ ጥፋተኛ ናቸው ተብለው የተገኙ ሰዎችን በአምስት ዓመት እስራት እንደሚያስቀጣ ተናግረዋል ።
ህጉ ተግባራዊ ከሆነ በኋላም 60 የሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ተቃዋሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኤኤፍፒ የቱኒዚያ ብሄራዊ የጋዜጠኞች ማህበርን ጠቅሶ ዘግቧል።
በእስር ላይ የሚገኙት እንዲፈቱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በዋና ከተማዋ ቱኒዝ እሑድ ዕለት ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ሰኢድ እአአ በ2019 ከተከናወነ ነፃ ምርጫ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡ ቢሆንም እአአ በ2021 ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያባርሩ ፓርላማውን ደግሞ አግደዋል።
በቀጣዩ ዓመት አዲስ ህገ መንግስት በህዝበ ውሳኔ ቢጸድቅም አምባገነናዊ አገዛዝን የመመለስ አደጋ አለው ሲሉ ተቺዎች ገልጸዋል።
የፖለቲካ ምስቅልቅልን እና የኢኮኖሚ ውድቀትን ለማስቀረት የሚያስችላቸውን ስልጣን እንደሆነ በመግለጽ ፕሬዝዳንቱ የውሳኔያቸውን ምክንያታዊነት ተከራክረዋል።