የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ እና ሌሎች አባቶች ወደ አገር እንዲገቡ መንግሥት ፈቀደ

ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ታግደው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ወደ አገር እንዲገቡ ተፈቀደላቸው።

ከአንድ ዓመት በላይ ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ ወደ አገር መግባት ተከልክለው የቆዩት አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ ሌሎች ሁለት የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ መነሳቱን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ባለፈው ዓመት ለቤተክርስቲያኗ ሥራ ከተጓዙበት አሜሪካ ጥር 28/2016 ዓ.ም. ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ ማንነቱ ባልተገለጸ የመንግሥት አካል ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ ተከልክለው ወደመጡበት መመለሳቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ስለ አቡኑ ወደ አገር እንዳይገቡ መከልከል የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም ቤተክርስቲያኗ ግን አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ወደ አገር እንዲገቡ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ለመንግሥት ጥሪ አቅርባ ነበር።

አቡነ ጴጥሮስ ወደ አሜሪካ ከተጓዙ በኋላ "ከአገር ስለመኮብለላቸው" ሐሰተኛ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲሰራጩ የነበረ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኗም ጳጳሱ ወደ አሜሪካ የተጓዙት በሲኖዶሱ እውቅና ለቤተ ክርስቲያኗ ሥራ መሆኑን ገልጻ ነበር።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ፀሐፊ እና የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረጋቸው ስብሰባዎች ላይ በአካል መገኘት ሳይችሉ መቅረታቸው ይታወቃል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ ከዚህ በፊት ወደ አገር መግባት ሳይችሉ ስለመቅረታቸው ብዙም ሳይነገር የነበሩትን ሁለት የቤተ ክርስቲያኗን አባቶች ጨምሮ ጠቅሷል።

መግለጫው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ "መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት እንዲመለከተው በጠየቀው መሠረት" ሦስቱ አባቶች ወደ አገር እንዲገቡ መፈቀዱን አመልክቷል።

የቤተ ክርስቲያኗ አባቶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ምክንያት የሆነው ጉዳይ በግልጽ ምን እንደሆነ ባልጠቀሰው መግለጫ ላይ "ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ" ወደ አገር እንዲገቡ መፈቀዱን ገልጿል።

አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ አቡነ ቴዎፍሎስ ደግሞ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳ አሪዞና አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም አቡነ ያዕቆብ የዩናይትድ ኪንግደም፣ አየርላንድ እና የሩቅ ምሥራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በግልጽ ሦስቱ አባቶች ላይ ወደ አገር እንዳይገቡ እገዳ ተጥሎ ስለመቆየቱም ሆነ አሁን ስለመነሳቱ ያለው ነገር ባይኖርም የቅዱስ ሲኖዶስ አባለት የሆኑት ጳጳሳቱ "በሲኖዶሱ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ እንደሚያደርግ" ገልጿል።

"መንግሥት አገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ቁርጠኛ" አቋም እንዳለው የገለጸው መግለጫው "አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን" አስታውቋል።

አክሎም መንግሥት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን እና ይህም እንደሚቀጥል ጠቅሶ "አንዳንድ አካላት ችግሮችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም እንኳን፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያንዋ እና ለምእመንዋ ሲል በሆደ ሰፊነት ለማለፍ ወስኗል" ብሏል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የነበረው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሎ የቆየ ሲሆን፣ በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ ግንኙነቱ ተበላሽቶ ቆይቷል።