ቻይና የኒውክሌር መሳሪያዎቿን በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍታለች፡ አሜሪካ

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ

ቻይና ባለፈው አንድ ዓመት የኒውክሌር ክምችቷን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋት አሁን ላይ 500 ማድረሷን አሜሪካ አስታወቀች።

በፔንታጎን ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት ቤይጂንግ በአውሮፓውያኑ 2030 የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋን በእጥፍ በማሳደግ ከ1,000 በላይ ለማሳደግ ማቀዷን ገልጿል።

ቻይና ኒውክለርን በመጠቀም “ቀድሞ ያለማጥቃት” ፖሊሲን ለመተግበር በቁርጠኝነቷን እንደቀጠለች ገልጿል።

ሪፖርቱ እንዳመላከተው ከሆነ የመሳሪያው ክምችት ከተገመተው በላይ ቢሆንም፣ የቻይና ክምችት ከሩሲያ እና ከአሜሪካ አንጻር አነስተኛ መሆኑን ጠቅሷል።

እንደ ስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሠላም ምርምር ኢንስቲትዩት ከሆነ ሩሲያ 5,889 ያህል የኒውክሌር አረሮች ሲኖሯት አሜሪካ 5,244 ባለቤት በመሆን ትከተላለች።

ቻይና ወደ 400 የሚጠጉ የኒውክሌር አረሮች እንዳሏት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እአአ በ 2021 ግምቱን አስቀምጧል።

አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “እነሱ [ቻይና] አካሄዳቸውን እንዲያቆሙ ለመጠቆም እየሞከርን አይደለም… ከቀደምት ትንበያዎች ለማለፍ መቃረባቸውን ግን እየጠቆምን ነው” ብለዋል።

ሁኔታው “ለአሜሪካ ከፍ ያለ ስጋትን ይፈጥራል” ሲሉም አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አገራቸው እአአ በ2049 ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጦር ኃይል እንደምትገነባ አስታውቀዋል። ወደ ሥልጣን ከመጡበት እአአ ከ2012 ወዲህ የአገሪቱን መከላከያ ለማዘመን ሲሠሩ ቆይተዋል።

የፔንታጎን ያወጣው መግለጫ ቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት “ከዚህ በፊት ከተደረጉ ሙከራዎች በመጠን እና በልኅቀት የበለጠ ነው” ብሏል።

ቤይጂንግ በ2022 የሦስት አዳዲስ የሚሳኤል ማዕከላትን ግንባታ አጠናቃ ሊሆን እንደሚችል የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

እነዚህም ቢያንስ 300 አዳዲስ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤል ያካትታሉ ሲል ዘገባው ገልጿል።

እነዚህ ሚሳኤሎች ከ5500 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የሚችሉ ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩናይትድ ስቴትስ ዘገባ እንዳመለከተው የሕዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር “የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙት ሃዋይ እና አላስካ የሚገኙ ዒላማዎችን ማጥቃት የሚችሉ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን” ለመሥራት ፍላጎት አላቸው።

ምንም እንኳን የኒውክሌር ክምችቷ እያደገ ቢመጣም ቻይና “ጠላትን ቀድሞ ባለማጥቃት” ፖሊሲዋ እንደቀጠለች ተነግሯል።

የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ባልደረባው ሄንሪ ቦይድ የተባለው የጭማሪ መጠን “በጣም የተጋነነ” እንደማይመስል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቻይና 1,000 የኒውክለር አረሮች እንዲኖራት ያስቀመጠችውን ግብ ለመድረስ “ከተገመተው በላይ በሆነ አነስተኛ ፍጥነት እየሄደች ነው” ሲሉ ግን አምነዋል።

በእስያ ሶሳይቲ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት ላየል ሞሪስ እንደ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ባሉ ዘርፎች መስፋፋት ቻይና ፖሊሲዋን እንደገና እንድታጤን በማድረግ ክምችቷ እንዲስፋፋ እያስገደዳት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቤይጂንግ ከቅርብ ወራት ወዲህ በታይዋን ላይ “ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጫናዎችን አጠናክራለች” ሲል ፔንታጎን ጨምሮ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ዢ፣ በ2027 ደሴቷን በግዳጅ መልሶ በቻይና ስር ለማስገባት ወታደራዊ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ የመከላከያ መሪዎቻቸውን ማዘዛቸውን ተዘግቧል።

ተከታታይ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ፣ ወደ ታይዋን የአየር ክልል በረራዎች እና በውሃ ዙሪያ የሚደረጉ ተከታታይ ወታደራዊ ልምምዶችን በማድረግ ደሴቷን አንዳትረጋጋ እያደረጋት መሆኑን የፔንታጎን ዘገባ አክሎ ገልጿል።

በቻይና እና አሜሪካ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው ሪፖርቱ ይፋ የተደረገው።

ዋሽንግተን ረቡዕ ዕለት የቻይና አየር ኃይል አብራሪዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ “ተንኳሽ እና አደገኛ” በረራዎችን በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የውሃ ክልል ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ላይ ላይ አድርገዋል ስትል ከሳለች።

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት የፔንታጎን ቪዲዮዎችን እና ፎቶዎችን አካቶ የወጣው መግለጫ ከ2021 (እአአ) ወዲህ ተመሳሳይ180 ክስተቶች ነበሩ ብሏል።