እስራኤልን ለማሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነችው ኢንዶኔዥያ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ተሰረዘች

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤልን ቡድን ለማሳተፍ ፈቃደኛ እንዳልሆነች የተገለጸው ኢንዶኔዥያ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነቷ በፊፋ ተሰረዘ።

ባለፈው አርብ በባሊ ሊካሄድ የነበረው የውድድሩ ይፋዊ የእጣ ድልድል መሰረዙን ተከትሎም ውሳኔው እንደተላለፈ ተገልጿል።

የባሊ አስተዳዳሪ ዋይን ኮስተር የእስራኤል ቡድንን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የኢንዶኔዥያ እግር ኳስ ማህበር ውድድሩን ለመሰረዝ መገደዱን አስታውቋል።

ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በአውሮፓውያኑ ከግንቦት 20 እስከ ሰኔ 11 ሊካሄድ እቅድ ተይዞለት ነበር።

ኢንዶኔዥያ ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላትም። ሆኖም በቅርቡ ተቃዋሚዎች ፍልስጥኤምን በመደገፍ የእስራኤል ቡድን ከውድድሩ ከመሳተፍ እንዲታቀብ ሲጠይቁም ተደምጧል።

እስራኤል ለውድድሩ ከማለፏ በፊት ነበር ኢንዶኔዥያ በአውሮፓውያኑ 2019 የአስተናጋጅነት ቦታው የተሰጣት።

“ፊፋ አሁን ባለው ሁኔታ ኢንዶኔዥያ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 2023 አዘጋጅነቷ እንዲነጠቅ ተወስኗል” ሲል ፊፋ በመግለጫው አስታውቋል።

“አዲስ አስተናጋጅ አገር በተቻለ ፍጥነት የምናሳውቅ ሲሆን ውድድሩ የሚካሄድባቸው ቀናት አይቀየሩም። በተጨማሪም በኢንዶኔዥያ እግር ኳስ ማህበር ሊጣሉ የሚችሉ ቅጣቶች በመጪው ጊዜ ይተላለፋል” ብሏል።

ፊፋ ውሳኔውን ከማስተላለፉ ከግማሽ ሰዓት በፊት የኢንዶኔዥያ እግር ኳስ ማህበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አሪያ ሲኑሊንጋ አገራቸው የማስተናገድ መብቷ ይጠበቅላታል የሚለው ተስፋ የመነመነ ነው ብለው ነበር።

"በስፖርት ውስጥ ፖለቲካዊ መስፈርቶችን ለተሳትፎ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ከእግር ኳሱ ምህዳር ውጭ መሆናችን አይቀርም” ብለዋል።

"ለሁላችንም በጣም ፈታኝ ነው። በስፖርቱ ውስጥ ወዳልተረጋጋ ሁኔታ እየሄድን ነው። እግር ኳስን ወይም ስፖርትን እና ፖለቲካን መለያየት አለብን።" ብለዋል።