በኢትዮጵያ ሴቶች ቸል ስለሚሉት የካንሰር ዓይነት ምን ያህል ያውቃሉ?

የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የምትወስድ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, MOH

እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር የሴቶችን ሕይወት በብዛት እየቀጠፉ ካሉ የካንሰር ዓይነቶች መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የጡት ካንሰር የሴቶችን ሕይወት በመቅጠፍ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ዶ/ር ኤልያስ ጀማል በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የማህፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስት ሲሆኑ፣ በማሕፀን ጫፍ ካንሰር ሕክምና ላይ የረዥም ዓመት ልምድ አላቸው።

ማሕፀንን ከሚያጠቁ የካንሰር ዓይነቶች አንዱ ይህ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መሆኑን እና የማሕፀን በር ላይ እንደሚከሰት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም “ለዚህ ዓይነት ካንሰር ዋነኛው መነሻ ኢንፌክሽን ነው። ይህም ኢንፌክሽን 70 በመቶ በሚሆኑ ሴቶች ላይ ይከሰታል” ብለዋል።

ሴቶችን ከሚያጋጥመው ኢንፌክሽን 90 በመቶ የሚሆነውን የራሳቸው ሰውነት እንደሚከላከለው ዶ/ር ኤልያስ ያስረዳሉ።

“ይህ ኢንፌክሸን በሁለት ዓመት ውስጥ በራሱ ሊድን ወይንም ሊጠፋ ይችላል” ይላሉ ስፔሻሊስቱ።

እንደ ዶ/ር ኤልያስ ገለጻ 10 በመቶ የሚሆነው ኢንፌክሽን በሴቶቹ ላይ ይቆያል።

ይህ ኢንፌክሽን ሳይድን ሲቆይ ደግሞ በማሕፀን ጫፍ ካንሰር የመያዝ ዕድል ይፈጥራል።

በሴቶች ሰውነት ላይ የሚከሰተው ኢንፌክሽን ወደ ካንሰር ለመለወጥ ከ10 እስከ 30 ዓመታት ይወስድበታል።

የካንሰሩን እድገት ሂደት ሲገልፁም “የዚህ ዓይነቱ ካንሰር ቶሎ ምልክት አያሳይም፤ በምርመራ ነው የሚታወቀው።

“ከኢንፌክሽን ወደ ካንሰር እየተሻገረ ባለበት ሰዓት ምንም ዓይነት ምልክት አያሳይም። ምልክት ማሳየት የሚጀምረው ወደ ካንሰር ከተለወጠ እና ካንሰሩ በሰውነቱ ውስጥ ማደግ ከጀመረ በኋላ ነው” ይላሉ ዶ/ር ኤልያስ ።

ይህ ዓይነቱ ካንሰር በመጀመሪያ የእድገት ደረጃ ላይ ምልክት ባለማሳየቱ ምክንያት እድሜያቸው ከ30 እስከ 49 መካከል የሚገኙ ሴቶች፣ በየሦስት ዓመቱ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።

ሲጃራ ማጨስ፣ የተለያዩ መድኃኒቶችን መጠቀም፣ ከ20 ዓመት ዕድሜ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነትን መጀመር እና ከአንድ በላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጓደኛ መኖር ለዚህ ዓይነቱ የካንሰር ዓይነት መነሻ ከሚሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ።

የሚታዩ ምልክቶች

ኢንፌክሽኑ ወደ ካንሰር ከተለወጠ በኋላ ለሴቷ ከሚታይዋት ምልክቶች መካከል አንዱ መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ከማሕፀኗ መፍሰስ መጀመሩ ነው ይላሉ ዶ/ር ኤልያስ።

“ሴቶች ይህ ከማሕፀናቸው የሚወጣውን ፈሳሽ በሚያዩበት ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም ይመጣሉ። ነገር ግን ተመላልሰው በመታከም ለውጥ ከሌለ ይህ ኢንፌክሽኑ ካንሰር ሆኗል ማለት ነው።”

ሌላኛው በማሕፀን በር ካንሰር በተያዘች ሴት ላይ የሚታየው ምልክት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከፈፀመች በኋላ ከማሕፀኗ ደም ይፈስሳል።

እንዲህ ዓይነቱን ምልክት ያዩ ሴቶች በእንዲህ ዓይነቱ ካንሰር የመያዛቸው ዕድል ከፍተኛ ስለሆነ ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው መታየት አለባቸው።

በሽንት ቱቦ አካባቢዎች ኢንፌክሽን፣ ከሆድ በታች ሕመም መሰማት፣ እግር ላይ የሚሰማ ሕመምን ሳይታከሙ ከቆዩ ደግሞ ሽንት ለመሽናት መቸገር እንደሚያስከትል ዶ/ር ኤልያስ ያስረዳሉ።

ችግሩ ከመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደረስ ደግሞ ሽንት በፍፁም እንዳይወጣ የማድረግ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ዶ/ር ኤልያስ ይናገራሉ።

በዚህ ካንሰር የተያዙት አብዛኞቹን ሴቶች ሕይወት የሚቀጥፈው ይህ ካንሰር፣ የሽንት ቧንቧን በመዝጋት ኩላሊት ሥራውን እንዲያቆም በማድረግ ነው።

“ብዙዎቹ በዚህ በሽታ የተያዙት የሚሞቱትም፣ ኩላሊታቸው ሥራ ማቆም ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው” ይላሉ ባለሙያው።

ካንሰር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክትባት እና ሕክምና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች፣ እድሜያቸው 14 ለሆኑ ልጃገረዶች በትምህርት ቤቶች ውስጥ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የክትባት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ መንግሥቱ ቦጋለ፣ ይህ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ክትባት በኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን ይናገራሉ።

“በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ካንሰር በዓመት 5000 ሴቶች ይሞታሉ። የሞታቸው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ቀድሞ በማወቅ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን ሕክምና ስለማያገኙ ነው። በተጨማሪም በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ነው” በማለት ይገልጻሉ።

ይህንኑ ችግር ለማቃለል በ2011 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም እድሜያቸው 14 ለሆኑ ሴት ልጆች በሁለት ዙር የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ለዜጎቻቸው የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እየሰጡ ካሉ አስር አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

“በመጀመሪያ ዙር 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶች ተከትበዋል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ናቸው የተከተቡት። በዘንድሮው ዓመት በአራት ክልሎች ውስጥ ነው መሰጠት የተጀመረው። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ደግሞ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ይሰጣል” ብለዋል አቶ መንግሥቱ ቦጋለ።

በመጀመሪያው ዙር ላይ ‘ክትባቱ ሴቶችን መካን ያደርጋል' የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ገጥሟቸው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ መንግሥቱ፣ በአሁኑ ዙር ግን የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ላይ ለውጥ ማየታቸውን ይጠቅሳሉ።

የማሕፀን ጫፍ ካንሰርን የሚያመጣው ቫይረስ በአብዛኛው የሚተላለፈው በግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው የሚሉት የማሕፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ኤልያስ፣ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ላልጀመሩ ልጃገረዶች ክትባቱ ውጤታማ መሆኑን ይናገራሉ።

ይህንን ክትባት የወሰዱ ሴቶች በዚህ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸውን 90 በመቶ የሚቀንስ እና ውጤታማ መሆኑን የሚናገሩት ስፔሻሊስቱ፣ ዕድሜያቸው 14 የሆናቸው ሴቶች በሙሉ ክትባቱን ማግኘት አለባቸው በማለት ይመክራሉ።

ካንሰሩ በሰውነታቸው ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ለሴቶቹ የሚሰጠው ሕክምና የቀዶ ሕክምና እና የጨረር ሕክምና ሲሆን ይህም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የተወሰኑ ሆስፒታሎች ብቻ ይገኛል።

ጥቁር አንበሳ፣ ጳውሎስ፣ ንደር፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ ሪፈራል፣ የሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል፣ የጅማ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ይህ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ሕክምና ከሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች መካከል ናቸው።