በጣልያን በጎርፍ ምክንያት 13 ሰዎች ሲሞቱ 13 ሺህ ተፈናቀሉ

ጣልያን ውስጥ በተከሰተ ጎርፍ ምክንያት 20 ወንዞች በከፍተኛ ሁኔታ ሞልተው በመፍሰሳቸው 13 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

13 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በስድስት ወራት ውስጥ መዝነብ ያለበት መጠን በአንድ ቀን ከግማሽ እንደዘነበ ተገልጿል። ወደ 280 የመሬት መንሸራተቶችም አጋጥመዋል።

ራቬና የተባለው ግዛት ከንቲባ እንዳሉት በምዕተ ዓመቱ ከገጠሟቸው አደጋዎች ይሄ የከፋው ነው። ይህ አካባቢ በጎርፍ ክፉኛ ነው የተጎዳው።

ሚሼል ደ ፓስካል እንዳለው በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

“የከፋ 48 ሰዓት አሳለፍን። መንደራችን በውሃ እና በጭቃ ተሞላ” ሲሉ የ71 ዓመቷ ሮበርታ ላዛሪኒ ተናግረዋል።

ከቦሎኛ በስተደቡብ የሚገኘው ቤታቸው ፈርሷል።

“እንዲህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። መፈናፈኛ አሳጣን። በድጋሚ እንዳይከሰት እመኛለሁ” ብለዋል።

የእሳት አደጋ ተከላካዮች ሰዎችን ከቤታቸው ለማስወጣት ሲጥሩ ነበር።

የሮበርታ ልጅ ላሚሪ “ማኅበረሰባችን ተሰብሯል” ይላል።

“ከዚህ በፊትም ጎርፍ ገጥሞናል። እንዲህ ያለ ግን አይተንም አናውቅ። ብቻችንን እንደቀረን ነው የተሰማን” ብሏል።

“ሁሉም መንገድ ወንዝ ሆነ። አንድም የተረፈን ንብረት የለም” ሲል ገልጾታል።

ኤሚላ-ሮማንጋ በተባለው ግዛት የሚገኝ መንደር ውስጥ ወንዞች ሁሉ ሞልተው እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በራቬና በተካሄደው ነፍስ የማዳን ሂደት ወቅት የሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።

ሩሲ በተባለው መንደር ለሰዓታት ጎርፍ ሳይቀንስ ቆይቷል።

የሕብረተሰብ ጥበቃ ሚኒስትር ኔሎ ሙሲሜሲ እንዳሉት ለ36 ሰዓታት የዘለቀ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 20 ሴንቲ ሜትር በሌሎች ቦታዎች ደግሞ እስከ 50 ሴንቲ ሜትር ደርሷል።

“ለረዥም ጊዜ ሳይዘንብባቸው የቆዩ አፈራማ ቦታዎች እርስ በእርስ ተጣብቀዋል። ውሃ መያዝ አይችሉም” ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ጠርተዋል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለደረሰው አደጋ ተጠያቂ ያደረጉት የጣልያንን አመራሮች ነው። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለመቀልበስ በቂ ጥረት አላደረጉም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ጎርፍ ከሚከሰትባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል የከባቢ አየር መሞቅ ዋነኛው ሲሆን፣ ይህም የሚከሰተው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ነው።

ከኢንዱስትሪ ዘመን ወዲህ ዓለም 1.1 ሴንቲ ግሬድ ግላለች። የካርበን ልቀት የማይቀንስ ከሆነ ሙቀቱ ከዚህም ይልቃል።

ወንዝ አቅራቢያ ካለው ቤቱ የተፈናቀለው አንቶኒዪ ፍራንሴስኮ ሪዙቶ እንዳለው ማንም ሰው እንዲህ የከፋ አደጋ አልጠበቀም።

“በየደቂቃው የውሃው መጠን ከፍ እያለ ነበር። ወደ ቤት ስንመለስ ውሃው ቤታችንን አጥለቅልቆታል። ሁሉንም እቃችንን ነው የጣልነው” ይላል።

ኤሚላ-ሮማንጋ የተባለው ግዛት ቀጠናዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ስቴፋኖ ቦናቺኒ እንደሚሉት የደረሰው ጉዳት በቢሊዮን ዩሮዎች ይገመታል።

ከወንዝ በላይ ወደሆኑ አካባቢዎች ሰዎች እንዲጓዙ የተደረገባቸው ቦታዎች አሉ።

እንደ ሉጎ እና ቼሪቪ ያሉ መንደሮች በተደጋጋሚ ነው ጎርፍ የገጠማቸው።

የ80 ዓመቱ ሊኖ ሌንዚ የልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ክፍል በጎርፍ እንደተጥለቀለቀ ይናገራሉ።

“እዚህ 70 ዓመት ነው የኖርኩት። እንዲህ ያለ ነገር ግን አይቼም አላውቅም። ውሃው ሁሉም ቦታ ነበር። ሁሉንም ንብረታችንን ነው ያጣነው” ብለዋል።

“ማንም ሊረዳን አልመጣም። መንግሥትም የአካባቢው አስተዳዳሪዎችም አልረዱንም። ሰፈራችን ያለ አንድ ወጣት ነው የተባበረን” ሲሉም በቂ እርዳታ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል።