የአባቱን የንግሥ በዓል ሥነ ሥርዓት ከቤተሰቡ ገለል ብሎ የታደመው ልዑል ሃሪ

ከንጉሣውያን ቤተሰቦቹ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ የገባው ልዑል ሃሪ ቅዳሜ ሚያዝያ 28/ 2015 ዓ.ም. የተካሄደውን የአባቱን የንግሥና ሥነ ሥርዓት ከቤተሰቡ ገለል ብሎ ብቻውን ነበር የታደመው።

የሰሴክሱ መስፍን ልዑል ሃሪ በዌስትሚኒስተር አቤ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዶ የነበረውን የንጉሥ ቻርለስ የንግሥና ሥነ ሥርዓት ከወንድሙ በሁለት ረድፍ ርቀት ላይ ተቀምጦ ነው የተከታተለው።

ባለቤቱ ሜጋን መርክል በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ያልታደመች ሲሆን፣ ልዑሉም ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሂትሮው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማቅናቱም ተገልጿል።

የንግሥና ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በረንዳ ላይ ንጉሡ እና ቤተሰባቸው ለሕዝብ ዕይታ በወጡበት ጊዜ ልዑሉ እንዳልተጋበዘ ቢቢሲ ተረድቷል።

ልዑሉ ‘ስፔር’ የተሰኘው አወዛጋቢ መጽሐፉን ከወጣ በኋላ ከንጉሣውያን ቤተሰቦቹ ጋር በአደባባይ ሲታይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሃሪ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ያመራው አርብ ዕለት ሲሆን የአባቱን የንግሥና ሥነ ሥርዓትን ታድሞ ቅዳሜ ዕለት ታድሞ በዚያው ዕለት በብሪታንያ አየር መንገድ ወደ ሎስ አንጀለስ መመለሱን የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የንግሥና ሥነ ሥርዓቱም ካለቀ በኋላ ብቻውን መኪና ውስጥ ሲገባም ታይቷል።

ንጉሡ እና ንግሥቲቱ በዌልስ ልዑል እና ልዕልት እንዲሁም በሌሎች ንጉሣውያን ቤተሰቦች ታጅበው በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በረንዳ ላይ ታይተዋል።

የልዑል ሃሪ ባለቤት ሜጋን መርክል ከልጆቿ ጋር በሎስ አንጀለስ እንደቆየች የተገለጸ ሲሆን፣ የልጃቸው ልዑል አርቺንም አራተኛ ዓመት ልደት እያከበረች ነበር ተብሏል።

ልዑል ሃሪም ለአርቺ ልደት በወቅቱ ለመድረስ የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አንድ ምንጭ ቀደም ሲል ለአሜሪካው የዜና ምንጭ ‘ፔጅ ሲክስ’ ተናግሯል።

ልዑል ሃሪ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ብቻውን እንደሚታደም ቀድሞ የታወቀ ሲሆን፣ በንጉሣዊው ቤተሰብ ውስጥም ምንም ዓይነት መደበኛ ሚና የለውም።

የሃሪ የግል ማስታወሻ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቡ አባላት ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

መጽሐፉ ከቤተሰቦቹ ጋር የተፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሲሆን፣ ከቀሪው ቤተሰቡ የመገለል ስሜት እንደሚሰማው ተናግሯል።

ባለቤቱ ሜጋን መርክል የንግሥናውን ግብዣ ውድቅ የማድረግ ውሳኔዋም በቤተሰቡ ያሉ አለመግባባቶች ስለመካረራቸውም ማሳያ እንደሆነም ተቆጥሯል።