በዛንዚባሩ ንግግር የትኞቹ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሮሞ ነጻነት ጦር እና ግንባር በጋራ በ1976 (እኤአ) በወቅቱ የነበረውን ሥርዓት በመቃወም ነበር የተቋቋሙት።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የግንባሩ ወታደራዊ ክንፍ ሆኖ የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ አመራሩን በዋነኛነት ኤርትራ ውስጥ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ወታደራዊው ክንፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ቤት ተመልሷል።
በአገር ውስጥ ታጥቆ የነበረው ኃይል ግን የትጥቅ ትግልን የሙጥኝ በማለቱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በይፋ ከጦሩ ራሱን መነጠሉን አሳውቋል።
የጦሩ መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል (ጓድ) መሮ የሚመራው ቡድን እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚለው ስም የሚጠራ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው ሲሆን፣ በሽብር ቡድንነትም ፈርጆታል።
ሸኔ ማለት ‘ሸን’ ወይም አምስት ከሚለው የኦሮምኛ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ‘ሸኔ’ ማለት ደግሞ አምስቱ እንደማለት ነው።
በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ አምስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‘ጉሚ ሸኔ’ ተብሎ ይጠራል። ጉሚ ሸኔ ማለት ‘አምስት አባላት ያሉት ጉባኤ’ እንደማለት ነው። ፓርቲው ግን ከአምስት በላይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሊኖረው ይችላል።
በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት በዚህ ቡድን ላይ በሳምንታት ውስጥ እርምጃ እወስዳለሁ ቢልም፤ በቡድኑ ተፈጽመዋል በሚባሉ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የፀጥታ ኃይል ላይ ግድያ እና የባንክ ዝርፊያዎች በመፈጸም ይከሰሳል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጋጋለበት ወቅት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በምሥራቅ ወለጋ፣ ቤጊ እና ጊዳሚ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ነበር። ከትግራይ ኃይሎች ጋር በጋራ ለመሥራትም ተሰማምቶ ነበር።
በተመሳሳይም በቄለም እና ምሥራቅ ወለጋ፤ በደምቢዶሎ እና በጊምቢ ከተሞችም ላይ ጥቃት መፈጸሙን መግለጹ ይታወሳል።
ሰኔ 11/2014 ዓ.ም ቅዳሜ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ጥቃት ፈጽሞ ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ተገልጿል።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር አዛዥ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) “አሁን፣ በበረሃዎች እና በገጠሮችን ብቻ ሳይሆን ጥበቃ ወዳላቸው ከተሞችም እየገባን ነው፤ የፖለቲካ ሰዎችን አስታጥቀው ቢያዘምቱም ጥበቃቸውን እያለፍን ነው” ሲል ተናግሮ ነበር።
ከተሞችን የማጥቃታቸውን አስፈላጊነት “አጥፍተናቸዋል የሚለውን የመንግሥትን ሐሰተኛ መረጃ እና ከፖሊስ በነጠቁት ያረጀ መሳርያ ነው የሚዋጉት ለሚለው [ፕሮፓጋንዳ] መልስ እንዲሆን ነው” ሲል መሮ በወቅቱ ገልጾ ነበር።
ይህ የአማጺው ቡድን እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራን ኦሮሚያ የሕዝቡን ሕይወት በማቃወሱ፣ ሠላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በኦሮሚያ ክልል፣ በፌደራል መንግሥቱም ሆነ በታጣቂ ቡድኑ በኩል ፍላጎት እንዳለ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
ከሳምንት በፊት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ከሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በታንዛኒያ ለመነጋገር ቀጠሮ ስለመያዛቸው ይፋ አደረጉ።
ቀጥሎም ታጣቂ ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ያስቀመጥነውን ቅድመ ሁኔታ በመቀበሉ ለንግግር ፈቃደኛ መሆኑን አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም በፌደራል መንግሥቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የሚደረገው ንግግር በተባለው ቀን በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ አስተዳደር የዛንዚባር ደሴት ተጀምሯል።
በዛንዚባሩ ውይይት ላይ አጀንዳዎችን የመቅረጽ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች መናገራቸውን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል። በመቀጠልም ሁለቱም ወገኖች በየበኩላቸው ፍላጎታቸውን የሚቀርቡበት ነው።
በዚህ ድርድር ዙሪያ ሊኖሩ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ፍላጎት
ለኦሮሞ ነጻነት እንታገላለን የሚለው ጃል መሮ “ዓላማችን የፖለቲካም የጦርም ግፊት የማይደርስበት የኦሮሞን ሕዝብ ነጻነትን ማረጋገጥ ነው፤ ነጻ እና ራሱን የቻለ ኦሮሞ እና ኦሮሚያን ለመመሥረት እና የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ነው” ሲል ቀደም ብሎ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።
“የኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ መጨቆን ቀርቶ፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በእኩልነት መኖር እፈልጋለሁ ካለም እርሱን ለማስከበር እንታገላለን” ብሏል።
በአሜሪካ ኬተሪንግ ዩኒቨርስቲ የታሪክ እና የአፍሪካ ጥናቶች መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር እዝቅኤልም ገቢሳ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቀደም ሲል ጀምሮ ያወጣው ማኒፌስቶ በመጥቀስ ቡድኑ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ማንሳቱን ያስረዳሉ።
ስለዚህ ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ድርድሩ ይዞት የሚገባው ይህንኑ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑን በመጥቀስ “የኢኮኖሚ እና የባህል ጥያቄዎችም ሊኖሩበት ይችላሉ። ነገር ግን የኦሮሞ ብሔርተኞች የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነው ብለው ለብዙ ዘመናት ይዘውት የነበረው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ መፈጸም አለበት የሚል ነው። ይህንኑ ነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ድርድሩ ይዞ ሊገባ የሚችለው” ሲሉ ያክላሉ።
ይህ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ ከመገንጠል ጋር መያያዙን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በዲሞግራፊ፣ በጂኦግራ፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ እና በሁሉ ነገር ማዕከል ነው። ስለዚህ ይህን ታላቅ ሕዝብ ሊገነጠል ነው ብሎ መናገር ለአዕምሮ እንኳን የሚመች አይደለም። ስለዚህ ከፖለቲካ ቋንቋ ውስጥ መቅረት ያለበት ጉዳይ ነው” ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡ ጥያቄ ተመልሷል የሚሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ “በፖለቲከኞች ሳይሆን በኦሮሞ ሕዝብ ድምጽ” የሚወሰን መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው ብቻ ሳይሆን ሊገለገልበት የሚገባ በመሆኑ በአደባባይ የሚፈጸም መሆን አለበት ይላሉ።
መንግሥትስ ምን ይዞ ይቀርባል?
መንግሥት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ኃይልን የመጠቀም ብቻ ሥልጣኑን ማስከበር ዋነኛ ዓላመው እንደሚሆን ይታመናል።
በዚህም ከህወሓት ጋር በተደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ እንደታየው በቀዳሚነት ግጭትን ማቆም በማስከተል ደግሞ አማጺው ትጥቅ እንዲፈታ እና ወደ ሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ እንዲመለስ ማድረግ የማይቀር ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
እንደ ፕሮፌሰር እዝቅኤል ከሆነ መንግሥት ይዞ መቅረብ የሚችለው መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን እንደሆነ ይገምታሉ።
የመንግሥት ሥልጣን የሚመነጨው “ከመሪዎች ሳይሆን ከሕገ መንግሥቱ በመሆኑ መንግሥት ‘እኔ አስፈጻሚ ነኝ እና የምፈልገውን ነገር በሙሉ አድርጋለሁ’ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ‘የተሰጠኝ ተግባር አለና እሱን መፈጸም አለብኝ። ለመፈጸም እንድንችል በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምን ምን እናስተካክል’ የሚል ሃሳብ ያቀርባል” ብለው ያስባሉ።
ለዚህ ደግሞ ዋናው ነገር ለሁለቱም ወገኖች መነሻ መሆን የሚችለው አገሪቱን ያቋቋመው እና አሁንም አንድ ላይ ይዞ ያለው ሕገ መንግሥት ከተከበረ ከሆነ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህ ደግሞ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት በዋቢነት አንስተዋል።
ለደቡብ አፍሪካው ስምምነት “መሠረት የነበረው ሕገ መንግሥቱ ነው። አሁንም ይኸው ነው መሆን የሚችለው። ከዚያ በኋላ በፖለቲካ ድርድር ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት የሚያስፈልግ ከሆነ ሁሉም ብሔር እና ብሔረሰቦች በተወካዮቻቸው በኩል የሚገናኙበት ሌላ ጊዜ የሚደረግ ስብሰባ ሊደረግ ይችላል።”
ጨምረውም መጀመሪያ ተኩስ ማቆም፣ ከዚያ በኋላ ግጭትን ማስወገድ (ሴሴሽን ኦቭ ሆስቲሊቲስ)፣ ከዚያ የፖለቲካ እና የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁለቱ ወገኖች የሚከተሉት አካሄድ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
ለድርድሩ ፈታኝ የሚሆኑ ነገሮች ይኖራሉ?
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ከሆነ መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በግጭት ውስጥ ናቸው። በዚህም ሳቢያ ደም እየፈሰሰ ነው። ስለዚህም ሁለቱም ወገኖች ይህንን የማስቆም ፍላጎት ስላላቸው ነው ወደ ንግግር የገቡት።
“ሁለቱም ወገኖች በጎ ፈቃድ ካላቸው ድርድር ጨርሰን ሠላማዊ ፖለቲካ ውስጥ እንገባለን፤ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንሄዳለን ብለው በሙሉ ልብ እና በበጎ ፈቃድ ተሰብስበው ከሆነ ብዙ የሚያስቸግራቸው አይመስለኝም።”
ስለዚህም ፍላጎቱ ካለ ይህ ንግግር እንዳይሳካ የሚያደርግ ነገር የለም የሚሉት ፕሪፌሰር እዝቅኤል “ሕገ መንግሥቱ ለሁለቱም ወገኖች ኃላፊነታቸውን እና ግዴታቸውን ማስቀመጡን” ያነሳሉ።
ሆኖም ፈተና መኖሩን አይሸሽጉም። “ያለውን ሕገ መንግሥት እና ሥርዓት የሚቃወሙ ወገኖች አሉ። ስለዚህ ፈተናው የሚኖረው ከመደራደሪያ ጠረጴዛው ዙሪያ ሳይሆን ከዚያ ውጪ፣ በፕሮፖጋንዳ እና በተለያዩ መንገዶች መሰናክል ሊፈጠር ይችላል” ብለው ይገምታሉ።
ከማን ምን ይጠበቃል?
ከዚህ በፊት ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንጻር እና ለንግግሩ ስኬት ከመንግሥት፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ከአሸማጋዮቹ የሚጠበቁ ጉዳዮች እንዳሉ ይታወቃል።
በመንግሥት ከህወሓት እና ከሌሎች ቡድኖች ሲጠበቅ እንደነበረው ታጣቂው ቡድን ሰላማዊ አማራጭን ብቻ እንዲከተል እንዲሁም ትጥቅ እንዲፈታ በዋናነት የሚጠብቀው እርምጃ መሆኑ አይቀርም።
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል በሽብር ቡድንነት የተጣለበት ፍረጃ እንዲነሳ እንዲሁም ከዚህ በፊት ሲጠይቀው እንደነረው የፖለቲካ ያላቸው እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቁ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ልዩነታቸውን በሰላም ለመቋጨት በሚያደርጉት ውይይት ኬንያ እና ኖርዌይ ዋነኛ የአሸማጋይነት ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ እና ውይይቱ እንዲጀመር የስዊድን፣ የኖርዌይ፣ የኬንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ድጋፍ እየሰጡ እንደነበር ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረው ነበር።
በተጀመረው ንግግር ከመግባባት ላይ ለመድረስ ከሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በማቀራረብ ሰላም በሚያወርድ መልኩ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ አለ።
መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በየበኩላቸው ሊሟሉ እና ሊከናወኑ የሚገቧቸው ነገሮች በመኖራቸው ለመስማማት ሰጥቶ የመቀበል መርኅ አስፈላጊ በመሆኑ ማን ምን ለማድረግ ተስማማ የሚለው በንግግሩ መቋጫ ላይ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በሻገር የተጀመረው ንግግር ውጤታማ እንዲሆን አቀራራቢዎቹ እና አሸማጋዮቹ ወገኖች በሎጂስቲክስና እና በገንዘብ በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ - ፕሮፌሰር እዝቅኤል።
“በሁለቱም በኩል የሚወጣ ወጪ አለ። የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ ወጪውን ለመሸፈን ይችላል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን ወጪውን ለመሸፈን ላይችል ይችላል። ስለዚህ መንግሥታት እና ድርጅቶች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።”
አክለውም ድርድሩን ለማሰናከል ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ መኖሩን በመጥቀስ፣ ሕዝቡ በዚህ ውስጥ ሚና እንዳለው ያነሳሉ።
“በተለይም ይህ የሚደረገው ንግግር በቀጥታ የሚመለከተው የኦሮሞን ሕዝብ ስለሆነ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተደራዳሪዎች ወጥተው ይሄን አድርገናል እስከሚሉ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ ነው ያለበት” ብለዋል።












