በአሜሪካ ታዋቂ አትሌቶች የወሲብ ጥቃቶችን ችላ በማለት ኤፍቢአይን ሊከሱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ የብሔራዊ የጂምናስቲክ ቡድን ዶክተር የወሲብ ጥቃት ደርሶብናል ያሉ አትሌቶች ኤፍቢአይን በ1 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊከሱ ነው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የአሜሪካ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በሕክምና ባለሙያው ላሪ ናሳር የተፈጸሙ የወሲብ ጥቃቶች ላይ ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎች ቢቀርቡም በአግባቡ አላስተናገደም ብለዋል።
ከከሳሾቹም መካከል የኦሎምሊክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎቹ ሲሞን ባይልስ፣ አሊ ሬይስማን እና ማኬይላ ማሮኒ ይገኙበታል።
ዶክተር ላሪ ናስር የጂምናስቲክ ስፖርተኞቹ ላይ ትንኮሳ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃቶችን በማድረስ ወንጀል የ175 ዓመት እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።
የኤፍቢአይ የበላይ ጠባቂ በበኩሉ ኤፍቢአይ ስለ ዶክተሩ የቀረበውን ክስ ችላ ማለቱንና የምርመራው ጅማሮ ላይም ስህተቶችን መሥራቱን አጋልጧል።
ባለፈው ዓመት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት የዋና ኢንስፔክተር ጽሕፈት ቤት ሪፖርት ኤፍቢአይ በዶክተሩ ላይ ስላከናወነው ምርመራ ግምገማ ሰጥቷል።
በሪፖርቱ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2015 ዶክተሩ ፈፅሟቸዋል በተባሉ ጥቃቶች ላይ ምርመራ ቢጀመርም ምንም ነገር ሳይደረግ ከአንድ ዓመት በላይ እንዲቀጥል ተደርጓል ይላል።
ለዚህም የኤፍቢአይ ወኪሎች ስህተቶችን በመፈጸም እንዲሁም ሆን ብለው ለመሸፋፈን እንደሞከሩ ሪፖርቱ አመልክቷል።
ለኤፍቢአይ ሪፖርት ከተደረገ በኋላም ዶክተሩ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ተከሳሾቹ አጋልጠዋል።
አብዘኞቹ የአሜሪካ ብሔራዊ የጂምናስቲክ ፕሮግራም አካል እንዲሁም በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የዶክተሩ ክሊኒክ ሕክምና ይከታተሉ የነበሩ አትሌቶች ናቸው።
ሪፖርት የተደረገላቸው የኤፍቢአይ መርማሪዎች እዚህ ግባ የማይባል እርምጃ እንደወሰዱ እና ምርመራ በማከናወን ዘርፉ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረጉም እንዲሁም ሌሎች ባለሥልጣናትን አላስጠነቀቁም ተብሏል።
“የነዚህ ወሲባዊ ጥቃቶች ሰለባ የሆንን አትሌቶች እኛን ሊጠብቁን በሚገቡ ሁሉም ተቋማት ማለትም በአሜሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በአሜሪካ ጂምናስቲክስ፣ በኤፍቢአይ እንዲሁም በፍትሕ ዲፓርትመንቱ ተክደናል” በማለት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ኬይላ ማሮኒ በሰጠችው መግለጫ ተናግራለች።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት ኤፍቢአይ ምርመራውን በተሳሳተ መንገድ ይዘውታል የተባሉ ሁለት የኤፍቢአይ ወኪሎች ላይ ክስ ላለመመሥረት ወስኗል።
ከሳሾቹ አትሌቶች ተቋሙ ላደረሰው ጉዳት ካሳ የጠየቁ ሲሆን ይህም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።












