በግጥሚያ መሀል አየር ላይ ቡጢ የሰነዘረው ደቡብ አፍሪካዊ ቦክሰኛ ሕይወቱ አለፈ

ደቡብ አፍሪካዊው የቀላል ሚዛን ቦክሰኛ ያለፈው እሑድ ግጥሚያ ላይ ሳለ ሕይወቱ አለፈ።
ሲሚሶ ቡቴልዚ የተባለው የ24 ዓመት ቦክሰኛ ለ10 ዙር ከተጫወተ በኋላ ነው ሕይወቱ ያለፈው።
የቀላል ሚዛን ቦክሰኛው ደርባን ውስጥ በተካሄደው ግጥሚያ ሳቢያ አንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ለሕልፈት እንደተዳረገ ተገልጿል።
ሲፌስህሌ ሙቱንግዋ ከተባለው ቦክሰኛ ጋር ለአፍሪካ ቀላል ሚዛን ሻምፒዮናነት ገጥመው፣ 10 ዙር ያህል ተጫውተው ነበር።
ሆኖም ግን ከ10ኛው ዙር በኋላ ሲሚዞ ቡቴልዚ አየር ላይ ቡጢ ሲሰነዝር የተመለከቱት ዳኛ ጨዋታው እንዲቋረጥ ወስነዋል።
የ24 ዓመቱ ቦክሰኛ ቡጢ እየሰነዘረ የነበረው በተቀናቃኙ ላይ ሳይሆን እንዲሁ ማንም ወደሌለበት አቅጣጫ፣ አየር ላይ ነበር።
በጨዋታው መሀል ተቀናቃኙ በቦክስ መጋጠሚያው ገመድ በኩል ሾልኮ ከወጣ በኋላ ጨዋታው በድጋሚ እንዲጀመር ተወስኗል።
ጨዋታው በድጋሚ ከተጀመረ በኋላ ግን ቦክሰኛው ተቀናቃኙን ትቶ አየር ላይ ቡጢ ሲሰነዝር ታይቷል።
ሲፌስህሌ ሙቱንግዋ ጨዋታውን እንዳሸነፈ ከተገለጸ በኋላ ሲሚሶ ቡቴልዚ ራሱን በመሳቱ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
አንጎሉ ውስጥ ደም እንደፈሰሰ ከታወቀ በኋላ ኮማ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
የደቡብ አፍሪካ የቦክስ ፌደሬሽን እና የቦክሰኛው ቤተሰብ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ቦክሰኛው ማክሰኞ ማታ ሕይወቱ አልፏል።
“ግሩም ቦክሰኛ ነበር። ውድድር ላይና ከውድድር ውጭም ተምሳሌት ነበር” ይላል መግለጫው።
በሆስፒታሉ ተገቢው ሕክምና ቢሰጠውም ሕይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
ፌደሬሽኑ የሕክምና ውጤቱን በገለልተኛ አካል አስመርምሮ ውጤቱን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅም አክሏል።
የቦክሰኛው አሠልጣኝ ቤኪ ምንጎሜዝሉ፣ ቦክሳው እስከ ውድድሩ ድረስ ፍፁም ጤናማ እንደነበር ተናግረዋል።












