“የሚላስ የሚቀመስ እንኳን አልነበረንም” ብራዚላዊው ኮከብ ሪቻርሊሰን

ብራዚላዊው አጥቂ ሪቻርሊሰን እየተካሄደ ባለው የዓለም ዋንጫ ሰርቢያ ላይ ‘በመቀስ ምት’ ያስቆጠራት ጎል ስያሜ ታጥቶላታል። 

ብዙዎቹ ዐይናቸው ሌላኛው ብራዚላዊ የእግር ኳስ ማግኔት ኔይማር ላይ ነበር። ነገር ግን በዚህ ጨዋታ የሰዎችን ቀልብ የገዛው የ25 ዓመቱ ሪቻርሊሰን ነው። 

ሪቻርሊሰን፤ የሰርቢያ ብሔራዊ ቡድንን መረብ ሁለት ጊዜ በመጎብኘት የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።

የቶተንሃሙ አጥቂ፣ ብራዚል በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የጎል መዝገቧን የከፈተችባቸውን ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። 

ይህ አጥቂ ሜዳ ላይ በሰራው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ በፈጸመው በጎ ምግባርም ስሙ ሲነሳ ከርሟል። 

ለመሆኑ ሪቻርሊሰን ማነው? ከሌሎች ብራዚላዊ ከዋክብትስ ምን ይለየዋል?

ዕድገት

ምንም እንኳ ሪቻርሊሰን ከአብዛኞቹ ብራዚላውያን ጋር የሚያመሳስለው ነገር ቢኖርም፣ እሱን ልዩ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉት።

ከአንዲት ትንሽዬ መንደር ኪሳቸው ካልዳበረ ወላጆች የተወለደው ሪቻርሊሰን በ16 ዓመቱ ትምህርት አቋርጦ ኳስ ማዘውተርን መረጠ።

ሪቻርሊሰን ከሁሉ ትሻለኛለች ብሎ የመረጣ እግር ኳስ ወላጆቹን፣ ወንድም እና እህቶቹን ትደጉም ጀመር።

ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከማምራቱ በፊት ለአትሌቲኮ ሚኔይሮ እና ለፍሉሚኒሴ ተጫውቷል። 

ወደ እንግሊዝ ከመጣ በኋላ መጀመሪያ ለዋትፈርድ ለጥቆ ደግሞ ብዙ ስምና ዝና ላተረፈረበት ኤቨርተን ተሰልፏል። 

እየተጠናቀቀ ባለው በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት ለለንደኑ ክለብ ቶተንሃም የፈረመው ሪቻርሊሰን፣ ሳይንስና ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በመሥራት አልፎም ዘረኝነትን በመፋለም ይታወቃል።

ተጫዋቹ በትውልድ አገሩ በሠራው የበጎ አድራጎት ተግባርም በፈረንጆቹ 2020 ከእንግሊዝ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ኮቪድና ክትባት

ብራዚል ውስጥ “እግር ኳስ እና ፖለቲካ አንድ ላይ አይሄዱም” የምትል ከብዙዎች አፍ የማትይጠፋ አባባል አለች።

ምንም እንኳ ብራዚላውያን የእግር ኳስ ጥበበኞች ፖለቲካን እንደተላጠ የኤሌክትሪክ ገመድ ቢፈሯትም ኔይማር የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጃይር ቦልሶናሮን በግልጽ ደግፎ ነበር።

ሪቻርሊሰንም ሐሳቡን በይፋ ከመግለጽ ያገደው አንዳችም ኃይል አልነበረም።

ብራዚል በኮቪድ ወረርሽኝ ትናጥ በነበረበት ወቅት ስለክትባት ጥቅም ለማወጅ የቀደመው አልተገኘም። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ 700 ሺህ ያህል ብራዚላውያንን ቀጥፏል።

የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት የኮቪድ ክትባትን ሲነቅፉ በነበረበት ወቅት፣ ሪቻርሊሰን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሚድያ ተከታዮቹ ይህን መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡

“እባካችሁ! ከልቤ ልማፀናችሁ። ክትባት መውሰዳችሁን እንዳትዘነጉ. . . ክትባቱ የእናንተ ነው። መብታችሁ ነው። ይህ ዕድል እንዳያመልጣችሁ።”

ሪቻርሊሰን፤ የሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር ከሆነ በኋላ የእግር ኳስ ጫማውን ለጨረታ አቅርቦ ገንዘቡን ለቤተ-ሙከራዎች ለግሷል።

እሣት፣ አማዞን

የብራዚልን የአካባቢ ሳይንስ ፖለሲ በጽኑ በመንቀፍ የሚታወቀው ሪቻርሊሰን በአገሩ ብራዚል የተነሳው እሣት የአገሪቱ ዋነኛ የብዘሃ ሕይወት መገኛ የሆነውን አካባቢ 30 በመቶውን ሲያወድም ድምፁን አሰምቷል።

ይህ ስፍራ ፓንታናል የሚባል ሲሆን፣ በብራዚል የሚገኝ እጅግ ጠቃሚ የሥነ-ምኅዳር አካል ነው።

አንድ ቃለ-መጠይቅ ሲያደርግ በእሣት ወደተጎዱት ሥፍራዎች ሄዶ በዐይኑ ያየውን ማመን እንዳቃተው ተናግሯል። 

ሪቻርሊሰን፤ ሰኔ 2022 ብሪታኒያዊው ጋዜጠኛ ዶም ፊሊፒስ ወደ አማዞን ጫካ ተጉዞ ደብዛው ከጠፋ በኋላ ባለሥልጣናት ፍለጋቸው እንዲያጠናክሩ ጠይቆ ነበር።

ዘረኝነት

ባለፈው መስከረም ብራዚል ከቱኒዚያ ጋር ፓሪስ ላይ በነበራት የወዳጅነት ግጥሚያ ላይ ጎል ያስቆጠረው ሪቻርሊሰን ደስታውን ሲገልጽ ሙዝ ይወረወርበታል።

ዘረኝነትን ለመግታት “ሥልጣኑ ያላቸው ሰዎች ወሬ ብቻ ከሆኑ፤ ይህ ድርጊት ይቀጥላል” ሲል በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

“ዘረኝነት ሁሌም አብሮን የሚኖር ነገር ነው። በቃላት እና በድርጊት ብቻ ሳይሆን በማይታይ መልኩ ይገለጣል” ሲል በፈረንጆቹ 2020 ተናግሮ ነበር።”

“ልጅ እያለሁ ከጓደኞቼ ጋር እግር ኳስ ስጫወት አንድ ሰው ምንም ሳላጠፋ ሽፍታ ሲል ሰደበኝ። ይህ ዘረኝነት ነው። ሰዎች ከፊት ለፊታቸው ጥቁር ሰው ሲመጣ አቅጣጫ ከቀየሩ ይህም ዘረኝነት ነው።”

“እኒህ የማይታዩ የሚመስሉ ጉዳዮች ዘረኝነት ምን ያህል እንደሰረጸ ያሳያሉ” ሲል ድምፁን አሰምቷል።

ሪቻርሊሰን፤ ጆርጅ ፍሎይድ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ አንድ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ረግጦ ከገደለው በኋላ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙ እግር ኳሰኞች መካከል አንዱ ነው።

ከደሃ የተወለደው

ሪቻርሊሰን፤ ኤስፒሪቶ ሳንቶ ከተባለችው ግዛት ድህነት ከደቆሳቸው ወላጆች ነው የተወለደው።

ታዳጊ ሳለ ከረሜላ እና ማስቲካ እየሸጠ ወንድ አያቱ የቡና እርሻቸውን እንዲገፉበት ያግዛቸው ነበር። 

“አንዳንድ ጊዜ. . .” ይላል ሪቻርሊሰን፤ “የሚላስ የሚቀመስ እንኳን አልነበረንም።”

ትምርህርቱን አቋርጦ ወደ እግር ኳስ ያመራበት ዋነኛው ምክንያት ቤተሰቡን ለመደጎምና ጠረጴዛቸው ላይ ምግብ ለማቅረብ ነው።

“ይህ የእኔ ታሪክ ብቻ አይደለም። እኔ ባደግኩበት ከተማም ሆነ በሌሎች የብራዚል ከተሞች ያሉ ሕፃናትም ነው” ሲል ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል።

“ብዙዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ሥራ ፈልገው ቤተሰቦቻቸውን ያግዛሉ። ትምህርት ያቋረጠ ሕፃን ሳይ ልቤ ይሰበራል። ራሴን በእነሱ ውስጥ አየዋለሁ።”

ቲክቶክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ በተሰኙት የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች ላይ 19 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሪቻርሊሰን ከእግር ኳስ ሜዳ ውጪ ብዙዎችን ማነቃቃት ይፈልጋል።

“የእግር ኳስ ሕይወቴን ከተመለከትኩ በኋላ በጣም ትልቅ ነገር ማድረግ እንደምችል እየገባኝ መጣ” ሲል ለኤቨርተን እየተጫወተ ሳለ ተናግሯል።

“ይህ የገንዘብ ጉዳይ አይደለም። መጀመሪያ ለቤተሰቦቼ ቤት ሠርቶ መስጠት ነበር ዓላማዬ። አሁን ግን ከዚህ የተሻለ ብዙ ነገር ማድረግ እንደምችል አመንኩ።”