በኤምባሲ ሠራተኛ ላይ ሽጉጥ ያነጣጠሩት የዩኬ አምባሳደር ሥራ ለቀቁ

በሜክሲኮ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር

የፎቶው ባለመብት, X/@subdiplomatic

በሜክሲኮ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር በኤምባሲው ሠራተኛ ላይ ሽጉጥ በመደገናቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ተገለጸ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀው ቪድዮ ጆን ቤንጃሚን መሣሪያ በሠራተኛ ላይ አነጣጥረው ያሳያል። መጀመሪያ ዘገባውን ያወጣው ፋይናንሻል ታይምስ ነው።

“በሜክሲኮ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ሰው በየቀኑ እየተገደለ ቢሆንም ይህ ሰው በሽጉጥ ይቀልዳል” የሚል ጽሑፍ ከቪድዮው ጋር ተለጥፏል።

አምባሳደሩ የተሳሳተ ቀልድ ነበር ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፣ የአምባሳደሩን ስም በሜክሲኮ የሚገኙ የዩኬ ልዑካን ዝርዝር ውስጥ አውጥቷል።

በኃላፊነት ላይ ከ2021 እስከ 2024 እንደቆዩ በዩኬ ድረ ገጽ ላይ ተጽፏል።

አምባሳደሩን የሚመስል ሰው መሣሪያ ይዞ መኪና ውስጥ ሲገባና የተለያዩ ሰዎች ላይ ሲያነጣጥር ይታያል።

ከጀርባ ሳቅ የሚሰማ ሲሆን፣ አንድ ሰው መሣሪያው ሲደገንበት ምቾት በማጣት ሲንቀሳቀስም በቪድዮው ይታያል።

አምባሳደሩ ከሜክሲኮ በፊት በጋና እና ቺሊ ሠርተዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በብዛት በመጻፍ የሚታወቁ ሲሆን፣ ብዙ የኤክስ ተከታዮችም አሏቸው።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለ ፓስፖርትና ሌሎችም ጉዳዮች ለሚጠይቁ ሰዎች በቀጥታ ምላሽ በመስጠት ይታወቃሉ።

ስለ አፍሪካ ፖለቲካ፣ እግር ኳስ እና ሮክ ሙዚቃ አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ።

ከሌሎች አምባሳደሮች አንጻር ለማነጋገር ቀላል ተብለው የሚወሰዱም እንደሆኑ ተገልጿል።

በሜክሲኮ የዩኬ ሙዚቃ ያለው ለስላሳ የዲፕሎማሲ መንገድን በተመለከተ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ሙዚቃ የሚወዱት አምባሳደሩ የዩኬ ሙዚቀኞች ሜክሲኮን እንዲጎበኙ በመጋበዝና አንዳንዴም ቤታቸው በማስተናገድ ይታወቃሉ።

በ2021 ሜክሲኮ አምባሳደር ከሆኑ በኋላ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። 32 አገራትም በቆይታቸው ተጉዘዋል።

በጉዞ ላይ ሳሉ የአደንዛዥ ዕፅ ቡድን ሲናሎዋ እና ዱራንጎ የተባሉ ግዛቶችን ተቆጣጥሯል። ይህንን ተከትሎ የኤምባሲው ሠራተኛ ላይ ሽጉጥ ማነጣጠራቸው ተሰምቷል።

አምና ከ30,000 በላይ ሰዎች በሜክሲኮ ተገድለዋል።

ሜክሲኮ ጠንካራ የመሣሪያ ሕግ አላት።

አምባሳደሩ ቀልድ ብለው ድርጊቱን ቢፈጽሙም መሣሪያው ቀለሀ ያለው ከመሆኑም ባሻገር ድርጊቱ የተፈፀመው በሜክሲኮ አደገኛ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ነገሩን ያባብሰዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለፋይናንሻል ታይምስ “ስለ ነገሩ እናውቃለን። ተገቢውን እርምጃ ወስደናል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ቢቢሲ ከአምባሳደሩም ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱም ማብራሪያ ጠይቋል።