ዲዲዬ ድሮግባ ሃይማኖቱን ወደ እስልምና ቀይሯል መባሉን አስተባበለ

የቀድሞው ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ዲዲዬ ድሮግባ ሃይማኖቱን ወደ እስልምና ቀይሯል መባሉን አስተባበለ።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር አይቮሪ ኮስት ዜጋ የሆነው ድሮግባ ይህን ያለው ከአንድ የሙስሊም የእምነት መሪ ጋር ሲጸልይ የሚያሳይ ምስል በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው።

ከድሮግባ ጋር በምስሉ የሚታዩት የእስልምና ሃይማኖት መሪ ፎቶግራፉን በማጋራት ድሮግባ ሙስሊም ሆኗል ሲሉ አስታውቀው ነበር።

ድሮግባ ከእስልምና እምነት መሪው ጋር ሲጸልይ የሚያሳየው ምስል በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ በርካቶች የቀድሞ እግር ኳሰ ተጫዋች እምነቱን መቀየሩን ሲቀባበሉት ነበር።

ይሁን እንጂ ዲዲዬ ድሮግባ ይህ እውነት አይደለም ሲል ሰኞ ምሽት በትዊተር ገጹ ላይ አስታውቋል።

ድሮግባ የትውልድ መንደሩን ሲጎበኝ፤ “ለሙስሊም ወንድሞቼ ያለኝን ክብር” ለመግለጽ ነው አብሯቸው እንደጸለየ በመናገር፣ ሃይማኖቱን አለመቀየሩን ገልጿል።

ድሮግባ ‘ከሙስሊም ወንድሞቹ’ ጋር ያሳለፍውን ጊዜ “የአብሮነት ጊዜ” ሲል ገልጾታል።

የድሮግባን ምስል ያጋሩት እና የእስልምና ሃይማኖትን መቀበሉን የገለጹት ሞሐመድ ሳላህ የተባሉት የሃይማኖት መሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩትን ምስል አጥፍተዋል።

ቀጠል አድርገው ደግሞ ድሮግባ የእስልምና ሃይማኖትን አልተቀበለም ያሉ ሲሆን፣ ሃይማኖቱን ወደ እስልምና እንዲቀይር በጸሎታቸው እንደሚያስቡት ገልጸዋል።

ዲደዬ ድሮግባ እግር ኳስ መጫወት ከማቆሙ በፊት ለአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዩ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ለሚወዳደሩ የእግር ኳስ ክለቦች ተጫውቷል።

ድሮግባ በተለይ ለእንግሊዙ ቼልሲ 11 ቁጥር መለያ ለብሶ በመጫወት ዝናው ናኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በክለቡ ታሪክም ከከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።

በተጨማሪም ለአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ቡድን ከ100 ጊዜ በላይ ተሰልፎ የተጫወት ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 እና 2010 የዓለም ዋንጫዎች ላይም ዝሆኖቹ ከሚባለው የአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተሰልፏል።

ድሮግባ እአአ 2018 ጫማውን ከመስቀሉ በፊት የአይቮሪ ኮስት የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችሏል።