በብዙዎች የማይታወቀው የ560 ኪሎ ሜትር የበረሃ ላይ የሩጫ ውድድር

“ፖሊሶች ሲያስቆሙህ ምስኪን ሁን” ይላል ኒልስ አሬንድ።

“እኔ እንዲያውም ፖሊስ ሳይ ያንገፈግፈኛል። ነገር ግን የስፒድ ፕሮጀክት አባል ከሆንክ ሁላችንም ነው የምትወክለው።”

“ለዚህ ነው ምስኪን ሁን የምንለው። ተባባሪ ሁን። «ምንድነው የምታደርገው?» ብለው ሲጠይቁህ፤ ጓደኛሞች አንድ ላይ ሆነን ወደ ቬጋስ እየሮጥን ነው በል” ይላል።

“ከዚህ የዘለለ ሊያውቁ አይገባም።”

አሬንድ ሰሜን ለንደን የሚገኝ አንድ ባር ቁጭ ብሎ የዚህን ምስጢራዊ ሩጫ ሕግጋት ያስረዳል።

አንዱ ሕግ የፀጥታ ሰዎች ሲያገኙህ እጅግ ተባባሪ መሆን እና ምንም ምስጢር አለማውጣት ነው።

ዘ ስፒድ ፕሮጀክት፤ ከሎስ አንጀለስ እስከ ላስ ቬጋስ የሚደረግ፤ እስካሁን ቅጣት ያልተላለፈበት፤ ስፖንሰር የሌለው 563 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሩጭ ውድድር ነው።

ድረ-ገፅ የለውም። ‘እዚህ ይመዝገቡ’ የሚል አማራጭም አልያዘም። ሕግ የለውም። በዚህ ነው መንገዱ የሚል ጥቆማ አይገኝም።

ተመልካች ማግኘት ፈፅሞ አይታሰብም። ውድድሩ አንድ ሳምንት እስኪቀረው ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው።

ይህ የሩጫው ዓለም የፈጠረው ‘የጡጫ ክለብ’ ነው። እርግጥ ነው ድብድብ የለውም።

ወደ ሎስ አንጀለስ አቅንቶ ድብቅ የሩጫ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ሃምቡርግ ካለ አንድ የደራ መንደር ፓርቲ ያሰናዳ ነበር።

ምንም እንኳ ይህ የሩጫ ውድድር ምስጢራዊ ቢሆንም፣ የዓለማችን ፈጣን እና ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም ትላልቅ ድርጅቶች ያውቁታል።

እንዴት ሊያውቁት ቻሉ? ይህም ሌላኛው ምስጢር ነው።

አሬንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን በረሃ በሩጫ ያቋረጠው ከአምስት ጓደኞቹ ጋር ነው። ሦስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች።

ሩጫው እየደራ ሲመጣ ብሪታኒያዊው ‘አልትራ’ ሯጭ ጄምስ ፑል ሳይቀር ይሳተፍ ገባ።

በይፋዊው መንገድ የሚደረገው ሩጫን ተሽቀዳድመው ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች፣ የዚህ ውድድር አባል ለመሆን ይሻሉ።

ዘ ስፒድ ፕሮጀክት ባለንበት ዓመት 10ኛ ዓመቱን አክብሯል። ይሄኔ ነው ውድድሩን ስፖንሰር ካላደረግን የሚሉ የታዋቂ ምርት ባለቤት ተቋማት (ብራንዶች) እየተጋፉ ወደ አሬንድ ቢሮ የመጡት።

ናይኪ፣ ትራክስሚዝ፣ ኒው ባላንስ. . . ብቻ የስፖርት ትጥቅ በማምረት የሚታወቁ ድርጅቶች ደጅ እየጠኑ ነው።

ሩጫው የሚጀምረው ሳንታ ሞኒካ ፒዬር ከተማ ነው። ሌሊት 10 ሰዓት።

ውድድሩ ትኩረት ይፈራል። የሰው ዐይን ያፍራል። እንዲያም ሆኖ ከዕይታ አልተሸሸገም። እንዲያውም በይፋ አደባባይ ቢወጣ ከሚያገኘው በላይ ትኩረት እየሳበ ነው።

ጄምስ ፑል ስለዚህ ብዙ ያውቃል። የ47 ዓመቱ አትሌት ስፖንሰሮች ባለፈው ዓመት ስለውድድሩ አጠር ያለች ፊልም ሠርተዋል።

ይህ ውድድር በቴሌቪዥን የኢትዮጵያ አትሌቶች ኬንያውያንን ጥለው ሲገቡ እንደምናየው በአጭር ቁምጣ እና ካናቴራ የሚደረግ አይደለም።

ከሎስ አንጀለስ ተነስተው ወደ ላስ ቬጋስ ሲያቀኑ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛሉ። በዚህ መሃል አየሩ ይቀያየራል።

ፑል ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ያለማንም አጋዥ ሲሮጥ፤ ሞቃት ቦታ ሲገጥመው ካንቴራ ሲያጠልቅ፤ ብርዱ ሲያንዘፈዝፈው ደግሞ በካቦርት ተጀቡኖ ነበር።

ሯጮች ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ሲያዳርሱ የት እንደሚያድሩ፤ ምግብ የት እንደሚበሉ የሚነግራቸው የለም። መንገድ ላይ ምን እንደሚጠብቃቸው አያውቁም።

ዝነኛው ሯጭ በዚህኛው ዓመት ሩጫ ሲሳተፍ የርሞ የሚባል መንገድ ሲደርስ 120 ኪሎ ሜትር የሚሆን ቀጥታ የተዘረጋ አስፋልት ገጥሞታል።

“ስድስት ሰዓት ሮጠህ ቀና ስትል እዚያው መንገድ ላይ ነህ” ይላል ፑል። “ስድስት ሰዓት አክለህ ቀና ስትል ያው መንገድ ነው።”

እንግሊዛዊቷ ሯጭ ፓውላ ራድክሊፍ ማራቶን በምትሮጥ ጊዜ በእጇ 100 ትቆጥራለች። ስትጨርስ ትደግመዋለች።

“እኔ እንደእሷ መቶ መቶ ብቆጥር ስንት ሊሆን እንደሚችል አስበኸዋል” ይላል በፈገግታ።

ፑል ይህ ውድድር በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ይመኛል። አዘጋጁ አሬንድም እንዲሁ። ሰዎች ጥንካሬያቸውን የሚፈትኑበት እንዲሆን ነው ሕልሙ።

ፑል ለቢቢሲ ሹክ እንዳለው አዘጋጁ አሬንድ በሚቀጥለው ኅዳር ተመሳሳይ ቅርፅ ያለው ውድድር በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሌ ውስጥ ሊያዘጋጅ አቅዷል።

ሁሉም ነገር ከሎስ አንጀለስ ላስ ቬጋስ ከሚደረገው ውድድር ጋር ቢመሳሰልም፤ ሯጮች በጣም ፈታኙን የአታካማ በረሃ ማቋረጥ ይኖርባቸዋል።

አታካማ በረሃ በዓለማችን ካሉ እጅግ አደገኛ ሥፍራዎች አንዱ ነው።

ይህን በረሃ የሚያቋርጡ ቡድኖች ራሳቸውን ችለው፤ ከማንም እርዳታ ሳይጠብቁ፤ ንብረታቸውን በጭነት መኪና ይዘው መጓዝ ይኖርባቸዋል።

ይህ ዕቅድ ተሳክቶ ውድድሩ ወደ አታካማ ካቀና ጄምስ ፑል የመጀመሪያው ተመዝጋቢ ነው። ለምን?

“እኔ ሯጮች የለንደን ማራቶንን ደግመው ደጋግመው ሲሮጡ ይገርመኛል። ካለፈው ዓመት አምስት ሰከንድ ለማሻሻል ከመሮጥ በጣም አስደሳች የሆነ ውድድር ማድረግ አይሻልም?” ይላል።