የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው በኒውዮርክ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በቁጥጥር ሥር ያዋለቻቸው የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት እና ባለቤታቸው በኒውዮርክ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው።
ማዱሮ እና ባለቤታቸው በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እና በጦር መሣሪያ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ትራምፕ በቬንዙዌላ እና በኮሎምቢያ ላይ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አክለውም ሜክሲኮን "አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ" በመናገር ዝተዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አዲሷ የቬንዙዌላ መሪ ዴልሲ ሮድሪጌዝ "ትክክለኛውን ነገር ካላደረገች"፤ "ምናልባትም ከማዱሮ የበለጠ ትልቅ ዋጋ ልትከፍል ትችላለች" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ለአሜሪካው መጽሔት 'ዘ አትላንቲክ' ይህንን የተናገሩት፤ ከሥልጣናቸው የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በኒውዮርክ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ለዛሬ ሰኞ የተያዘላቸውን ቀጠሮ እየተጠባበቁ ባለበት ወቅት ነው።
ማዱሮን በዕፅ ዝውውር እና በጦር መሳሪያ ወንጀሎች የምትከስሰው አሜሪካ፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት "የናርኮሽብርተኛ" አገዛዝን ይመሩ ነበር ትላለች። ማዱሮ ግን እነዚህን ክሶች ውድቅ አድርገዋል።
ቅዳሜ ዕለት በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ማዱሮ እና ባለቤታቸው ተይዘው ወደ አሜሪካ ተወስደዋል።
ከዚህ ክስተት በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጋር ጦርነት ውስጥ አይደለችም ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። አንዳንድ የዴሞክራት የኮንግረስ አባላት ግን ድርጊቱን "የጦርነት አዋጅ" ሲሉ ጠርተውታል።
እሁድ ዕለት ከዘ አትላንቲክ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ትራምፕ፤ የቬንዙዌላን የመሪነት ሥልጣን ስለተረከቡት ሮድሪጌዝ ሲናገሩ፤ "ትክክለኛውን ነገር ካላደረገች፣ በጣም ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች፤ ምናልባትም ከማዱሮ የበለጠ" ብለዋል።
"የስርዓት ለውጥ፣ ምንም ብለህ ልትጠራው ትችላለህ፤ አሁን ካለው ሁኔታ የተሻለ ነው። ከዚህ የከፋ ሊሆን አይችልም" ሲሉ መናገራቸውን መጽሔቱ ዘግቧል።
ትራምፕ፤ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ከሥልጣናቸው ያነሱበት ኦፕሬሽን ከተፈጸመ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ "ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተገቢ እና አመዛዛኝ የሥልጣን ሽግግር" እስከሚደረግ ድረስ አሜሪካ አገሪቱን "ትመራለች" ብለው ነበር።
የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ወደ ቬንዙዌላ ገብተው መሠረተ ልማቱን እንደሚጠግኑ እና "ለአገሪቱ ገንዘብ መስራት እንደሚጀምሩም" ሲናገሩ ተደምጠዋል። ምንም እንኳ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ይህንን ቢሉም፤ አሁንም አገሪቱን እየተቆጣጠሩ ያሉትን የማዱሮ አጋሮች ናቸው።
የኩባ መንግሥት እንደገለጸው፤ የአሜሪካ ኃይሎች ማዱሮን እና ባለቤታቸውን ለመያዝ በከፈቱት ጥቃት 32 "ጀግና ኩባውያን ተዋጊዎች" ተገድለዋል። የረጅም ጊዜ የማዱሮ ሶሻሊስት አጋር የሆነችው ኩባ የሁለት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አውጃለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ፤ እሁድ ጠዋት በሰጧቸው በርካታ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልሶች የአሜሪካ በቬንዙዌላ የፈጸመችውን ወታደራዊ እርምጃ ተከላክለዋል። እርምጃው ዋሽንግተን ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ጋር ጦርነት ውስጥ ነች ማለት እንዳልሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሩቢዮ፤ በኤንቢሲ ቴሌቪዥን ለሚተላለፈው 'ሚት ዘ ፕሬስ' በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ "እኛ ጦርነት እያደረግን ያለነው ከእፅ አዘዋዋሪ ድርጅቶች ጋር ነው። ይህ ከቬንዙዌላ ጋር እተደረገ ያለ ጦርነት አይደለም" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ፤ ቬንዙዌላ "ትክክለኛ ውሳኔዎችን ካለስተላለፈች"፤ አሜሪካ "ፍላጎቶቻችን መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ በርካታ የማስገደጃ መንገዶችን እንጠቀማለን" ብለዋል።
ከእነዚህ መንገዶች አንዱ አሜሪካ በቬንዙዌላ ነዳጅ ላይ የጣለችው "እገዳ" እንደሆነም ጠቁመዋል። "ሁሉንም ነገር በድርጊታቸው እንመዝናለን፤ ምን እንደሚያደርጉም እናያለን" ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ በቬንዙዌላ ጎረቤት ኮሎምቢያ ላይም ዝተዋል። በኮሎምቢያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ የሚወሰድበት አጋጣሚ መኖሩን ውድቅ ያላደረጉት ትራምፕ፤ ይህ ዓይነቱ እርምጃ "እኔ ጥሩ ይመስለኛል" ብለዋል። የኮሎምቢያውን ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮንም "በሽተኛ ሰው" ሲሉ ዘልፈዋል።
"ኮሎምቢያም በጣም ታማለች፤ የምትመራውም ኮኬይን ማምረት እና በአሜሪካ መሸጥ በሚወድ በሽተኛ ሰው ነው፤ ይህንንም ለረጅም ጊዜ አያደርገውም" ብለዋል።















