ኤርትራ "ትርጉም የለሽ ውዝግብ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት የለኝም" ስትል የኢትዮጵያን ክስ አጣጣለች

የፎቶው ባለመብት, MOI Eritrea/Office of the prime minister - ethiopia
ኤርትራ የኢትዮጵያ ያቀረበችባትን ክስ "ትርጉም የለሽ" በማለት በዚህ ውዝግብ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት እንደሌላት በማስታወቂያ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው አጭር መግለጫ አስታወቀች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት የተወሰኑ አካባቢዎችን ተቆጣጥራለች እንዲሁም ታጣቂዎችን ትደግፋለች ሲል ቅዳሜ ዕለት በጻፈው ደብዳቤ ክስ እና የድርድር ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ኤርትራ ለዚህ ክስ በሰጠችው ምላሽ "ትርጉም የለሽ ውዝግብ ውስጥ ነዳጅ ለመጨመር እና ሁኔታውን ለማቀጣጠል ተነሳሽነቱም ሆነ ፍላጎቱ" እንደሌለው በመግለጽ አጣጥለዋለች።
የወደፊት አጀንዳዎችን ለማስፈጸም የቀረበ የውሸት ውንጀላዎች በሚል ርዕስ በወጣው በዚህ የኤርትራ መግለጫ የኢትዮጵያን መንግሥት ክሶችን "ሐሰት እና የፈጠራ" ሲል ውድቅ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቲት 30/2018 ዓ.ም. ለኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቸው ሉዓላዊ ግዛቶቹ እንዲወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንዲሆን ጠይቋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ሰሜን ምሥራቅ ድንበር ከዚህ ቀደም ከተቆጣጠሩት አካባቢ የበለጠ ዘልቀው እንደገቡ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።
በድንበር አካባቢዎች የነበሩ የባለፉት ጥቂት ቀናት እንቅስቃሴዎች፤ የኤርትራ መንግሥት በሁለቱ ሀገራት መካከል የበረታውን ውጥረት የበለጠ የሚያባብስ መንገድ እንደመረጠ እንደሚጠቁሙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ ደብዳቤው ላይ ሁለቱ አገራት በሚያዋስናቸው አካባቢዎች የኤርትራ መንግሥት በስም ላልተጠቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች "ቀጥታ የቁሳቁስ ድጋፍ እና እርዳታ" እንደሚያቀርብ በመጥቀስ ወንጅሏል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ላይ በሰጠው አጭር መግለጫ ላይ ለኢትዮጵያ መንግሥት ክስ እና ውንጀላ "ሐሰት እና ፈጠራ" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የማስታወቂያ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ "በድምጸቱ እና በይዘቱ፣ ከኋላው ባለው ምክንያት እና ዓላማው አስገራሚ ነው" ሲል የደብዳቤውን ይዘት ነቅፏል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ "በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በኤርትራ ላይ ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየው የጥላቻ ዘመቻ አካሄድ እና አዙሪት ውስጥ ሌላ አሳዛኝ ተግባር ነው" ሲል የኢትዮጵያ መንግሥትን ደብዳቤ ይዘት ኮንኗል።
የኤርትራ መንግሥት በዚህ መግለጫው ላይ ከዚሀ ቀደም ያለውን በማስታወስ "የኤርትራ መንግሥት ትርጉም የለሽ ውዝግብ ውስጥ ነዳጅ ለመጨመር እና ሁኔታውን ለማቀጣጠል ተነሳሽነቱም ሆነ ፍላጎቱ የለውም" ብሏል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቲት 30/2018 ዓ.ም. ለኤርትራ አቻው በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በመጣስ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ገልጿል።
ደብዳቤው የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር ከግዛቱ ለቅቆ እንዲወጣ መጠየቁን አስታውሶ፤ ይህ ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ "የባሕር አገልግሎት ጉዳዮችን እና በአሰብ ወደብ በኩል የባሕር መዳረሻን ጉዳይ ጨምሮ ሁሉንም የጋራ ጥቅም ጉዳዮችን ለመፍታት በቅን ልቦና በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ" መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የኤርትራን መንግሥት ሉዓላዊነቷን እና ድንበሯን ከመጣስ እንድትቆጠብ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉን ቢገልጽም ጥሰቶቹ መቼ እንደተከሰቱ በግልጽ አላመለከተም።
የኤርትራ ጦር በትግራይ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፎ የህወሓት ኃይሎችን ተዋግቷል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከዚህቀ ደም በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ በአልጀርስ ስምምነት መሠረት በተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ላይ የተቀመጡ የድንበር ማካለሎች ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል።
ኢትዮጵያ የኤርትራ ወታደሮች ሉዓላዊ ግዛቷን ጥሰው በኃይል የተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች መኖራቸውን ስትገልጽ ይህ የመጀመረያዋ አይደለም።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው የኤርትራ ጦር አባላት በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያሉ ስፍራዎችን ተቆጥጥረው እንደሚገኙ እና "የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድንበር አካባቢዎች እንደሚፈጸሙ ሪፖርቶች መውጣታቸውን" ቀጥለዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።
በመስከረም ወር መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሰሩ ነው ሲል ከስሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚያቀርበው ክስ እና ውንጀላ የኤርትራ መንግሥት ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ የኤርትራ መንግሥት ከህወሓት እና ከፋኖ ጋር እየሠራ ነው ስትል መወንጀሏም ይታወሳል።















