በአሜሪካ መንግሥት ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ደቡብ ኮሪያውያን ሠራተኞች ወደ አገራቸው ተሸኙ

የኮሪያ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ኮሪያ አውሮፕላን ሐሙስ ዕለት እኩለ ቀን ላይ ከሃርትፊልድ-ጃክሰን አትላንታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሠራተኞቹን ጭኖ ተነስቷል

ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት በሃዩንዳይ ፋብሪካ ላይ የኢሚግሬሽን ኦፊሰሮች በፈጸሙት ድንገተኛ ወረራ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከ300 በላይ ደቡብ ኮሪያውያን አርብ ወደ አገራቸው ይገባሉ ተባለ።

ሠራተኞቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እና የሃዩንዳይ ዋና ስራ አስፈፃሚ እስሩ በኢንቨስትመንት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ጠቅሰው ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።

ሠራተኞቹን እና ከፋብሪካው በቁጥጥር ስር የዋሉ 14 ኮሪያውያን ያልሆኑ ሠራተኞችን ያሳፈረው የደቡብ ኮሪያ አውሮፕላን ሐሙስ ዕለት እኩለ ቀን ላይ ከሃርትፊልድ-ጃክሰን አትላንታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቷል።

አንድ የደቡብ ኮሪያ ዜጋ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት በአሜሪካ መቆየትን መርጧል ተብሏል።

አውሮፕላኑ አርብ ከሰአት ኢንቼዮን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዋይት ሐውስ በተሰጠ መመሪያ ምክንያት ጉዞው ከአንድ ቀን በላይ መዘግየቱን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሠራተኞቹ አሜሪካ ውስጥ ቆይተው መሥራት እና አሜሪካውያንን ለማሠልጠን ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆናቸውን ለመጠየቅ እንዲዘገዩ ማዘዛቸውን የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጥ ዋይት ሐውስን አነጋግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሊ በተጨማሪም የሠራተኞቹን እስር ተከትሎ ኩባንያዎች በአሜሪካ ኢንቨስት ለማድረግ "በጣም ያመነታሉ" ብለዋል።

"ሁኔታው በጣም ግራ የሚያጋባ ነው" ሲሉ የኮሪያ ኩባንያዎች የባህር ማዶ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ሠራተኞቻቸውን መላክ የተለመደ አሰራር መሆኑን ጠቁመዋል።

"ይህ ከአሁን በኋላ የማይፈቀድ ከሆነ በአሜሪካ ውስጥ የማምረቻ ተቋማትን ማቋቋም የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል ... ኩባንያዎች ይህን ማድረግ ጠቃሚ ነው ወይ ብለው እንዲጠይቁ ያደርጋል" ብለዋል።

ሴኡል ለደቡብ ኮሪያ ሠራተኞች ሊኖር ስለሚችሉ የቪዛ አማራጮች ላይ ከዋሽንግተን ጋር እየተደራደረች ነው።

ፕሬዚዳንቱ "ይህ ማለት [ከፍተኛ] ኮታዎች እንዲኖር ማድረግ ወይም አዲስ የቪዛ ምድቦችን መፍጠር ነው" ብለዋል ።

አርብ ዕለት የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ኮንግረስ ለኮሪያ ኩባንያዎች የሚሰጥ አዲስ ቪዛን እንዲደግፍ መጠየቁን ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት ከአሜሪካ ሴናተሮች ጋር በዋሽንግተን ባደረጉት ውይይት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ዩን በደቡብ ኮሪያውያን እስር ላይ ያላቸውን ስጋት በድጋሚ መናገራቸውን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀዩንዳይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆሴ ሙኖዝ እስሩ የፋብሪካውን መክፈቻ ያዘገየዋል ብለዋል።

ሚስተር ሙኖዝ ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት የሠራተኞቹ እስር ቢያንስ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት መዘግየትን ይፈጥራል ምክንያቱም አሁን እነዚህ ሁሉ ሰዎች መመለስ ይፈልጋሉ።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባለስልጣናት በጆርጂያ ከሚገኙት ግዙፍ የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነው የባትሪ ፋብሪካ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ 475 ሰዎችን፣ ከ300 በላይ የሚሆኑት የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ናቸው፣ በቁጥጥር ስር አውለዋል።

ፋብሪካውን ከሃዩንዳይ ጋር የሚያንቀሳቅሰው ኤልጂ ኢነርጂ ሶሉሽን እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ብዙዎቹ ሠራተኞቻቸው የተለያዩ ቪዛዎች ነበሯቸው ወይም በቪዛ ቆይታ ፕሮግራም ውስጥ ነበሩ።

የፋብሪካው ሠራተኛ በጥቃቱ ወቅት ስለተፈጠረው ድንጋጤ እና ግራ መጋባት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከታሰሩት አብዛኛዎቹ ሠራተኞች በቦታው ላይ የማምረቻ መስመሮችን የሚዘረጉ መካኒኮች መሆናቸውን እና በተቋራጭ ድርጅት ተቀጥረው እንደሚሠሩ ሠራተኛው ተናግሯል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ወረራውን "አስደንጋጭ" ሲሉ ገልጸውታል፤ ዶንግ-ኤ ኢልቦ የተሰኘው ጋዜጣ "በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ የንግድ ድርጅቶቻችን እንቅስቃሴ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሊቸልስባቸው ይችላል" ሲል አስጠንቅቋል።

የዮንሃፕ የዜና አገልግሎት በበኩሉ ሁለቱ ሀገራት "በወዳጅነታቸው ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመጠገን እንዲተባበሩ" አሳስቧል።

የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ፤ በዋሽንግተን የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ላይ በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለማፍሰስ ቃል ገብታለች።

ይህንን ቃል የገባችበት አንዱ ምክያትን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፍ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በከፊል ለመከላከል ነው።

የሁለቱ አገራት መንግሥታት ሚስጥራዊ የንግድ ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት የተካሄደው የፋብሪካው ዘመቻ፤ ሴኡል ውስጥ ስጋት ፈጥሯል።