የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ትንቅንቅ. . . የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ታውቋል - ሊቨርፑል። ከሊጉ የሚወርዱ ሦስት ቡድኖችም ተረጋግጠዋል - ኢፕስዊች፣ ሌስተር እና ሳውዝሃምፐተን።

በቀጣይ በአውሮፓ የተለያዩ ውድድሮች የሚሳተፉ ቡድኖች ይለያሉ።

የሊጉ ቀጣይ ጨዋታዎች አርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ እንዲከናወኑ መርሃ ግብር ወጥቶላቸዋል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የጨዋታዎቹን ውጤት እንደሚከተለው ገምቷል።

አርብ

ማንቸስተር ሲቲ ከዎልቭስ

ዎልቭሶች ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፉ በኋላ ያለምንም ፍርሃት የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል።

ሲቲም ጠንካራ ተከላካይ መስመር እንዳለው እና ውጤታማ መሆኑን ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አሸንፎ አሳይቷል።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ጨዋታውን ቢቆጣጠርም ዎልቭስን ከጨዋታ ውጪ አያደርግም።

ግምት፡ 2 – 1

ቅዳሜ

አስቶን ቪላ ከ ፉልሃም

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቪላ ከሻምፒዮንስ ሊግ እና ከኤፍኤ ዋንጫ ውጪ ሆኗል። ቀሪው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለመጨረስ መፎካከር ነው።

ቪላ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል።

ፉልሃም ደግሞ ለመገመት አስቸጋሪ ቡድን ነው።

ቪላ ጎል የሚገባበት ቢሆንም ጎሎችን ለማስቆጠር አይቸገርም።

ግምት፡ 3 – 1

ኤቨርተን ከ ኢፕስዊች ታውን

ኢፕስዊች መውረዱን ቢያረጋግጥም ሙሉ ለሙሉ እጅ ይሰጣል ማለት አይደለም።

በራስ መተማመናቸው በውድድር ዘመኑ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ይህንን ጨዋታ አያሸንፉም።

በአርሰናል እና በኒውካስል ከባድ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ኤቨርተን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተዳክሞ ታይቷል።

አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ከሚጠበቅባቸው በላይ ውጤታማ ሆነዋል።

ግምት፡ 2 – 0

ሌስተር ከ ሳውዝሃምፐተን

ሌስተር ደካማ ሲሆን ሳውዝሃምፕተን ደግሞ ከዚህ የነሳ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አጥቂው ጂሚ ቫርዲ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከቡድኑ የሚለያይ ሲሆን፣ ይህ የስንብት ጨዋታው ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ሲጫወቱ ሌስተር 2 ለምንም ከመመራት ተነስቶ 3 ለ 2 አሸንፏል። ቫርኢም ጎል አስቆጥሯል።

ግምት፡ 1 – 0

አርሰናል ከ በርንመዝ

በርንመዝ ጠንካራ መሆኑን ማሳየው በመጀመሪያው ዙር አርሰናልን ማሸነፉ ነው። ሚኬል አርቴታ ተጫዋቾችን ካሳረፉ ይበልጥ የከብዳቸዋል።

አርቴታ ለሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ተጫዋቾቹ በጥሩ ብቃት ላይ ሆነው እንዲገኙ በማጫወት እና እንዳይጎዱ በመፍራት መካከል ይወድቃሉ።

በርንመዝ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን አርሰናልን ለማሸነፍም ብቃት አለው።

ይህ የሚወሰነው በአርሰናል አሰላለፍ ነው።

ግምት፡ 1 – 1

እሐድ

ብሬንትፎርድ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ጋር ያለበትን የዩሮፓ ሊግ የመልስ ጨዋታ ከግምት በማስገባት ተጫዋቾችን እንደሚቀይር ይጠበቃል።

የሩበን አሞሪም ቡድን ባለቀ ሰዓት በርንመዝ ጋር አቻ ቢለያዩም ብሬንትፎርድ ግን ይህንን ዕድል አይሰጣቸውም።

ብሬትፎርድ ሲያጠቃ አደገኛ ነው።

ግምት፡ 2 – 0

ብራይተን ከ ኒውካስል

ብራይተን ባለፈው ሳምንት በካርሎስ ባሌቦ ድንቅ ጎል ወደ ማሸነፍ ተመልሷል።

ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር ኒውካስልን ቢያሸንፍም በወቅቱ ኒውካስል ወደ ጥሩ አቋሙ አልደረሰም ነበር።

ኒውካስል ይህንን ጨዋታ አሸንፎ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ለመያዝ ይፈልጋሉ።

ግምት፡ 2 – 2

ዌስት ሃም ከ ቶተንሃም

ይህ ጨዋታ በደካማ ቡድኖች መካከል እንደሚደረግ የሚያሳየው በ17ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖች መሆናቸው ነው።

ቶተንሃም ትኩረቱ በዩሮፓ ሊግ ላይ በመሆኑ ዌስት ሃም ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ይጫወታል።

ግራሃም ፖተር ዌስት ሃምን ከያዙ በኋላ በሚጠበቀው ልክ ለውጥ አላመጡም።

ስፐረስ ተጫዋቾችን ስለሚያሳርፍ ይህ ለዌስት ሃም ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል።

ግምት፡ 2 – 1

ቼልሲ ከ ሊቨርፑል

ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ፈንጠዝያው በመቀጠሉ የትኞቹ ተጫዋቾች ይሰለፋሉ የሚለው ወሳኝ ይሆናል።

ቼልሲ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ተስፋ የሚሰጣቸውን ውጤት ቢያስመዘግቡም አሁንም አሳማኝ አይደሉም።

ይህ የሚፈትናቸው ጨዋታ ባይሆንም ሊቨርፑል ግን በቀላሉ እጅ አይሰጥም።

ግምት፡ 1 – 2

ሰኞ

ክሪስታል ፓላስ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ክሪስታል ፓላስ ለኤፍኤ ዋንጫ ፍጻሜ መድረሱን ተከትሎ በጥሩ የሞራል መነቃቃት ላይ ሲሆን ፎረስት ደግሞ ሐሙስ ዕለት በብሬንትፎርድ ተሸንፏል።

ፎረስት በተደጋጋሚ እንዳሳየው በጥሩ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት መጫወት ይርበታል።

በዚህ ጨዋታ ፎረስት ነጥብ የሚጥል ይመስላል።

ግምት፡ 1 – 1