የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ "ለፍትሐዊ ምርጫ ምቹ መደላድል ባለመኖሩ" በዕጩነት እንደማይቀርቡ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives of FDRE
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ ጠንካራ ጥያቄዎች እና ትችቶችን በመሰንዘር የሚታወቁት የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በመጪው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላለመወዳደር መወሰናቸውን አስታወቁ።
ዶ/ር ደሳለኝ እዚህ ውሳኔ ላይ ካደረሷቸው ምክንያቶች አንዱ "ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ" እንደሆነ ገልጸዋል።
በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወክለው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ይህንን ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ዛሬ አርብ ጥር 29/2018 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው።
ዶ/ር ደሳለኝ በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የባሕር ዳር ከተማን ወክለው ከተመረጠ በኋላ ከ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ በአገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውስጥ አባል ሆነው ቆይተዋል።
የምክር ቤት አባሉ፤ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በዕጩነት ስለመመዝገብ አለመመዝገባቸው ከመራጮች፣ ከደጋፊዎች እና ከመገናኛ ብዙኃን "በተደጋጋሚ" ጥያቄ ሲቀርብላቸው መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ጥር 1 ቀን የጀመረው የዕጩዎች ምዝገባ በመጪው እሁድ የካቲት 1 ቀን ይጠናቀቃል።
ቀድሞ በሊቀ መንበርነት ጭምር ከመሩት አብን የለቀቁት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ሌሎች ፓርቲዎችን ወክለው በመጪው ምርጫ እንዲወዳደሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበር አመልክተዋል።
"አንዳንድ ፓርቲዎችም ባሕር ዳርም ሆነ አዲስ አበባ በፈለግሁበት ቦታ በዕጩነት እንድቀርብ ዕድሉን ሰጥተውኝ ነበር" ብለዋል።
በግል ዕጩነት ቀርቦ የመወዳደር ሀሳብንም "በጥልቀት" እንዳሰቡበት አስረድተዋል። "ሆኖም ግን በመጪው 7ኛው ዙር ምርጫ ራሴን በዕጩነት ላለማቅረብ መወሰኔን ለሕዝቤ ይፋ ማድረግ እፈልጋለሁ" ሲሉ ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት በአሁኑ ወቅት "በሀገራችን ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ" እንደሆነ በጽሁፋቸው ገልጸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁለት ጉዳዮችን በምክንያትነት አንስተዋል።
በቀዳሚነት የጠቀሱት "ነፃ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩ" ነው።
በተጨማሪም እስካሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ "በፓርላማ ውስጥ ተጨማሪ 5 ዓመታትን በመቆየቴ ለሕዝቤ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑንም ተረድቻለሁ" ብለዋል።
በመጪው ሰኔ የሚያበቃው የአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን "እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴነት" ተግባራቸውን አከናውነው የአገልግሎት ጊዜያቸውን እንደሚያጠናቅቁ አስረድተዋል።
አክለውም "ወደፊት ሀገሬን እና ሕዝቤን እንዴት ለማገለግል እንደምፈልግ የማሳውቅ ይሆናል" ብለዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ እስካሁን በነበራቸው ቆይታ "ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ፍቅር፣ አክብሮት እና ጽኑ እምነት" አሳይቶኛል ላሏቸው "የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያውያን ወገኖች" ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
"ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በኩሩው የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ተመርጨ፣ እናንተን ወክዬ፣ ለሕዝባችን ሀቀኛ ድምፅ በመሆን ለማገልገል በመቻሌ ታላቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።















