ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምሥራቅ ሸዋ ወለንጪቲ ከተማ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸው ተነገረ
በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ከተማ ማክሰኞ ምሽት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በንፁሃን ሰዎች ላይ የሕይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተነገረ።
ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የቦሰት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር መሐመድ ሱፋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ግንቦት 08/2015 ዓ.ም. ማክሰኞ ምሽት ላይ በወለንጪቲ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደተፈጸመም ፖሊስ አስታውቋል።
የፖሊስ አዛዡ ኮማንደር መሐመድ ሱፋ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ማክሰኞ አመሻሽ፣ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ወደ ወለንጪቲ ከተማ ዘልቀው ለመግባት ባደረጉት ሙከራ ነው በንጹሃን ሰዎች ላይ ሞትና ጉዳትን ያደረሱት።
“በዚህ በእኛ ቦሰት ወረዳ ውስጥ ኦነግ ሸኔ የሚባለው ኃይል በሰፊው ይንቀሳቀሳል። በአብዛኛው ጊዜ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ይሞክራሉ። ከተማዋ ላይም ጥቃት ለማድረስ ሲጥሩ ነበር” ብለዋል የፖሊስ አዛዡ።
ታጣቂ ቡድን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ በበርካታ ቁጥር ወደ ከተማዋ ለመግባት ሙከራ ማድረጉን እና በአካበቢው የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በጥምረት ጥቃቱን ለመከላከል እንደቻሉ ኮማንደር መሐመድ ሱፋ ገልጸዋል።
አክለውም በከተማዋ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተሰማርተው ከነበሩት ታጣቂዎች ወገን ስድስት መሞታቸውን እና አራት ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።
በምሥራቅ ሸዋ ስለተሞከረው ጥቃት፣ ስለተገደሉ እና ስለተያዙ ተዋጊዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አስካሁን ያለው ነገር የለም።
በታጣቂዎች በወለንጪቲ ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት እና የተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ከ30 ደቂቃ በላይ እንዳልቆየ የገለጹት ኮማንደር መሐመድ፣ የታጣቂዎቹ የጥቃት ዓላማ “እስረኞችን ለማስፈታት ነበር” ብለዋል።
“በፖሊስ ጽህፈት ቤት ውስጥ ልዩ ልዩ እስረኞች አሉ። ከእነርሱም ወገን ተይዘው የታሰሩ አሉ። እነዚህን ለማስፈታት ነበር ወደ ፖሊስ ጣቢያው የመጡት።”
ነገር ግን ታጣቂዎቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያው መግባት እንዳልቻሉ እና በአቅራቢያው ያለው የአገር መከላከያ ሠራዊትም ደርሶ እርምጃ በመውሰዱ “የተወሰኑት ሲገደሉ እና ሲቆስሉ የቀሩት ደግሞ የያዙትን በመጣል ወደ ጫካ ሸሽተዋል” ብለዋል አዛዡ።
የወለንጪቲ ከተማ በአሁኑ ሰዓት [ረቡዕ ረፋድ ላይ] በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን የተናገሩት ኮማንደሩ፣ ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚያቋርጠው ዋና መንገድም መደበኛ የትራንስፖርት አግልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ባለፈው እሁድ ግንቦት 06/2015 ዓ.ም ያልታወቁ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ከፍተው አራት የፖሊስ ባልደረቦችን መግደላቸው ተሰምቷል።
በቢሾፍቱ ከተማ ታጣቂዎች እሁድ እኩለ ሌሊት ላይ ተኩስ መክፈታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከሰው ሕይወት ባሻገር በአካባቢው የነበሩ መኪኖችም በጥይት መደብደባቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በታንዛንያ፣ ዛንዚባር ተገናኝተው ለዘጠኝ ቀን የሰላም ውይይት ሲያደርጉ ቢቆዩም ያለስምምነት መለያየታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና ጥቃቶች መቀጠላቸው ይሰማል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር ከተደረገ በኋላ መንግሥት የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን በመግለጽ ክስ አቅርቧል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በዚህ መግለጫው ላይ የሰላም ንግግሩ ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች “መጠነ ሰፊ ጥቃት” ከፍተዋል ብሏል።
መግለጫው አክሎም “ይህ በሰላም ንግግሩ ወቅት ከግጭት መራቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ከተደረሰበት መግባባት በተቃራኒው የቆመ ነው” ሲል ከሷል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው የመጀመሪያ ዙር የሰላም ንግግር ማብቃቱን ተከትሎ በተናጠል ባወጡት መግለጫ ላይ ዳግም ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ይህንን የታጣቂው ቡድን ክስ ተከትሎ ከመከላከያ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይንም ሸኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ መሆኑ ይታወሳል።