በቱርክ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅራቢያ በተፈፀመ “የሽብር ጥቃት” ጉዳት ደረሰ

በቱርክ መዲና አንካራ በሚገኘው የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅራቢያ በተፈፀመ “የሽብር ጥቃት” ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

ሚኒስትር አሊ የርሊካያ እንዳሉት ዛሬ እሑድ ረፋድ 3: 30 ሁለት ጥቃት አድራሾች በንግድ ተሽከርካሪ ወደ አካባቢው በማምራት ጥቃቱን አድርሰዋል።

አንደኛው ጥቃት አድራሽ በሚኒስቴሩ ሕንጻ ፊት ለፊት ራሱን ያጠፋ ሲሆን ሌላኛው መገደሉን ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ፍንዳታው ያጋጠመው ምክር ቤቱ ከሦስት ወራት እረፍት በኋላ ስብሰባውን ከማካሄዱ ከሰዓታት በፊት ነው።

ሚኒስትር የርሊካያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍም “የመጨረሻው ሽብርተኛ እስከሚጠፋ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል” ብለዋል።

ስለ ፍንዳታው ቀድሞ የዘገበው የአገሪቷ ሚዲያ በአካባቢው የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የገለጸ ሲሆን የድንገተኛ አገልግሎት ሠጪ አካላትም ወደ ሥፍራው እየሄዱ ነው ብሎ ነበር።

የእሳትና ድንገተኛ አገልግሎት እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ቡድንም በፍጥነት ወደ ሥፍራው እንዲሄዱ ወደ አካባቢው የሚወስዱ መንገዶች ለሌሎች ተሽከርካሪዎች ዝግ መደረጋቸውም ተገልጿል።

ጥቃቱን የፈፀሙት እነማን እንደሆኑ ግልጽ አይደለም። እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካልም የለም።

በቱርክ የሽብር ጥቃት መፈፀሙ ሲገለጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ኢንስታንቡል መሃል ከተማ በተፈጸመ “የሽብር” ጥቃት 6 ሰዎች መገደላቸውን እና 81 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ለዚህ ፍንዳታ የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲን (ፒኬኬ) ተጠያቂ አድርገዋል።

ፒኬኬ የተሰኘው የሚሊሻ ቡድን ከቱርክ ግዛት ላይ ነጻ የኩርድ አስተዳደር ለመመስረት ይፋለማል።

ቱርክ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ይህን ቡድን አሸባሪ ሲሉ ፈርጀውታል።