ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአሜሪካ ሰማይ ተመትተው የወደቁት ሦስት ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት ስጋት አይደሉም ተባለ
በአሜሪካ ሰማይ ሲበሩ የነበሩና ተመትተው የተጣሉት ሦስቱ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ ቁሶች ከቻይና ስለላ ጋር ስለመገናኘታቸው መረጃ የለም ሲል ዋይት ሃውስ ገለጸ።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪብሪ ምንነታቸው ያልታወቁት በራሪ አካላት ከንግድ ወይም ከምርምር ጋር ሊያያዙ የሚችሉ መሆናቸውንና አስጊ እንዳልሆኑ ጥቅሰዋል።
የአሜሪካ እና የካናዳ ባለስልጣናት ተመትተው የወደቁትን ሦስት በራሪ አካለት ስብርባሪዎች የት እንዳሉ አያውቁም ወይም አላገኙም።
ቀደም ብላ ቻይና አሜሪካ ባልተጣራ ጉዳይ ላይ የተጋነነ ምላሽ ስትሰጥ ነበር ስትል ወቅሳለች።
ቻይና በአሜሪካ ተመትቶ የወደቀባትን ፊኛ የአየር ሁኔታ ቅኝት የሚሰራና በንፋስ ተገፍቶ አቅጣጨውን የሳተ እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ትናንትት በሰጡት ዕለታዊ መግልጫ በአላስካ፣ ሚቺገንና ካናዳ ተመትተው የተጣሉት ሦስቱ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪዎች ስብርባሪ እስካልተገኘ ድረስ ዓላማቸውን እና መነሻቸው ለመለየት አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል።
“እነዚህ ሶስት በራሪ ቁሶች የቻይና የስለላ መርሃግብር አካል ስለመሆናቸው የሚያመላክት ወይም የሚጠቁም አንዳችም ነገር አላገኘንም። አሊያም ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን የስለላ ተግባር ውስጥ ሰለመሆናቸው የሚያስረዳ ነገር የለም” ያሉት ቃል አቀባዩ “ከንግድ ወይም ምርምር ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ ስለዚህ አስጊ አይደሉም” ሲሉ አክለዋል።
ሆኖም እስካሁን ድረስ የትኛውም ኩባንያ፣ ድርጀት ወይም መንገሥት ቁሶቹ የኔ ናቸው አላለም።
በሁሮን ሃይቅ በራሪ አካሉን መቶ ለመጣል አሜሪካ የተኮሰችው ሚሳኤል ኢላማውን ስቶ ባልታወቀ ቦታ ላይ መውደቁን የአሜሪካ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል። ሆኖም በሁለተኛው ኢላማውን አግኝቶ በራሪውን አካል መትቶ ጥሏል።
ባለስልጣናቱ የአሜሪካ የአየር ክልል አሁን ጸድቷል ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ የሰጠችወን ምላሽ ተችተዋል።
ቃል አቀባዩ ዋንግ ዌንቢን ትላንት በሰጡት መግለጫ “በአሜሪካ በርካታ ሰዎች ‘እንዲ ከፍተኛ ውጪ የሚያስወጣ እርምጃ መውሰድ ለአሜሪካና ለግብር ከፋዩ ዜጋ ምን ጥቅም ያስገኛል’ ሲሉ እየጠየቁ ነው” ብለዋል።