ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና ዘረ መላቸው የተለወጡ ምርቶችን የመጠቀም ጉዳይ
ከጥቂት ዓመታት በፊት በዘረ መል የተሻሻሉ ላሞች የሰው ወተት ማምረት ቻሉ የሚል አስገራሚ ዜና ወጣ።
በቻይና የግብርና ዩኒቨርስቲ የሚመራ ቡድን የሰውን ልጅ ጂን በ300 ላሞች ውስጥ በማስገባት የሰው ወተት ስኬታማ በሆነ መልኩ ማምረት ቻለ ተባለ።
ከእናት የሚገኘው ወተት የህፃናትን በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግ እና የኢንፌክሽን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚረዱ ጠቃሚ ይዘቶች ስላለው ይህንን በላም ወተት ውስጥ እንዲገኝ ለማድረግ የታለመው።
ይህ አስገራሚ ዜና ቢመስልም የሰው ልጅ ምግብ እና የሳይንስን ልኅቀት ትስስርን ከሚያሳየው ጂኤምኦ (የዘረ መል ለውጥ) ጋር በተያያዘ በርካታ ውዝግቦች ተነስተዋል።
ለአስርት ዓመታትም የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪዎች፣ ኩባንያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሸማቾች ጥበቃ ማኅበር፣ የዓለም ንግድ ድርጅቶችንም በማከራከር እና በማወዛገብ ቀጥሏል።
ለመሆኑ ግን ጂኤምኦ (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም) ወይም ሰው ሠራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው ሕያዋን ሲባል ምን ማለት ነው?
‘ጂኤምኦ’ ማለት የጄኔቲክ ምኅንድስናን በመጠቀም ዘረመሉ (ዲኤንኤ) የተቀየረ ማንኛውንም ሕያዋን ማለት ነው።
ይህም ተክሎችን፣ እንስሳትን (ሰዎችን ጨምሮ) ወይም ባክቴሪያዎችን ያጠቃልላል።
ሆኖም ከትርጉሙም ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጎራ ያሉ አካላት የሚሰጧቸው ገለጻዎች ምን ያህል ውስብስብ ሁነቶች የተካተቱበት እንደሆነ አመልካች ነው።
ሰዎች በተፈጥሮ ላይ ጣልቃ የሚገቡበት ምግብ ነው? ባዕድ ዲኤንኤ ( ዘረ መል) በማካተት የተፈጠሩ ናቸው? ጂናቸው የተስተካከለ (ጂን ኤዲትድ) የሚባሉትስ ምግቦች፣ ከማዳቀል ጋር በተያያዘ የጂንን መዋቅር የሚቀየርበት ሂደት ነው?
ሳይንሱ ምንድን ነው የሚያደርገው?
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ተመራማሪ እና የምግብ ሳይንስ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ታደሠ ፍቅሬ፣ “ሰው ሠራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው ሕያዋን ዘረ መላቸው የተሻሻለ እንስሳት ወይንም የዕጽዋት ዝርያዎች ናቸው” ይላሉ።
ዘረ መላቸው ተፈላጊ የሆኑ ባህሪያትን ለማጉላት፣ ተፈላጊ ያልሆኑትን ደግሞ በመቀነስ የሚከናወኑ መሆኑንም ያስረዳሉ።
“የተወሰኑ ዘረ መሎችን በመጨመር፣ በመቀነስ ወይም በማሻሻል ዝርያ የማሻሻል እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የምንጠቀምበት፤ ምናልባትም በግብርናው ዘርፍ በጣም ልዩ የሚባል ትልቅ ግኝት ወይም ሳይንስ የሚባለው ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።
ጥቂት ስለ ሳይንሱ ስናይ ጂን ኤዲቲንግ እና ጂን ሞዲፊኬሽን የሚባሉ የቴክኖሎጂ ሂደቶች ይኖሩታል።
ጂን ኤዲቲንግ የአንድን ዘረ መል ክፍልን በማውጣት የሚፈለገውን ግብ የሚያስገኝ ነው።
ጂን ሞዲፊኬሽን በበኩሉ የተወሰነ ዘረ መል ከሌላ ዝርያ ጭምር በመጨመር የሚፈለገውን ግብ ማግኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።
ይህ አዲስ ሳይንስ አይደለም ብለው የሚሞግቱም አልጠፉም።
ሰዎች በአነስተኛ ደረጃ ረዥም ጊዜ ወስደው ሲያከናውኑት መቆታቸውን ይገልጻሉ።
በቆሎን በዚህ መልክ በማሻሻል አሁን ስዊትኮርን (ጣፋጭ የሆነ በቆሎ) የሚባለውን የበቆሎ ዓይነት ለማግኘት ችለዋል ይላሉ።
አሁን ያለው የጄነቲክ ምኅንድስና ግን ዘረ መሉን በቀጥታ በመቀየር ማዳቀልን በመተው ረዥም ዓመታት የሚወስደውን አሠራር ማስቀረቱን ይናገራሉ።
እከሌ የተባለው የግብርና ምርምር በማዳቀል እገሌ የሚባል ምርጥ ዘር አገኘ ሲባል ሰምተናል።
የአንዳንዶቹ ሃሳብ ከዚህም ጋር ይገናኛል። ይህንንምሰው ሠራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው ሕያዋን በግብርና ምርምር ተቋማት በማዳቀል ከሚገኙ ምርጥ ዘሮች ጋር ያላቸው ልዩነት ጥቂት ነው በሚል ይገልጻሉ።
የሕዝብ ብዛት እና የምግብ እጥረት
የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው።
በቅርቡ 8 ቢሊዮንም ደርሷል።
“ይህን ሕዝብ እየመገበን መቆየት ከቻልን ትልቅ ነገር ነው” የሚሉት ዶ/ር ታደሠ፤ ይህ ግን “ትልቅ ፈተና” መሆኑን ይጠቁማሉ።
“የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ መጠቀም መቻል ያስፈልጋል። አንዱ የግብርና ቴክኖሎጂ ደግሞ ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ ነው። የእንስሳት እና የእጽዋት ዘረ መል የሚሻሻለውም ለዚሁ ተግባር ነው” ይላሉ።
“እኔ የምግብ ባለሙያ ነኝ። የምግብ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የድኅረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነኝ። የምሠራው ማንኛውንም ጂምኦንም ተጠቅመን የምግብን ምርት መጨመር ግዴታችን ነው።”
ጂኤምኦን የሚደግፉ አካላት ይህ ሳይንስ ብዙ ምርት እንዲገኝ፣ በሽታን ወይም ድርቅን የሚቋቋሙ ባህሪያትን እንዲዳብር እና ሌሎችንም ጉዳዮች ያነሳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሚነሱት ስጋቶች በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳት፣ በባህላዊ የግብርና አሰራር ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲሁም የኩባንያዎች የበላይነት እና የቴክኖሎጂው “ከተፈጥሮ ውጪ” ነው የሚሉ ናቸው።
ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው ምግቦች ጎጂዎች ናቸው የሚለው አሁንም እንዳከራከረ ነው።
ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች እክሎችን እንደሚያስከትሉ በርካታ ሪፖርቶች ቢወጡም ዶክተር ታደሰ በጤና ደረጃ በሳይንስ የተረጋገጠ ሪፖርት አይደለም ይላሉ።
“በጤና ደረጃ በሳይንስ ተረጋገጦ ሪፖርት የተደረገም ምንም ዓይነት ነገር የለም። ካንሰር ያመጣሉ፣ ሌላም ችግር አለባቸው፣ ዘረ መል ይቀይራሉ ሁሉ ተብሎ ይነገራል። በሸማቾች፣ በተጠቃሚዎች ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ በአክቲቪስቶች የሚነሱ ጥያቄች አሉ። ነገር ግን በሳይንስ የተረጋገጠ ምንም አይነት ችግር የለም።”
ተመራማሪው እንደሚሉት ዘረ መላቸው የተቀየሩ እንስሳት እና እጽዋት ከሌሎቹ ከተለመዱ እንስሳት እና እጽዋት የተለየ የምግብ ወይም ኬሚካላዊ ይዘት የላቸውም። ስለዚህ በሳይንስ ምንም ዓይነት የጤና ወይንም ከዚህ ጋር የሚያያዙ ነገሮች አላቸው ተብሎ እንደማይታመን ያስረዳሉ።
“የምግብ ደኅንነት ላይም እሠራለሁ። በዚህም ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው ምግቦች በጤንነት ላይ ያላቸውብ ጎጂም ሆነ ጠቃሚ ገጽታዎችን ነው የምመለከተው። ባለሙያዎች የሚስማሙበት አንድ ነገር ጂኤምኦ ለምግብነት በጣም ወሳኝ ናቸው።”
ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ጥሩ ቴክኖሎጂ ቢሆኑም እንኳን በአካባቢ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት ግን በጥንቃቄ መታየት አለበት በሚለው ላይ ይስማማሉ።
ጥቅሙ እና ያለ ተሞክሮ
በጥቅም ደረጃ ስንመለከት ተክሎች እና እጽዋት ተፈላጊ ነገራቸውን ለመጨመር እና የዓለም የምግብ አቅርቦትንና የምግብ ምርትን ለማሻሻል ትልቅ ሚና አላቸው።
“ጎልደን ራይስ ፕሮጀከት” ወይም በግርድፉ “ወርቃማው የሩዝ ፕሮጀክት” የሚባለው ፕሮጀክት በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ነው።
የምግብ ሳይንቲስቶች መደበኛውን ሩዝ በቫይታሚን ኤ እንዲበለጽግ አደረጉ። የቫይታሚን ኤ እጥረት በመኖሩ የህጻናት ሞት እና ዐይነ ስውርነት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ይህንን ሩዝ ያመርቱ ጀመር።
አንድ ኩባያ ወርቃማው ሩዝ አንድ ሰው ከሚያስፈልገው ዕለታዊ የቫይታሚን ኤ የፍጆታ መጠን ግማሹን ይሰጣል።
ሩዙ ጠቀሜታው ጎልቶ ቢነገረም በተለያዩ አገራት መሰናክሎች ገጥመውታል። በፊሊፒንስ ተቃዋሚዎች ሠልፍ ከመውጣት ጀምሮ ለሙከራ የተተከለውን ሩዝ እስከማጥፋት ደርሰው ነበር።
በዚህ የግብርና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ማምረትም ይቻላል። ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችንም እንደዚሁ።
እነዚህ ማሻሻያዎች ረሃብ እና ድርቅ ላሉባቸው አካባቢዎች ፍቱን ይሆናሉ ማለት ነው።
ይህ ማለት ግን ስጋት የላቸውም ማለት አይደለም።
“በመጀመሪያ ጎልቶ የሚወጣው በአካበቢ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ነው። እኔም የምስማማበት ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች የሚስማሙበትም ነው። እነዚህ በተለይ ዘረ መላቸው የተቀየሩ ትራንስጄኒክ የምንላቸው ካልተዛመዱ እንስሳት ወይንም እጽዋት ብዙ ጊዜ ከጀርሞች ዘረ መላቸው መጥቶ እንስሳት ወይንም እጽዋት ውስጥ ሲገባ ዘረ መላቸው በዘራቸው ውስጥ ይዛመታል ተብሎ ይጠረጠራል።
“ይህ ደግሞ ወደፊት አካባቢ ላይ የሚያመጣው ችግር አይታወቅም። ዘረ መል ኢቮሉሽን ወይንም ዘገምተኛ የሆነ ለውጥ ውስጥ ነው ሁሌም ያለው። ይህ ነገር ለአካባቢ ጥሩ ያልሆነ ነገር ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ጥርጣሬ አለ። ይህንን ሳይንቲስቶችም እኔም እጋራዋለሁ” ይላሉ።
በጤና በኩል ግን የሚያመጡት ወደፊትም የሚጠረጠር የሚያሰጋ ነገር የለም ሲሉ ተመራማሪው አበክረው ያስረዳሉ።
ሌላኛው ስጋት ደግሞ የአረም ጉዳይ ነው።
አንዳንዶቹ በዚህ ዘዴ የሚገኙ ምርቶች ከተጋላጭነታቸው አንጻር ከፍተኛ ፀረ አረም ይፈልጋሉ።
ሌሎቹ ዝርያዎች ደግሞ በእራሳቸው አረምን ማጥፋት የሚችሉ ናቸው።
ይህ ደግሞ ‘ጠቃሚ’ አረሞችን እስከ ወዲያኛው ሊያጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ያሳድራል።
ከዚህ አንጻር የትኛው ጎን የተሻለ ነው? ከተባለ ግን ጥቅማቸው ያመዝናል።
ብዙም የማይነገረው የዚህ ዘርፍ ደካማ ጎን የባለቤትነት ጥያቄው ነው።
ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው ሕያዋን ባለቤትነት በትልልቅ ኩባንያዎች የተያዘ ነው።
በነባሩ አስተራረስ ገበሬዎች ለሚቀጥለው ዓመት የሚተክሉትን ዘር ከዘንድሮው ዓመት ምርት ቀንሰው ያስቀምጣሉ።
ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው ሕያዋን ባለቤትነት በኩባንያዎች ከተያዘ ግን ይህ አይሳካም።
በየዓመቱ ዘሩን ከኩባንያዎቹ እንዲገዙ ሊያስገድዱ ይችላሉ።
ይህን ካልሆነ አምራቾች ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ማለት ነው።
ቢቢሲ፡ ስለዚህ እርስዎ ጠቃሚ ጎኑን ነው የሚቀበሉት?
ዶ/ር ታደሠ፡ እጅግ በጣም። ምክንያቱም ማስቀመጥ ይቻላል። ለምሳሌ በ2050 የዓለም የሕዝብ ቁጥር 9.3 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የምግብ ጥናት ኢንስትቲዩት እንዳሳየው በዚህ ጊዜ 70 በመቶ ተጨማሪ የምግብ አቅርቦት ዓለም ይፈልጋል። ይህን ለማሟላት ቢቻል ማንኛውንም ቴክኖሎጂ ሳንመርጥ መጠቀም አለብን ብዬ አስባለሁ። አሁን ያሉትን ጂኤምኦ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ቴክኖሎጂ ካላመጣን እና ካላወጣን ይህንን ሕዝብ ቀልቦ መቀጠል አይቻልም የሚል እምነት ስላለኝ ጂኤምኦ እንደማንኛው አገር ምንም ሳንመርጥ በተለይ ታዳጊ አገራት እጅግ በጣም ሊጠቀሙበት ይገባል። ምክንያቱም ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ።
ዘረ መላቸው የተለወጠ ምግቦችን መመገብ
ቢቢሲ፡ እርስዎ ተመግበው ያውቃሉ ጂኤምኦ የሆኑ ምግቦችን?
ዶ/ር ታደሠ፡ በትክክል ተመግቤ አውቃለሁ።
ቢቢሲ፡ አውቀው ነው ሳያውቁ?
ዶ/ር ታደሠ፡ አውቄ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕብረተሰብ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተመጋቢም ተጋላጭም ነው። ለምሳሌ ከውጭ የሚገቡ የእርዳታ እህሎች በአንድም በሌላ መልክም ዘረ መላቸው የተለወጠ ነው። ምሳሌ ማንሳት እችላለሁ አሜሪካ አገር የሚመረተው በቆሎ 93 በመቶ ዘረ መሉ የተቀየረ ነው። አሜሪካ ለኢትዮጵያ በቆሎ ወይም ዘይት በእርዳታ መልክ ታቀርባለች። እነዚህ ምርቶች የተገኙት ዘረ መላቸው ከተቀየሩ እህሎች ወይም ዝርያ እንደሆነ እሙን ነው። እየተመገብነው ነው የመጣነው ወደፊትም እየተመገብነው እንቀጥላለን። ዛሬ በረሃብ ከመሞት በቴክኖሎጂ የተሻሻሉትን ተመግበን ነገ የሚመጣውን ችግር መጋፈጡ ይቀድማል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ አውቄም ተመግቤያለሁ። የተሻጉ ምርቶች ላይ 'ጂኤምኦ' እና 'ነን ጂምኦ' ተብሎ የተጻፈባቸው አሉ። ብዙ ጊዜ ጂኤምኦ በማየት ማወቅ ይቻላል። እኔ ጂኤምኦ ተብሎ የተጻፈባቸውን ተመግቢያለሁ። አውቄ ጉዳት ስለሌለው ወይንም የማምንበት ነገር ስለሌለ ነው።
ቢቢሲ፡ በዚህ ዘርፍ ምን እንቅስቃሴ አለ?
ዶ/ር ታደሠ፡ እኔ ባለኝ መረጃ በመንግሥት ተቀባይነት ኖሮት ምርት ውስጥ የገባው ጥጥ ብቻ ነው። የምግብ አዝዕርቶች በእርዳታ ከሚመጡት በስተቀር በመንግሥት እውቅና አገር ውስጥ ገብቶ በምርት በእንቅስቃሴ ላይ ያለ ነገር የለም። በተፈጥሮ የጂኤምኦ ምርቶች በጣም ውድ ናቸው። ግብዓቶቹን እና ፓኬጆቹን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ሜካናይዝድ የሆነ የግል ዘርፍ ወይንም ፕራይቬት ኢንቴንሲዘቭ እርሻ ይፈልጋል። ኢትዮጵያ አነስተኛ ይዞታ ባላቸው ገበሬዎች ደረጃ የሚተገበር ስላለሆነ ምርት ላይ አለ የሚል እምት የለኝም።
ጥጡ ቅርብ ጊዜ ነው የገባው ግንዛቤ ማስጨበጫ በግብርና ሚኒስቴር እና በግብርና ምርምር ኢንስቲዩቶች ተሰርቷል። ጥጥ ደግሞ በባህሪው የሚመረተው በግል እርሻዎች ውስጥ ስለሆነ ማንኛውንም ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን አብሮ መጠቀም ስለሚቻል እሱ ላይ በገፍ እየተሠራበት እና ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን በተለይም እየተስፋፋ ያለው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ጋር በተያያዘ በርካታ እንደሆነ በቂ መረጃ አለኝ። በዘርፉ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠሩ መሆኑን ያየኋቸው እኔም የተሳተፍኩባቸው አሉ።
ይህን ለማሳካት ደግሞ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው መንግሥት አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት አለባቸው ይላሉ።
“ጉዳቱን እና ጠቀሜታውን በትክክል ሕዝቡ ተረድቶት እንዲጠቀም ያሉት ውዥንብሮች እና ብዥታዎች እንዲጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል” ይላሉ።
እነዚህም ምርቶች በመጠቀም ረገድ አውሮፓን እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ባለሙያው፣ አመራጮች አሏቸው፣ የሕዝብ ቁጥራቸውም አነስተኛ ነው በማለት የምግብ እጥረት ችግር እንደማያሳስባቸው ጥጠቅሳሉ።
“እኛ ጋር ግን የምግብ ችግር አለብን። የግንዛቤ ችግርም አለ። ስለዚህ ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠሪያ ንቅናቄ መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ይገልጻሉ።
ለዚህ ግን የሕብረተሰቡን የምግብ ፍላጎት እና የምግብ ደኅንነት ባስጠበቀ መልኩ መመሪያ እና ግልጽ ፖሊሲ ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ።
ኬንያ የጤና ጉዳት ያመጣል በሚል ለአስርት ዓመታት አግዳ ያቆየቻቸው ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው የእህል ዘሮች እና የእንስሳት ምግቦች ጥቅም ላይ እንዲወሉ እና ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በቅርቡ ፈቀዳለች።
“እኔ እንደ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንዲሁም ዓለም ላይ ያለው የሕዝብ ቁጥር ጫና መጨመርን እንደሚረዳ ሰው፣ ይህ በሁሉም አገራት እና መንግሥታት መፈቀድ አለበት። ኬንያ መንግሥት መፍቀዱ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። ይህም ዓለምን ለመመገብ ቴክኖሎጂ የሰጠውን ሃብት እና ቴክኒክ ለመጠቀም ቁርጠኝነት እና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ማድረግ ያለበትን ነው ብዬ አምናለሁ።”
ዶ/ር ታደሠ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው በማንሳት፣ ሕብረተሰቡም መረጃ ከተዓማኒ ሚዲያዎች እና ከመንግሥት አካላት እየወሰዱ ቴክኖሎጂውን በመልመድ እና በማላመድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
በተለይም እንደኬንያ ያሉ አገራት ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው የእህል ዘሮች እና የእንስሳት ምግቦች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመፍቀዳቸው ድንበር ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት ብለዋል።
ይህንን ደግሞ የሚሉት አካባቢ ላይ በሂደት የሚያስከትለው ጉዳት ስለማይታወቅ መሆኑን ይናገራሉ።
“ቁጥጥር ካልተደረገ ጥሩ ስለማይሆን ቁጥጥር ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ሕጋዊ በሆነ እና በተጠና መልኩ ግን መፈቀድ አለበት። የምግብ ደኅንነት ችግር በሆነበት ዓለም ላይ ቴክኖሎጂ መምረጥ የምንችለበት ቅንጦት ላይ አይደለንም።”
ሰው ሠራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገበት ድንች፣ እንሰት እና በቆሎ ለመሞከር እየተሠራ መሆኑ የሚናገሩት ተመራማሪው፣ ይህም ጥረት “መበረታታት አለበት” በማለት ይመክራሉ።
በጉዳዩ ላይ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ጨምሮ የሚመለከታቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት አካላትን በማነጋገር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።