የአገሪቱ ባለሥልጣናት መነጋገሪያ የሆነው ከነፍሳት የሚሠራው የጣልያን ፓስታ

ከነፍሳት የሚሠራው የጣልያን ፓስታ

በሰሜን ጣልያን አልፕስ አቅራቢያ በሚገኝ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ‘ክሪኬት’ የተባለው የፌንጣ ዝርያ ነፍሳት ተሰብስበዋል።

ይዘላሉ። ድምጽ ያሰማሉ። እነዚህ ነፍሳት ምግብ ሆነዋል።

መጀመሪያ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቀመጣሉ፣ ይቀቀላሉ ከዚያም ይደርቃሉ። መጨረሻ ላይ በደቃቁ ይፈጫሉ።

ጣልያን የሚገኘው ፋብሪካ ነፍሳቱን ወደ ምግብነት ይቀይራል። በፋብሪካው በየቀኑ አንድ ሚሊዮን ክሪኬቶችን ለምግብነት እንዲሆኑ ያዘጋጃል።

የፋብሪካው ባለቤት ኢቫን አልቤኖ ይባላል።

ፓስታ፣ ዳቦ፣ ፓንኬክ፣ ኃይል ሰጭ ብስኩት እንዲሁም መጠጥ የሚሆነውን ዱቄት ያስጎበኛል።

ክሪኬቶችን ብቻ ሳይሆን ጉንዳን እና ሌሎችም ነፍሳትን መመገብ በእስያ ለሺዎች ዓመታት የተለመደ ነው።

አሁን የአውሮፓ ኅብረት ነፍሳት ለሰው ምግብነት ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ፈቅዷል።

ዩጎቭ የተባለ ተቋም የሠራው ጥናት የሚጠቁመው ጣልያን ውስጥ ነፍሳትን መመገብ ከመንግሥት አመራሮች አንስቶ ተቃውሞ ገጥሞታል።

በፒዛ እና በፓስታ ምርት ውስጥ ነፍሳትን መጠቀም እስከመከልከል ደርሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ “በየትኛውም መንገድ ተቃውሞ እንገልጻለን። ይሄ እብደት ነው። ግብርናችንን፣ ባህላችንንም ያውካል” ብለዋል።

ጣልያናዊ ፋብሪካዎች ግን ነፍሳትን ለምግብ ግብዓትነት እያዋሉ ይገኛሉ።

ኢቫን እንደሚለው ሥራቸው ዘላቂነት ያለው ነው።

“አንድ ኪሎ የክሪኬት (ፌንጣ መሰል ነፍሳት) ዱቄትን ለማምረት 12 ሊትር ውሃ ብቻ ነው የምንጠቀመው። ከአንዲት ላም ከዚህ እኩል የሆነ ፕሮቲን ለማምረት በሺዎች የሚቆጠር ሊትር ውሃ ያስፈልጋል።”

ነፍሳትን ማርባት ቀንድ ከብት ማርባት ከሚያስፈልገው ቦታ ባነሰ ነው የሚከናወነው። የሥጋ እና የወተት ምርት ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ስማቸው ይነሳል።

ነፍሳት ግን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ይውላሉ፣ ሲሉ ሳይንቲስቶች ይከራከራሉ።

እዚያው ጣልያን ውስጥ ቱሪን አቅራቢያ በሚገኝ ሬስቶራንት ምግብ አብሳዩ ሲሞን ሎዶ፣ ፓስታ የሚሠራው 1 ሺህ ዓመታት ባስቆጠረ የምግብ አሠራር ነው።

ዱቄቱ 15 በመቶ ክሪኬት ነው።

ጠንከር ያለ መዓዛ አለው።

አንዳንዶች ምግቡን ለመሞከር አይፈቅዱም። ይህንን ዘገባ የጻፈችው የቢቢሲ ዘጋቢ እንዲሁም ሌሎችም ምግቡን የሞከሩ ሰዎች ምግቡ እንደጣፈጣቸው ይናገራሉ።

ጣዕሙ ብቻ ሳይሆን ምግቡ በቫይታሚን፣ በፋይበር (አሰር)፣ በማዕድናት እና አሚኖ አሲድ የተሞላ ነው።

ዋጋው ግን ወደድ ይላል።

ኢቫን እንደሚለው “ክሪኬት ያለው ምግብ ከፈለጉ ኪስዎ ይፈተናል።”

ዱቄቱ “የቅንጦት ግብዓት” ከሚባሉት መካከል ነው።

አንድ ኪሎግራም 60 ዮሮ ያወጣል። ፓስታው ስምንት ዩሮ ይሸጣል።

በመደብር ከሚሸጠው ፓስታ ስምንት እጥፍ ይወደዳል።

የሥጋ ዋጋ ከዚህ ያነሰ መሆኑን የሚገልጸው ሥጋ አምራቹ ክላውዲዮ ላውቴሪ ነው።

ሥጋ ማኅበራዊ ተቀባይነትም አለው።

ከነፍሳት የተዘጋጀው ምግብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ከነፍሳት የተዘጋጀው ምግብ

በጣልያን እስከ 100፣ ከዚያ በላይም የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ለዚህ ምክንያቱ የሜዲትራኒያን ምግብ መሆኑን የሚያምኑም አሉ።

ክላውዲዮ እንደሚለው ጣልያናውያን በተመጣጠነ ሁኔታ ሥጋ መብላት ያዘወትራሉ። የነፍሳት ምግብ ግን ለጣልያን የአመጋገብ ሥርዓት ስጋት እንደሆነ ይናገራል።

“እነዚህ ምርቶች ዝቃጭ ናቸው። አለመድናቸውም። የሜዲትራኒያን አመጋገብ አካል አይደሉም። ለሰዎች አስጊ ሊሆኑን ይችላሉ። ነፍሳት መብላት ሰውነታችንን ምን እንደሚያደርገው አናውቅም። እነዚህን ምግቦች እነቅፋለሁ። አልበላቸውም።”

የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔውን ሲያጸድቅ ተቃዋሚ የነበሩት የጣልያን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ሲሆኑ ውሳኔውን “እብደት ነው” ሲሉ ነበር የተቃወሙት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ጣልያን “የምግብ ማዕከል” ናት ይላሉ። ምርጫ ያሸነፉትም የጣልያንን ባህል ለመጠበቅ ቃል በመግባት ነው።

“የነፍሳት ምርቶች ወደ መደብር እየገቡ ነው” በማለትም እየቀፈፋቸው ቪድዮ ቀርፀው ለቀዋል መሪዋ።

የጣልያን አመራሮች ነፍሳት ከጣልያን ምግብ ጋር እንዲተሳሰሩ ስለማይፈልጉ ምርቶቹ በግልጽ ከጣልያን ምግብ ጋር እንዳይቀላቀሉ ይፈልጋሉ።

ከነፍሳት የሚሠራው የጣልያን ፓስታ

የነፍሳት ምግብ አወዛጋቢ የሆነው በጣልያን ብቻ ሳይሆን በፖላንድም ጭምር ነው።

ከአገር አቀፍ ምርጫ አስቀድሞ ጉዳዩ እያነጋገረ ይገኛል።

ሁለቱ የአገሪቱ ትልልቅ ፓርቲዎች አንዳቸው ሌላቸውን የሚወቅሱት ዜጎች ‘ነፍሳት እንዲመገቡ በማስገደድ’ እንደሆነ ተዘግቧል።

ዋና ተቃዋሚ ፓርቲውን የሚመራው ዶናልድ ተስክ፣ መንግሥት ‘የነፍሳት ሾርባ እያበረታታ ነው’ ሲል ወቅሷል።

የክሪኬት ቴላቴሊ የሚሸጠው ዳንኤል ስኮጋሚልዮ “ነፍሳትን ስለመመገብ ብዙ የተዛባ መረጃ አለ” ይላል።

“ብዙዎች ጥላቻቸውን ይገልጹልኛል። የምግብ ባህላቸው ሲቀየር ደስ አይላቸውም” ሲል ያስረዳል።

ሆኖም ግን ሬስቶራንቱ ውስጥ ብዙዎች ለመቅመስ ሲሉ የክሪኬት ምግብ ያዛሉ።

ስምንት ቢሊዮን የደረሰው የዓለም ሕዝብ ምግብን ጨምሮ የመሠረታዊ ግብዓቶች እጥረት ሊገጥመው እንደሚችል ስጋቶች ይሰማሉ።

በመላው ዓለም የምግብ ምርት 70 በመቶ መጨመር እንዳለበት የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ተቋም ይገልጻል።

የፕሮቲን ምንጭ የሆኑ ነፍሳትን መመገብ ግዴታ ሊሆን ይችላል።

ኢቫንም የሚለው ይሄንኑ ነው። “አካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዜሮ ነው። ዓለምን የምናድነው እኛ እንሆን ይሆናል” ሲል አቋሙን ይገልጻል።