የሱዳን ጦር ሠራዊት በዋና ከተማዋ ካርቱም ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በተቀናቃኙ ኃይሎች መገኛ ቦታዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ተገለጸ።
ባለፉት ሳምንታት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአገሪቱ ጦር ላይ የበላይትን በመያዝ በቁጥጥሩ ስር የሚያስገባቸው አካባቢዎች ስለመጨመራቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
በቅርቡም በጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከካርቱም በቅርብ ርቀት በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ “ትልቅ ዘመቻ” ማካሄዱን ገልጿል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በካርቱም፣ በኦምዱርማን እና በአገሪቱ ምዕራባዊ ክልል ዳርፉር ውስጥ ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቷል።
በተለይ በመዲናዋ እና በኦምዱርማን ጎዳናዎች ላይ አስከሬኖች ወድቀው እንደታዩ የዐይን እማኞች ለዜና ወኪሎች ተናግረው ነበር።
ሰባት ወራት ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ለማቀራረብ የተደረጉት ጥረቶች በሙሉ አልተሳኩም።
ባለፉት ወራት ጦርነት በማቆም ከስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች እንዲሁም የአካባቢው አገራት ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን አልተሳካላቸውም።
ይልቁንም በሱዳን የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ሚሊሻዎች አንዳቸው ከሌላኛው ጋር ወግነው እንደሚዋጉ እየገለጹ ይገኛሉ።
በቅርቡም የፍትሕ እና እኩልነት ንቅናቄ (ጄም) እና የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ (ኤስኤልኤም) የተባሉ ሁለት አማጺ ቡድኖች ከመንግሥት ሠራዊት ጋር በመሆን የጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎን ጦር ለመውጋት ዝግጁ ነን ብለው ነበር።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉንም በውጭ መንግሥታት እና በሱዳን ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የአረብ ሚሊሻዎች ታግዞ በውጊያ አውዶች በአገሪቱ ጦር ላይ ድል እያስመዘገበ ይገኛል።
የሱዳን ጦር መሪ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አበደል ፈታህ አል-ቡርሃን ደግሞ ድጋፍ ለማሰባሰብ በቅርቡ በጎረቤት አገራት ጉብኝት ሲያደርጉ ነበር።
ጄኔራሉ በቅርቡ ወደ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ይታወሳል።
ከሰባት ወራት በላይ ያስቆጠረው ውጊያ ቢያንስ ከ7ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ ያሳያል።












