እስራኤል ‘አሸባሪ አገር’ ናት ያለችው አየርላንዳዊት ከሥራ ተባረረች

ኮርኒ ኬሪ የተባለች አየርላንዳዊት እስራኤል “አሸባሪ አገር ናት” ብላ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመጻፏ ከአየርላንድ የቴክኖሎጂ ተቋም ተባረረች።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር ከሥራ የተባረረችው በፖለቲካዊ አቋሟ እንደሆነ ካመነች ጉዳዩን ወደ ሕግ አካል እንድትወስደው ነግረዋል።

ዊክስ ከሚባል የቴክኖሎጂ ተቋም ነው የተባረረችው። በደብሊን ወደ 500 የሚጠጉ ሠራተኞች አሉት።

ኮርኒ ኋላ ላይ ማንኛውም ነውጥ በማንም ቢፈጸም እንደምትኮንን ገልጻለች።

ተቋሙ “ነጻና ግልጽ ነው” ሲሉ መሪው ኒር ዞሀር ተናግረዋል። “የማንንም የፖለቲካ ምልከታ አንገድብም” ብለዋል።

ሆኖም ግን ኮርኒ “ተመሳሳይ ነውጠኛ መልዕክት” አስተላልፋ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷት ነበር ብለዋል። ተቋሙ “ሊያሰናብታት የወሰነውም” በዚህ ምክንያት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ጉዳዩ በአየርላንድ የታችኛው ምክር ቤት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝሩን እንደማያውቁ ገልጸው ኮርኒ ጥያቄዋን በሕግ መያዝ እንደምትችል ገልጸዋል።

በአየርላንድ የሠራተኞች ሕግ አንድን ሰው በፖለቲካ አቋም ከሥራ ማባረር አይፈቀድም ብለዋል።

“የተባረረችው ሰው ከሠራተኞች ማኅበር ወይም ከጠበቃ ምክር እንድትጠይቅ ነው የምመክራት። በተሳሳተ መንገድ ከሆነ የተባረረችው መፍትሄ ይኖራል” ሲሉ አክለዋል።

አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው ዊክስ የተባለው ተቋም የሠራተኞች መልዕክት መለዋወጫ ከፍቷል። ይህም “የእስራኤልን ትርክት ለመደገፍ” ነው ተብሏል።

ሠራተኞች ቪድዮ በመሥራት ስለ እስራኤል-ጋዛ ጦርነት “በዓለም አቀፍ ዕይታ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ” እንደሚበረታቱም ተገልጿል።

አንድ የምክር ቤት አባል የሠራተኛዋ መባረር “በሺዎች በሚቆጠሩና አስከፊውን ጦርነት በሚቃወሙ ሠራተኞች ላይ ጫና የሚያሳድር ነው” ሲሉ ተቃውመዋል።

ሠራተኞች በፖለቲካ አቋማቸው ከሥራ በማረራቸው አደገኛ አካሄድ ነውም ብለዋል።

ሌላ የምክር ቤት አባልም “አገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነባት ናት። ክርክር፣ የሐሳብ ልዩነትም ይከበራል” ብለዋል።

በእስራኤልና አየርላንድ መካከል ያለው ግንኙነትን በተመለከተ ንግግር እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው የሠራተኛዋ መባረር የተሰማው።

የአየርላንድ ፕሬዝዳንት ማይክል ዲ ሂጊንስ እስራኤል ሐማስ ለፈጸመው ጥቃትና እገታ ምላሽ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳ ጥቃት እንደፈጸመች ተናግረዋል።

በአየርላንድ የእስራኤል አምባሳደር ዳና ኤርሊጅ፣ ፕሬዝዳንቱን “የተዛባ መረጃ እንዳላቸው” ተችተዋል። አየርላንድ በጦርነቱ ገለልተኛነቷንም ጠይቀዋል።

“በአየርላንድ ለእስራኤል የተዛባ ምልከታ አለ” ብለዋል አምባሳደሩ።

የእስራኤል ኤምባሲ ሠራተኛ አየርላንድ ሐማስን ትደግፋለች የሚል ጽሑፍ ኤክስ ላይ ጽፈው ኋላ ላይ እንዲጠፋ ተደርጓል።