በአሜሪካ የኃይል ሰጪ መጠጥ ቆርቆሮዎች በስህተት በቮድካ መሞላታቸውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

የአሜሪካ ባለስልጣናት 'ሴልሺየስ' የተባለው ኃይል ሰጪ መጠጥ (energy drink) ቆርቆሮዎች በቮድካ መሞላታቸውን ተከትሎ ተጠቃሚዎች መጠጡን ከመጠቀማቸውን በፊት በአግባቡ እንዲፈትሹ አስጠነቀቀ።

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ማስጠንቀቂያ የተላለፈው 'አስትሮ ቫይብ ብሉ ራዝ' በሚል በሚዘጋጀው የኃይል ሰጪ መጠጡ የጣዕም አይነት ላይ ነው።

ይህ ሁኔታ የተፈጠረው አንድ የማሸጊያ አቅራቢ በስህተት ባዶ የሴልሺየስ ቆርቆሮዎችን 'ሃይ ኑን' ወደተባለ የቮድካ መጠጥ አምራች ኩባንያ በመላኩ ነው። እነዚህ ባዶ የማሸጊያ ቆርቆሮዎች የደረሰቡት ኩባንያው ደግሞ በአልኮል ሞልቷቸዋል።

ቮድካ አምራቹ ኩባንያ በተጨማሪም ይህ ስህተት ከተፈጠረበት ማምረቻ የወጣ 'ቢች ቫሪቲ' በሚል ስያሜ የሚመረት የመጠጥ አይነት ከገበያ እንዲሰበሰብ ጠይቋል።

ይሁን እንጂ እነዚህን ምርቶች በተመለከተ እስካሁን ምንም በሽታ ወይም የጎንዮሽ ጉዳት ስለመድረሱ ሪፖርት እንዳልተደረገ የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር አስታውቋል።

አስተዳደሩ በድረ ገፁ ላይ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ ስህተት የተፈጠረው በሁለት ምርቶች ላይ ነው። እነዚህ ምርቶች በዚህ ሳምንት ከሰኞ እስከ ረቡዕ በነበሩት ቀናት ውስጥ ፍሎሪዳ፣ ኒው ዮርክ፣ ኦሃዮ፣ ደቡብ ካሮላይና፣ ቨርጂኒያ እና ዊስኮንሰን ወደሚገኙ የችርቻሮ ነጋዴዎች እንደተላኩ ተገልጿል።

ከገበያ እንዲሰበሰቡ የሚፈለጉት የኃይል መጠጥ እና የሃይ ኑን መጠጦች የምርት ቁጥርም ይፋ ተደርጓል።

የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር፤ " ሸማቾች፤ ይህ የተፈጠረባቸው የምርት ቁጥሮች የያዙትን የሴልሺየስ አስትሮ ቫይብ ኃይል ሰጪ መጠጥ፣ የስፓርክሊንግ ብሉ ራዝ ምርት ቆርቆሮዎችን እንዲጥሉ እና ፈሳሹን እንዳያጠጡ ይመከራሉ" በማለስ አሳስቧል።

በአስተዳደሩ ከተገለጹት የምርት ቁጥሮች ውጪ ያሉ የሃይ ኑን ቢች ቫራዬቲ ምርቶች ይህ ስህተት እንዳልተፈጠረባቸው እንዲሁም ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ተገልጿል።