ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የቻይና ቀዳሚዋ ነዳጅ አቅራቢ ሆነች
የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ በምዕራባውያን ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ፣ ለቻይና በርካሽ ዋጋ ድፍድፍ ነዳጅ በመሸጥ ትልቋ ነዳጅ አቅራቢ ሆነች።
ከሩሲያን ወደ ቻይና የሚገባው ነዳጅ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ግንቦት ላይ ከፍተኛው ክብረ ወሰን ነው በተባለው 55 በመቶ ጨምሯል።
ይህም የቻይና ከፍተኛ የነዳጅ አቅራቢ የሆነችውን ሳዑዲ አረቢያን ከነበረችበት ደረጃ ዝቅ አድርጓታል።
ምንም እንኳን በኮቪድ ወረርሽን እና በተዳከመው ምጣኔ ሀብት ሳቢያ ፍላጎቱ የቀነሰ ቢሆንም፣ ቻይና ከሩሲያ የምታስገባውን ነዳጅ ጨምራለች።
ባለፈው የካቲት ወር ላይ ቻይና እና ሩሲያ ግንኙነታቸው ወሰን እንደሌለው ገልጸው ነበር።
ከቅርብ ወራት ወዲህ የቻይና ፔትሮሊየምና ኬሚካል ኮርፖሬሽን፣ ሲኖፔክ እና በመንግሥት የሚመራው ዠንዋ ኦይልን ጨምሮ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች፣ሩሲያ ባደረገችው ከፍተና ቅናሽ ምክንያት የሚያስገቡትን ድፍድፍ ነዳጅ መጠን ጨምረዋል።
ሩሲያ የዋጋ ቅናሽ ያደረገችው ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተጣለባትን ማዕቀብ ተከትሎ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ድንበኞች የሩሲያን ነዳጅ በመተዋቸው ነው።
እንደ ቻይና የደንበኞች አጠቃላይ አስተዳደር መረጃ ከሆነ፣ በምሥራቅ ሰርቢያ የፓስፊክ ውቅያኖስ የነዳጅ ማስተላለፊያ እና በባሕር የሚጓጓዘውን ጨምሮ ወደ ቻይና የሚገባው ነዳጅ በአጠቃላይ ባለፈው ወር ላይ 8.42 ሚሊየን ቶን ይጠጋል።
ይህም የቻይና ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ምንጭ የነበረችውን ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ወር 7.82 ሚሊየን ቶን በማቅረብ ይዛ ከነበረው የመጀመሪያ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃነት ዝቅ አድርጓታል።
መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያን ነዳጅ ሊያግዱ እንደሚችሉ የገለጹ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረትም በሩሲያ ጋዝ ላይ ካለው ጥገኝነት ለመላቀቅ እየሰራሁ ነው ብሏል።