አውሮፓ በሩሲያ ላይ በጣለችው ማዕቀብ ከ400 ቢሊየን ዶላር በላይ ታጣለች፡ ፑቲን

የአውሮፓ ሕብረት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ በመጣሉ ምክንያት በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት ኪሳራ ሊያጋጥመው እንደሚችል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።

ሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ በተዘጋጀ ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት መድረክ ላይ ፑቲን እንዳሉት አገራቸው ላይ በተጣለው ማዕቀብ ሳቢያ የአውሮፓ ሕብረት ከ400 ቢሊየን ዶላር በላይ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ሊገጥመው ይችላል ብለዋል።

በ27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ውስጥ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ መሆኑንና ቡድኑ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ በሚጥልበት ጊዜ የአገራቱን ዜጎች ትክክለኛውን ጥቅም ወደጎን ገፍቷል ሲሉ ፑቲን ወቅሰዋል።

ጨምረውም የምጣኔ ሀብት ጫናው ዕቀባው ከተጣለባት ሩሲያ ይልቅ፣ ዕቀባውን በጣሉት አገራት ላይ “የበለጠ ጉዳትን ያስከትላል” ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው "በሩሲያ ላይ እየተካሄደ ያለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕቀባ ከመነሻው አንስቶ ምንም አይነት የመሳካት እድል የለውም” ብለዋል።

ምዕራባውያን ከዩክሬን ወረራ በኋላ በሩሲያ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች “እብደትና የሚያስከትሉትን ጉዳት ያላገናዘቡ ናቸው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተችተዋል።

ምዕራባውያን መንግሥታት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ሩሲያ ላይ ጫናን በመፍጠር እና የራሳቸውን የምጣኔ ሀብት ጥቅም በማስጠበቅ መካከል ሚዛን ለመጠበቅ ሲጥሩ ቆይተዋል።

ነገር ግን አንድ የሩሲያ ባለሥልጣን በአገራቸው ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች በምጣኔ ሀብቷ ላይ ከባድ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አመልክተዋል። የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ኤልቪራ ናቡሊና ሐሙስ ዕለት እንደተናገሩት “የአገሪቱ 15 በመቶ አገራዊ ምርት” በማዕቀቦቹ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቋል።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሩሲያ ያሏቸውን ተቋማት እየለቀቁ ቢወጡም ፑቲን ግን በራቸው ለመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች አሁንም ክፍት እንደሆነ ጥሪ አቅርበዋል።

ፑቲን በተጨማሪም ዩክሬን ውስጥ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፋዊ የምግብ አቅርቦት ቀውስን በተመለከተም፣ ሩሲያ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን የእህል ምርትና ማዳበሪያ በከፍተኛ ደረጃ ልትጨምር እንደምትችል ተናግረዋል። በዚህም አገራቸው የእህል ምርት አቅርቦቷን በ50 ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድግ አቅሙ አላት ብለዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ለዓለም ከፍተኛውን የእህል ምርት የሚያቀርቡ አገራት ሲሆኑ ከወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የጥቁር ባሕር ወደቦቿ በመዘጋታቸው ዩክሬን ምርቷን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልቻለችም።

አሁንም በተለያዩ የዩክሬን አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያዎች እየተካሄዱ ሲሆን ምዕራባውያንም በሩሲያ ላይ ከጣሏቸው ምጣኔ ሀብታዊ ዕቀባዎች በተጨማሪ፣ ዩክሬን እራሷን እንድትከላከልና በጦርነቱ አሸናፊ እንድትሆን ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያወጡ ዘመናዊ የጦር ማሳሪያ ድጋፍ እያደረጉላት ይገኛሉ።