እንግሊዝ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ደረሰች

ኦሌ ዋትኪንስ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠራት ጎል ኔዘርላንድስን 2 ለ 1 ያሸነፈችው እንግሊዝ እሑድ ለሚከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ መድረሷን አረጋገጠች።

ኔዘርላንድ በዣቪ ሳይመንስ አስደናቂ ጎል ጨዋታውን መምራት ብትችልም በደቂቃዎች ልዩነት የእንግሊዙ አምበል ሃሪ ኬን በአጨቃጫቂ ሁኔታ የተገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች አቻ ሆነዋል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቆ እንግሊዝ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ወደ ተጨማሪ ሰዓት ልታመራ ነው ሲባል ነው ዋትኪንስ ተቀይሮ በመግባት የማሸነፊያዋን ጎል ያስቆጠረው።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሰችው እንግሊዝ ፊል ፋደን ካደረጋቸው ሁለት አደገኛ ሙከራዎች የመጀመሪያው በግቡ ቋሚ ሲመለስ ሁለተኛውን ደግሞ የብርቱካናማዎቹ ግብ ጠባቂ አድኖበታል።

ከእረፍት በፊት ዴንዝል ደምፍሪስ ያደረገው ሙከራ በጎሉ አግዳሚ ሲመለስ ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የገቡትን ኔዘርላንዶች ጎል እንዳያስቆጥሩ በረኛው ጆርዳን ፒክፎርድ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

ጨዋታው መገባደጃ ላይ በሃሪ ኬንን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኦሌ ዋትኪንስ ያስቆጠራት ጎል እንግሊዝን ለፍጻሜ አብቅታለች።

በዚህም እንግሊዝ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በቅታለች።

ትችቶችን ሲያስተናግድ የነበረው የአሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት ቡድን በበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም በውድድሩ ጠንካራ መሆኗን በማስመስከር ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ካገኘችው ከስፔን ጋር ይገጥማል።

ከመመራት በመነሳት እያሸነፈች ለፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ በ2020 በመለያ ምት በጣሊያን የተነጠቀችውን ዋንጫ የምታነሳብት ዕድል ተፈጥሮላታል።