ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተወካዮች ምክር ቤት በህወሓት ላይ አሳልፎት የነበረውን የሽብርተኛነት ፍረጃ አነሳ
በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት ተሰይሞ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፍረጃው ተነሳለት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደወሰነው ህወሓት የአገሪቱ መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጃቸው ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ ወስኗል።
ምክር ቤቱ 280 አባላቱ በተገኙበት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ህወሓት ላይ ተላልፎ የነበረውን የሽብርተኝነት ስያሜን በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ሲወስን፣ 61 ተቃውሞ እና አምስት ድምጸ ታዕቅቦ ተመዝግቧል።
በስብሰባው ላይ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ህወሓትን ከሽብርተኛ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ መደረጉ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጉልህ ስም ካላቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ህወሓት ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በትጥቅ ትግል፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በበላይነት በመምራት እና የትግራይ ክልልን በብቸኝነት ሲያስተዳድር ቆይቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ኃይሎቹ ከፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ሲያካሂዱ ቆይተው ከአራት ወራት በፊት በተደረገ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ መቆሙ ይታወሳል።
ከፍተኛ የህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች በጦርነቱ ወቅት መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በእስር ላይ ይገኛሉ።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ፕሪቶሪያ ላይ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በፈረሙት ስምምነት መሰረት ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በትግራይ መደበኛ ሕይወት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ተስማምተዋል።
ከእዚህም መካከል የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንደሚፈቱ እና በቡድኑም ላይ ተጥሎ የነበረው የአሸባሪነት ስያሜ እንዲነሳ እንደሚደረግ ተገልጾ ነበር።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ስምምነት ከተፈረመ ከአራት ወራት በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም. ህወሓትን በሽብር ቡድንነት ያሳለፈውን ውሳኔ እነዲነሳ አድርጎታል።
ህወሓት በሽብርተኝነት በተፈረጀበት ወቅት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርገው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው ቡድንም በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
ሆኖም ግን ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ስሙ ሲነሳ መንግሥት ሸኔ የሚለው ይህ ቡድን ግን ባለበት እንዲቆይ ተደርጓል።
ስለህወሓት በአጭሩ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው።
ከ45 ዓመታት በላይ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ለነበረው ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማኅበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።
ቡድኑ የትጥቅ ትግል በጀመረበት ወቅት ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እና ‘የሪፐብሊክ’ የመመሥረት ጉዳይ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ይህ ሐሳብ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳልቆየ መስራቾቹ ይናገራሉ።
በ1968 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው የድርጅቱ ጉባኤ ‘ነጻዋን ትግራይ’ የሚለው አጀንዳ በአብዛኛው አባል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ውድቅ ተደረገ።
ከዚያም የድርጅቱ አላማ የመደብ ትግል በማድረግ ለጭቁን ሕዝቦችን ‘የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን መብት’ እንደሚታገል በመግለጽ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመሆን ወደሥልጣን ወጥቷል።
ህወሓት ለ17 ዓመታት ባካሄደው የትጥቅ ትግል ወቅት ከፍልሚያ ውስጥ ገብቶ የነበረው ከወታደራዊው መንግሥት ጋር ብቻ አልነበረም።
ቡድኑ የትጥቅ ትግል በሚያደርግበት ጊዜ በተመሳሳይ ወታደራዊው መንግሥትን ተቃውመው ከወጡት ከኢዲዩ፣ ከጀበሃ፣ ከኢህአፓ እና ከሌሎችም ቡድኖች ጋር በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ልዩነት መሠረት በማድረግ ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር።
ነገር ግን ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት እየሰፋ ከትግራይ ባሻገር ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር፣ በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን በማቀፍ እንዲሁም ሊወክሉ ይችላሉ በሚል ድርጅቶችን እንዲቋቋሙ በማድረግ ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግ የተባለውን ግንባር ፈጠረ።
በህወሓት የበላይነት ይመራ ነበር የሚባለው ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም እና በ1987 ዓ.ም አዲስ ሕገ መንግሥት በማጽደቅ ከሁለት አስርታት በላይ ሥልጣን ላይ ቆይቷል።
የአገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን በበላይነት በሚመራው ኢሕአዴግን በበላይነት ተቆጣጥሮ የቆየው ህወሃት በሕዝባዊ ተቃውሞዎች ምክንያት ግንባሩ ውስጥ ለውጦች ሲካሄዱ፣ በህወሓት እና በቀሪው የግንባሩ አባላት መካከል ጎልተው የታዩ ክፈተቶች ተፈጠሩ።
በመጨረሻም የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ጥምረት የነበረው ኢህአዴግ ከስሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሪነት የተመሠረተው የብልጽግና ፓርቲ ሲተካው፣ ህወሓት በአዲሱ ስብስብ ውስጥ ላለመግባት ከመወሰኑ ባሻገር “ውህደቱ ሕጋዊ አደለም” በማለት ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር።
ይህ መቃቃርም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አገራዊ ምርጫ በተሰረዘበት ጊዜ በተናጠል ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ምርጫ ሰበብ የበለጠ ተካሮ ነበር።
ከዚያም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በተከፈተው ጦርነት ምክንያት የህወሓት እና የማዕከላዊው መንግሥት ጠላትነት ይፋ ሆነ።
በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በበላይነት የመራው ህወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም. ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ተሰይሞ ነበር።
ጥር 10/2013 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን ማስታወቁ ይታወሳል።
ቦርዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ህወሓት በአመጽ ተግባር ላይ መሰማራቱን በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጡን በመግለጽ፣ ሕጋዊ ሂደቶችን በመከተል የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት በመሰረዝ ማንም በህወሓት ስም መንቀሳቀስ እንደማይችል ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል።